የወርቅ ማዕድን ሠራተኛው ከመገደላቸው በፊት ቤተሰባቸው ከታጣቂዎች ጋር ያደረገው የመጨረሻው የስልክ ምልልስ

አቶ ዳንኤል ቀልቤሳ በቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሰርተዋል

የፎቶው ባለመብት, Family Handover

የምስሉ መግለጫ, አቶ ዳንኤል ቀልቤሳ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ ማገልገላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ተናግረዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ማስጠንቀቂያ፡ ቀጥሎ የሚያነብቡት ታሪክ ሊረብሽዎት ይችላል

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ገንጂ ወረዳ የሚገኘው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት አባታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ምርመራ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ኩባንያው ከጥቃቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ የድርጅቱን አንድ ሠራተኛ ጨምሮ "በርካታ [ሰዎች] ተገድለዋል" ሲል አሳውቋል።

ተቀማጭነቱን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው እና የቱሉ ካፒን የወርቅ ልማት የሚመራው ኬፒ የተሰኘው ኩባንያ በመግለጫው ላይ በጥቃቱ በርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት እና የፀጥታ አካላት መገደላቸውን ከመግለጽ ውጪ ቁጥራቸውን ይፋ አላደረገም።

በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ንብረትም መውደሙን ቢቢሲ ባገኛቸው እና ትክክለኛነታቸውን ባጣራቸው ቪዲዮዎች ለማወቅ ተችሏል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ አቶ ዳንኤል ቀልቤሳ ይባላሉ።

አቶ ዳንኤል ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኩባንያው ውስጥ ማገልገላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ተናግረው እንዴት እንደሞቱ ግን በትክክል ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የቤተሰቡ አባላት ስለ አቶ ዳንኤል አሟሟት ሁለት ነገሮችን መስማታቸውን ይናገራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቃቱ በተፈጸመበት አርብ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም. ቤተሰቡ አቶ ዳንኤልን በስልክ ለማግኘት መቸገራቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ዳንኤል በየጊዜው ለቤተሰባቸው የሚደውሉ ቢሆንም የዚያን ዕለት ግን ከጠዋት ጀምሮ ቢደውሉላቸውም ሊያገኟቸው አልቻለም።

ይሁን እንጂ ከሰዓት በኋላ 9፡30 አካባቢ፣ አንድ ማንነቱን የማያውቁት ሰው በአቶ ዳንኤል ስልክ ደውሎ እንዳናገራቸው ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"የሆነ ሰው ሄሎ አለኝ… ይህ ስልክ የዳንኤል አይደለም? ሲለኝ 'አዎ፣ የዳንኤል ነው አልኩት።' 'ዳንኤል፣ ምንሽ ነው ብሎ ጠየቀኝ" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።

"ዛሬ በእጃችን ገብቷል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ታውቂያለሽ ወይ ብሎ ጠየቀኝ። ካቢኔ ነው አይደል?" አለኝ። 'አይ፣ ዳንኤል ካቢኔ አይደለም። ከማኅበረሰቡ ጋር ነው የሚሠራው' ስል መለስኩለት" ሲሉ አክለዋል።

"ወርቅ ማውጫ ኩባንያ እንደሚሠራ ነገርኩት። ይህንን ከማለቴ በፊት ግን 'እያወቅሽ ነው አይደል የላክሽው' አለኝ፤ 'ምንድን ነው? ይህ እኮ [በወርቅ ማውጫው ውስጥ መሥራት] ለዳንኤል አዲስ ነገር አይደለም'" በማለት ማስረዳታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

"'የፖለቲካ ሥራ ነው አይደል የሚሠራው?' ሲለኝ በሙያው እንደሚሠራ ነገርኩት። ከዚያ 'ልግደልልሽ ታዲያ?' አለኝ። ከዚያ ቀጥሎ ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ" ሲሉ በወቅቱ ከደወለላቸው ሰው ጋር የተነጋገሩትን ያስታውሳሉ።

