በአበሽጌ እና አዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚፈፀመው ጥቃት "በአካባቢዎቹ አስተዳደር ጭምር የተደገፈ ነው" ሲል አብን ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ አበሽጌ ወረዳ እና በአዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት "በአካባቢዎቹ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ጭምር የተደገፈ ነው" ሲል ከሰሰ።
አብን ትናንት አርብ መስከረም 8፣ 2019 ዓ. ም ባወጣው መግለጫ ይህን ያለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እና በአበሽጌ ወረዳ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና ግድያዎች መፈፀማቸውን ተከትሎ ነው።
ፓርቲው ባቀረበው ክስ ላይ ከክልሎቹ አስተዳደርም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ ምላሽ የለም።
በአበሽጌ ወረዳ ዋልጋ ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ መስከረም 4፣ 2019 ዓ.ም በተፈፀመ የቅርብ ጊዜ ጥቃት ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከተገደሉት በተጨማሪ 20 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጥቃቱን የፈፀሙት 'ፋኖ' ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ ታጣቂ ቡድኑን ከስሰዋል።
ከቀናት በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ፣ በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን እና ሥራውን አጠናቆ ሪፖርት ገና አለማቅረቡን ገልጸዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በበኩሉ፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን እንደሌለው እና "ኃላፊነቱን እንደማይወስድ" ገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን፣ በጥቃቱ ስለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት "የሚያጣራ ቡድን አደራጅተን ልከናል" ያሉ ሲሆን፤ የተገደሉ እና የታገቱ ሰዎች መኖራቸውን ግን አረጋግጠዋል።
አብን ባወጣው መግለጫ፤ የጥቃቱ ሰለባዎች በአካባቢው ለዘመናት የኖሩ የአማራ ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ የጥቃቱ ዓላማ "የግዛት ወሰንን ማስፋት እና ሃብት ንብረትን መንጠቅ" እንደሆነ አመልክቷል።
"ነዋሪዎች ከኖሩበት የኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲፈናቀሉ ከተደረገ በኋላ ይዞታቸው ለአመራሮች እና አጋር ባለሃብቶች ተከፋፍሎ እየተሰጠ ነው" ሲልም ወንጅሏል።
ይህም "አበሽጌ ወረዳን ወደ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን ለማጠቃለል የሚደረግ ሴራ ነው" ብሏል።
ቢቢሲ ክሱን በገለልተኛነት አላረጋገጠም።
አብንም ላቀረበው ክስ ያቀረበው ማስረጃ ባይኖርም በ2016 ዓ.ም. አጋጠመ ያለውን ክስተት አስታውሷል።
"የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለበትን ስጋት በማሳወቅ ከኦነግ ሸኔ ጥቃት ራሱን ለመከላከል ለመደራጀት ጥያቄ ማቅረቡን" በመግለጫው የጠቀሰው አብን፣ "ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው የፀጥታ አመራሮች በሕጋዊ መንገድ የታጠቁትን መሣሪያ በመንጠቅ እና ከጀርባው በመውጋት ሕዝቡን ለጥቃት አጋልጠዋል" ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በአመያ ወረዳ ቆታ እና በዳርጌ አካባቢዎች "በኦሮሚያ አድማ ብተና እና በሸኔ ታጣቂዎች የተቀናጀ ጥቃት ከ54 በላይ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አርሶ አደሮች፣ ስድስት መነኮሳት እና ሦስት አገልጋዮች እና ሌሎች በርካታ ንጹሃን ተጨፍጭፈዋል" ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው ጨምሮም ከሦስት ዓመት በፊት ከወልቂጤ እና ከአበሽጌ ወረዳ የታፈሱ ከ1000 በላይ ሰላማዊ የአማራ ተወላጆች ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሕገ ወጥ ማቆያዎች አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ሲደርስባቸው መቆየቱን አስታውሷል።
አብን በትናንቱ መግለጫው ተጎጂዎችን መልሶ የመክሰስ እና ስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ይህም እየተፈፀመ ያለውን "መዋቅራዊ ጥቃት" አደገኛ ያደርገዋል ብሏል።
"ከዚህ ቀደም የተፈፀሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሲያስተባብሩ የነበሩ የታወቁ የሚዲያ ዘመቻ መሪዎች አሁንም ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው" ሲልም ከስሷል። ሆኖም እነዚህ አካላት እነማን እንደሆኑ በስም አልጠቀሰም።
በሚፈፀሙ ጥቃቶች የጉራጌ እና የኦሮሞ ተወላጆችም ሰለባ መሆናቸውን የገለጸው አብን፣ ድርጊቶቹን አውግዞ፣ የፌደራል መንግሥቱ "በአስተዳደራዊ መዋቅር እና የጸጥታ አካላት የተደገፈ ጥቃት" ሲፈፀም እያየ ዝምታን መምረጡ ወይም እርምጃ አለመውሰዱ "ይሁንታ እንደመስጠት" እንደሚቆጠርም ገልጿል።
ፓርቲው ባቀረበው ክስ ላይ ከክልሎቹ አስተዳደርም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ ምላሽ የለም።
አብን በመግለጫው በአበሽጌ እና በአዋሳኝ ኦሮሚያ አካበቢዎች የሚፈፀሙ "በደሎች እንዲቆሙ፣ ያል አግባብ የታሰሩ ግለሰቦች እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ ራሳቸውን ለመከላከል በሕጋዊ መንገድ የታጠቋቸው መሣሪያዎች እና የተወሰዱባቸው ንብረቶች እንዲመለሱላቸው" ሲል ጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለዜጎች "ገለልተኛ ጥበቃ እንዲደረግ" እና "በጥቃቶች ላይ በተሳተፉ የመንግሥት አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ ታጣቂዎች እንዲሁም ግለሰቦች ለፍትሕ እንዲቀርቡ" ጠይቋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማትም ገለልተኛ ቡድን በማሰማራት ምርመራ እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርቧል።
ኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚጎራበቱበት በዚህ አካባቢ በተደጋጋሚ ጥቃቶች የተፈፀሙ ሲሆን፤ ለጥቃቶቹ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ ሲል በሽብር የፈረጀው፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂ ቡድን እንዲሁም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ፋኖ ይከሰሳሉ።
ቡድኖቹ በተደጋጋሚ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በደረሰ ጥቃት እና ይህንን ተከትሎ በተፈፀመ የአፀፋ ጥቃት ቢያንስ 24 ሰዎች መገደላቸውን ተጎጂዎች እና ነዋሪዎች መግለጻቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎችም በተመሳሳይ በአካባቢው ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያለው "ከመሬት ጋር በተያያዘ ምክንያት" እንደሆነ ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል ኖኖ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ "የአማራ ተወላጆች ለዓመታት ከኖሩበት ቤት እና መሬት መፈናቀላቸውን" ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ የተፈናቀሉት ሰዎች በአጎራባቹ ጉራጌ ዞን መኖር እንደጀመሩ ያስረዳሉ።
እነዚህ ነዋሪዎች ቤታቸው ለሌሎች ነዋሪዎች "ተላልፎ እንደተሰጠ" እና መሬታቸው እንዲመለስላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መፍትሔ እንዳላገኙ መግለፃቸው አይዘነጋም።
አሁንም ከሚኖሩበት አበሽጌ ወረዳ በሚፈፀምባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈናቀሉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።















