አሜሪካ የኢትዮጵያን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማንሳቷን ተግባራዊ ስታደርግ፣ በኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አነሳች

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን ተግባራዊ ሲያደርግ፣ በኤርትራ የመከላከያ ኃይል እና ሌሎች ተቋማት ላይ የጣለውን ማዕቀብ አነሳ።
አሜሪካ ከአምስት ዓመታት በፊት በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዘመን በሁለቱ አገራት ወታደራዊ፣ የፖለቲካ እና ሌሎች ተቋማት አመራሮች እንዲሁም ተቋማት ላይ የተለያዩ ዓይነት ዕቀባዎችን ጥሎ ቆይቷል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የቆየው የጦር መሳሪያ እንደሚነሳ ካሳወቀ በኋላ ውሳኔው ከመስከረም 8/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን ይፋ ሆኗል።
ዳይሬክቶሬቱ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ስትከተል የነበረችውን የክልከላ ፖሊሲ በማንሳት አሁን ላይ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን እና ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ የፈቃድ ማመልከቻዎችን ሲገምግም ቆይቶ ነው የዕገዳው መነሳት ተግባራዊ የሆነው።
በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ዕቀባ መነሳቱን የሚያሳውቅ ደንብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. ይፋ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ዝውውር ክልከላ ደንብ ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ አገራት ተርታ "እንድትሰረዝ" መደረጓ ተገልጿ።
በዚህም ኢትዮጵያ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ፣ ለደኅንነት እና ለሌሎችም የአገር ውስጥ የደኅነንት ኃይሎቿ የሚውሉ የመከላከያ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ከውጭ ገዝታ ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ አገራት መላክ እንድትችል የሚፈቅድ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር በኤርትራ የመከላከያ ኃይሎች እና በሌሎች አካላት ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል።
ኤርትራ ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ከነበራት ተሳትፎ ጋር በተያያዘ በ2014 ዓ.ም. በኤርትራ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ማዕቀቦች ጥላ ቆይታለች።
በዚህም የአሜሪካ መንግሥት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) እንዲሁም ከፓርቲው ጋር ትስስር ባላቸው ህድሪ ትረስት እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ላይ ማዕቀብ ጥሏል። በተጨማሪም በኤርትራ መከላከያ ኃይል እና በሁለት ከፍተኛ የኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ ዕቀባ ተጥሎ ነበር።
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት በኋላ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መስከረም 7/2014 ዓ.ም. ላይ በጦርነቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን በነበሩት ኃይሎች መሪዎች እና ተቋማት ላይ የተለያዩ ዕቀባዎች እንዲጣል የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አውጥተው ነበር።
ከእነዚህም መካከል ግንባር ፈጥረው የትግራይ ኃይሎችን ሲወጉ በነበሩት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እና ተቋማቶቸቻው ላይ ማዕቀቦት ተጥለው ለአምስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ነው እንዲነሳ መወሰኑ የተገለጻው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ አሜሪካ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እንደምትፈልግ ሲገለጽ የነበረ ሲሆን የተለያዩ ግንኙነቶች መደረጋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ማዕቀቡ መተነሳቱ የተገለጸው በትግራዩ ጦርነት ወቅት አጋር የነበሩት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት ተበላሽቶ ወደ ጦርነት ይገባሉ እየተባለ ባለበት ጊዜ ነው።