"እኔም ቀስ እያልኩ መለስኩለት፤ 'ከገደልከው ታሪክ ተጠያቂ ያደርግሃል፣ እግዚአብሔርም ይጠይቅሃል' አልኩት" ሲሉ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላ ቤተሰብ በተደጋጋሚ በመደወል የአቶ ዳንኤልን ድምጽ እንዲያሰማቸው ቢጠይቁም "ሌላ ቡድን ነው እየጠየቀው ያለው" በማለት ሳያገናኟቸው መቅረቱን ገልጸዋል።

'ጭንቅላቱ እና ጆሮው መካከል ተመትቷል'

የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በግድያው ማዘኑን አስታውቋል።

በመግለጫው ላይ ለሠራተኞቹም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምቹ ሁኔታዎች እስኪፈጠሩ ድረስ ወዲያውኑ ሥራ መቋረጡንም ጨምሮ ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች የቤተሰብ አባላት እንዳሉት መጀመርያ የሰሙት የአቶ ዳንኤልን በታጣቂዎቹ መያዝን ነው። በኋላም በተፈጸመው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ይናገራሉ።

ቢቢሲ አቶ ዳንኤልን በምን ምክንያት እንደተገደሉ ወይም እንዴት እንደተገደሉ ከገለልተኛ ወገን አላጣራም።

የአቶ ዳንኤልን አስከሬን ለመለየት አዲስ አበባ ወደሚገኘው ምኒሊክ ሆስፒታል የሄዱ የቤተሰብ አባላት፣ አስከሬናቸውን ለመለየት ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል።

"ፊቱን ለመለየት ትንሽ ችግር አጋጥሞኝ ነበር። ነገር ግን ፀጉሩን፣ እግሮቹን እና ጥፍሩን ስመለከት" አቶ ዳንኤል መሆናቸውን ማወቃቸውን አስረድተዋል።

የወርቅ ማዕድን ውስጥ ሠራተኛ የሆኑት የአቶ ዳንኤል አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ከመላኩ በፊት ገንጂ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

በቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ምሰል

የፎቶው ባለመብት, Screenshot from SM

የምስሉ መግለጫ, በቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ምሰል

ከገንጂ ሆስፒታል ለቤተሰቦቻቸው የተላከው ደብዳቤ በደረታቸው ግራ በኩል እና በጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ከተመቱ በኋላ በከባድ ደም መፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ያስረዳል።

"ጭንቅላቱ እና ጆሮዎቹ መካከል ብዙ ጊዜ ተመትቷል። ሁለተኛው ደግሞ በደረቱ ቀኝ እና ግራ በኩል ተመትቷል" ሲሉ የዳንኤልን አስከሬን በሆስፒታል ውስጥ ያዩት የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ቤተሰቦች የነገሯቸውን ሲያስረዱም፣ የወርቅ ልማት ፕሮጀክቱ ሠራተኞች "ጠዋት ላይ እንደተከበቡ" ይናገራሉ።

"ውስጥ ያሉት እና [የጥበቃ አባላት] ከውጭ የገቡት ታጣቂዎች መታኮስ ጀመሩ። ታጣቂዎች የእያንዳንዱን መኝታ ቤት በሮች እየከፈቱ ሰዎችን ሲፈልጉ ነበር ብለውናል።"

"በዚህ ጊዜ [አቶ ዳንኤል] መኝታ ክፍሉ ውስጥ ነበር። ከጥቃቱ የተረፈው ሰው እንዳለው ሌላ ጊዜ አብረው ያመልጡ ነበር በዚህ ቀን ግን እርሱ ክፍሉ ውስጥ መቅረቱን ነግሮናል።"

"ግለሰቡ 'እኔ እንደምንም ብዬ ወጣሁ። በክፍሉ ውስጥ ነው በጥይት የተመታው። ተመልሰን ስንመጣ ያገኘናቸው ክፍላቸው በር ላይ ተገደለው ነው' ብሎናል" ሲሉ ከጥቃቱ ከተረፉ ቤተሰቦች የሰሙትን ያስረዳሉ።

