በንቅለ ተከላ ለሰው የተተካ የአሳማ ኩላሊት ለ271 ቀናት በመሥራት በህክምናው ዘርፍ ክብረ ወሰን ያዘ

የፎቶው ባለመብት, Kate Flock/Massachusetts General Hospital
ከአሳማ የተወሰደ ኩላሊት በአንድ ታካሚ አካል ውስጥ ለ271 ቀናት የሠራ ሲሆን ይህም እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ረጅሙ ጊዜ መሆኑን የአሜሪካ ሐኪሞች ገለፁ።
ሕክምናው የተደረገለት ቲም አንድሪውስ፣ ንቅለ ተከላው ተስፋ ሰጥቶት እንደነበረ እና ደሙን በዲያሊሲስ (በኩላሊት እጥበት) ለማጣራት ወደ ሆስፒታል ከመሄድ ለወራት እንደታደገው ተናግሯል።
በማስ ጄኔራል ብሪግሃም ሆስፒታል ያለው የሕክምና ቡድን አባላት፣ የአሳማ አካላት ከሰው ለጋሽ አካል እስኪገኝ ድረስ "መሸጋገሪይ" ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ጥናታቸው እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ለአንድሪውስ የተገጠመለት የአሳማው ኩላሊት በመጨረሻ መሥራት አቁሞ ከሰውነቱ ተወግዷል። በዚህም ምክንያት ኩላሊት ለጋሽ እስኪያገኝ ድረስ ለአጭር ጊዜ ወደ ዲያሊሲስ መመለስ አስፈልጎት ነበር።
ሐኪሞችና ሳይንቲስቶች ለንቅለ ተከላ የሚውሉ አካላት እጥረት በመኖሩ፣ ዜኖትራንስፕላንቴሽን በመባል የሚታወቀውን ከሌሎች የእንስሳት ዝርያዎች የሚወሰዱ አካላትን በሰው ላይ የመጠቀም ሂደትን እየመረመሩ ነው።
በአሜሪካ በአሁኑ ጊዜ 100 ሺህ ያህል ሰዎች የኩላሊት ልገሳ በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፣ በየዓመቱ 25 ሺህ ንቅለ ተከላዎች ብቻ ይከናወናሉ። በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
አንድሪውስ ዕድሉን ለማግኘት እስከ ሰባት ዓመት ሊፈጅበት እንደሚችል ተነግሮት ነበር። ነገር ግን ሰዎች ዲያሊሲስ በማድረግ በሕይወት መቆየት የሚችሉት በአማካይ አምስት ዓመት ብቻ ነው።
"ጊዜዬ እየተሟጠጠ ነበር... ሁኔታውም በጣም የሚያስጨንቅ ነበር" ሲል ተናግሯል።
ነገር ግን ከአሳማ ተወስዶ የሚደረግ የኩላሊት ንቅለ ተከላን "ተስፋ" እና "ወደፊት መልካም ነገር እንዲጠብቅ" እናዳደረገው ገልጿል።
"ተስፋ ከሁሉ በላይ የሚያስፈልግ ነገር ነው። ከ[ዲያሊሲስ] ማሽን ነፃ የመሆን እና ሕይወትን የመኖር ዕድል ነው" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Kate Flock/Massachusetts General Hospital

የፎቶው ባለመብት, Kate Flock/Massachusetts General Hospital
አሳማዎች ለዜኖትራንስፕላንቴሽን (xenotransplantation) ተስማሚ እንስሳት እንደሆኑ ይታመናል። የአካላቸው መጠን ከሰው አካላት ጋር በአንጻራዊነት የሚመጣጠን ነው።
ነገር ግን ከአንድ አሳማ ላይ ኩላሊት ወስዶ ለሰው መትከል ቀላል አይደለም። ምክንያቱም የሰው አካል ወዲያውኑ የአሳማውን አካል "እንግዳ ነገር" እንደሆነ በመለየት ኩላሊቱን ሊያጠፋ የሚችል ከባድ የመከላከያ ጥቃት ይጀምራል።
ይህ ሂደት በእያንዳንዱ ሴል ላይ ጉዳት በማድረስ ቀዳዳዎችን ስለሚፈጥር እና አካሉ ከውስጥ ወደ ውጭ በደም መርጋት ስለሚጎዳ በደቂቃዎች ውስጥ ኩላሊቱ ቀለሙን ወደ ጥቁር ይለውጣል።
በመሆኑም ተመራማሪዎች 69 የዘረመል ማሻሻያዎች የተደረጉባቸውን የዩካታን (ሜክሲኮ) ትንንሽ የአሳማ ዝርያዎችን አርብተዋል። የዚህም ዓላማ አካላቸውን ከሰው አካል ጋር የበለጠ ተመሳሳይ ማድረግ ነው።
እነዚህ የዘረመል ማሻሻያዎች የሰው የመከላከያ ሥርዓት የአሳማ ህዋሳትን በመለየት እንዲያጠቃ የሚያደርጉ አንዳንድ ባህሪያትን የሚያስወግዱ ናቸው። በተጨማሪም የአሳማው ኅብረ ህዋስ ከሰው በሽታን የመከላከያ ሥርዓት እንዲሸሸግ እንደ የሚያስችል የሰው ዘረ መል (ዲኤንኤ) ጨምረዋል።
በአሳማ ዲኤንኤ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ቫይረሶች ወደ ሰው እንዳይተላለፉ እና ኢንፌክሽን እንዳያስከትሉ የሚያደርጉ ተጨማሪ የጂን ማሻሻያዎችም ተደርገዋል።
አንድሪውስ በዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ ምክንያት ወደ መጨረሻ ደረጃ የደረሰ የኩላሊት በሽታ የነበረበት ሲሆን ኩላሊቶቹም ሥራቸውን እያቆሙ ነበር።
በ2017 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ይህን የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ሲደረግለት 66 ዓመቱ ነበር።
በላንሴት የሕክምና መጽሔት ህትመት ላይ በወጡ ዝርዝሮች መሠረት፣ የተተካለት የአሳማ ኩላሊት ወዲያውኑ ነው መሥራት የጀመረው።
ይህ ኩላሊት ለ271 ቀናት በተሳካ ሁኔታ መሥራቱን ቀጥሎ፣ በዚያው ዓመት ጥቅምት ወር ተወግዷል። ከዚያ በኋላ ቲም ለ82 ቀናት በዲያሊሲስ ሲታገዝ ቆይቶ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ከሰው ለጋሽ የተገኘ ኩላሊት ተተክሎለታል። ያ ኩላሊት እስካሁን በጥሩ ሁኔታ እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል።