"በኋላም ጥቃቱ ሲቆም ግለሰቡ ዳንኤልን ከወደቀበት አንስቶ ወደ ሆስፒታል እንደወሰደው ነገረን" ብለዋል።

ቢቢሲ ስለ ግድያው ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻለም። አብዛኞቹ የወረዳው እና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት በክስተቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ለቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ እና ኮሚቴ ተቋቁሞ መግለጫ ሊሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ ላይም የጥቃት ፈጻሚውን ማንነት አላሳወቀም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የወረዳው ባለሥልጣን ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው ወንጀሉን መንግሥት ሸኔ ሲል የሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ፓርላማ 'አሸባሪ' ተብሎ የተፈረጀው ይህ ቡድን ስለግድያው አስካሁን ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን አስተያየት ለማግኘት ለዋና አዛዡ አማካሪ በጽሑፍ መልዕክት ጥያቄ ቢያርብም ምላሽ አላገኘም።

ቢቢሲ ቬሪፋይ የጥቃቱን ቦታ እና ቀንን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የተመለከታቸው ሁለት ቪዲዮዎች ታጣቂዎች በኩባንያው ግቢ ውስጥ ተኩስ ሲከፍቱ ያሳያሉ።

በቪዲዮው ላይ ታጣቂዎቹ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተዋጊዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።

እንዲሁም ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአንድ ሳምንት በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ውስጥ በማዕድን ቁፋሮ እና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩ የውጭ እና የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን አስጠንቅቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኘው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ላይ የተወሰደውን እርምጃም በምሳሌነት ጠቅሷል።

ታጣቂዎቹ ቀደም ሲል በፋብሪካው እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል በሚል ይወነጀላሉ።

"በአጋጣሚ ተገደለ ብለን አናምንም"

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ግድያው ስለተፈጸመበት መንገድ ጥያቄዎች እንዳላቸው እና ከለላ ሊደረግላቸው ይገባ ነበር በማለት ለአቶ ዳንኤል ፍትህ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የቤተሰብ አባል በበኩላቸው ሌሎች ሰዎች በታጣቂዎቹ ተይዘው በሕይወት መትረፋቸውን አቶ ዳንኤል ደግሞ እዚያው ዒላማ ተደርጎ መገደላቸውን በመጥቀስ ለምን? ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ ዳንኤል በጥቃቱ ወቅት ተለይተው ስለመገደላቸው ቢቢሲ አላረጋገጠም።

የአቶ ዳንኤል ሞት "በአጋጣሚ አልነበረም... ሆን ተብሎ የተደረገ ነው" ሲሉ አስከሬኑን የተመለከቱ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።

ሌላኛው የቤተሰብ አባል ደግሞ "አባታችን አባትም እናትም ነው። ለእኛ የእናት ልብ ያለው" በማለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጠንክረው ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ሌላኛው የቤተሰብ አባል በበኩላቸው አቶ ዳንኤል "እሱ ሰላማዊ ሰው ነው፣ ልጆቹን ለማሳደግ የሚሮጥ እና የሚታትር ሰው ነው። እውነቱ መታወቅ አለበት" ብለዋል።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ዳንኤል በኦሮሚያ የውሃ፣ የማዕድን እና የኢነርጂ ቢሮ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ነዋሪዎች፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት እንዲሁም ተሽከርካሪዎች ዒላማ ተደርገው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በዚህም መንግሥት 'ሸኔ' የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስሙ ይነሳል።

ታጣቂዎች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እና እገታዎች የተነሳም በአምዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ስተት እና መስተጓጎል ተፈጥሯል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቃት የተፈጸመበት የወርቅ ማዕድን ማውጫም በደኅንነት ስጋት ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ሥራውን ማቆሙን በይፋ አስታውቋል።