የኤርትራ የፖለቲካ እስረኞች ይገኙበታል የሚባለው አደገኛው እና ምሥጢራዊው እስር ቤት

የዒራዒሮ እስር ቤት ክፍሎችን የሚሳይ የሳተላይት ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Satellite image ©2026 Vantor

የምስሉ መግለጫ, የዒራዒሮ እስር ቤት ክፍሎችን የሚሳይ የሳተላይት ምሥል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ዒራዒሮ በኤርትራ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲቋቋም እንዲሁም ሥልጣን በሕዝብ በሚመረጥ መንግሥት እንዲያዝ ጥያቄ ያቀረቡ የቀድሞ የነጻነት ታጋዮችን እንዲሁም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በርካታ ጋዜጠኞች የታጐሩበት ድብቅ እስርቤት ነው።

ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ከ10 ዓመተት በኋላ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ ለውጦችን እንዲያካሂዱ በይፋ ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ደጋፊዎቸቻው በቁጥጥር ስር አውለዋል ደብዛቸው ካጠፉ እነሆ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል።

እነዚህ ቡድን 15 (ጂ15) በመባል የሚታወቁት ባለሥልጣናት፣ በነጻነት ትግሉ እና ከዚያም በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲደረግ በግልጽ ባሠራጩት ደብደባ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ መስከረም 8/1994 ዓ.ም. ነበር ለእስር የተዳረጉት።

እስረኞቹ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ ክስ ሳይቀርብባቸው እና የት እንዳሉ ሳይታወቅ የቆዩ ሲሆን፣ በሕይወት ካሉ ዒራዒሮ በሚባለው አሰቃቂ እና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ይታመናል።

አደገኛ እና ምሥጢራዊ እስር ቤት

ዒራዒሮ/ኢላኢሮ በኤርትራ ቆላማ ስፍራ በሰሜን ቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚገኘው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት እስር ቤት ሲሆን፣ ለመኖር እጅግ አዳጋች በሆነ ስፍራ ላይ ይገኛል።

ኢራዒሮ ኤርትራ ነጻ አገር ሆና ከተመሠረተች በኋላ በአገሪቱ ካሉ እስር ቤቶች ዝርዝር ውስጥ ሰፍሮ ቢገኝም፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በአካባቢው 'አውሒተት' ማቆያ ተብሎ ይጠራ ነበር።

በአገሪቱ ውስጥ ውስጣዊ ቀውስ መባባስ የጀመረው ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ይገባኛል ምክንያት በተካሄደው ጦርነት አያያዝ እና አካሄድ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያቀረቡት ጥያቄ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው።

በዚህም ሳቢያ በኤርትራ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች ሽኩቻ ተፈጥሮ ነበር ሲሉ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ ዳን ኮኔል ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቀረቡት ዋና ዋና ጥያቄዎች ጊዜ ያለፈባቸው ብሔራዊ ምክር ቤት እና የአገሪቱ መሪ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ፣ በድንበር ጦርነት ምክንያት የዘገየው ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሕዝባዊ የሥልጣን ሽግግር እና ተጣያቂነትን እንዲሰፍን የሚሉ ይገኙባቸዋል።

ወቅቱ የኢትዮ- ኤርትራ የድንበር ጦርነት አልጀርስ ላይ በተደረሰው ስምምነት አብቅቶ፣ የተባበሩት መንግሥተት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አንሚ) ጣልቃ የገባበት ጊዜ ነበር።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጓዶቻቸው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች "ተሳስታችኋል" የሚል አጭር ምላሽ በመስጠት ውድቅ ማድረገው ካድሬዎቻቸው በባለሥልጣናቱ ላይ የክስ እና ስም የማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተው ነበር።

ሁኔታው እንተባባሰ በመሄዱ መስከረም 11/1994 ዓ.ም. ዓለም በአሜሪካ ላይ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት በተጠመደበት ወቅት፣ ከቡድኑ 11 አባላት እንዲሁም አስራ ሁለት ጋዜጠኞች እና ፀሐፊዎች ከቤታቸው፣ ከሥራ ቦታቸው እና ከመንገድ ላይ ተለቅመው በቁጥጥር ውለዋል።

የቡድን-15 አባላት መጀመሪያ ላይ እምባትካላ በሚባል እስር ቤት ታስረው የተበሩ ሲሆን፤ በወቅቱ በተገኘ መረጃ እና ሰነድ መሠረት ከወራት በኋላ ሰኔ ወር ላይ ወደ አደገኛው ዒራዒሮ እስር ቤት ተዘዋውረዋል።

የኤርትራ መንግሥት የአገሪቱን ነጻነት እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት እና ለሁለት ዓመት በተካሄደው የድንበር ጦርነት ወቅት "ክህደት ፈጽመዋል" በሚል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከስሷቸዋል።

በተጨማሪም ጋዜጠኞችን "የውጭ እርዳታ እያገኙ ብሔራዊ ደኅንነትን ለአደጋ የሚያጋልጡ የውሸት ወሬዎችን በማሠራጨት" ከስሷቸዋል።

ሆኖም ዛሬም ድረስ የኤርትራ መንግሥት በቡድን-15 አባላት እና በጋዜጠኞች ላይ ምንም ዓይነት ዝርዝር ክስ በይፋ አላቀረበም።

የሳተላይት ምሥል

ዒራዒሮ የት ነው የሚገኘው?

ዒራዒሮ በሰሜናዊ ቀይ ባህር ዞን፣ ሺአብ በሚባል ንዑስ ዞን ውስጥ በአንድ ቆላማ ቦታ ይገኛል።

በኤርትራ ውስጥ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠበቀው ከዚህ እስር ቤት እስካሁን የተፈታ እስረኛ እንደሌለ ይነገራል።

ቦታው በአስቸጋሪ ኮረብታዎች የተከበበ እና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የሌለበት ሲሆን፣ ጋህቴላይ ሸብ ከሚባለው ዋና መስመር በግምት 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ቦታው ከምሥራቅ በኩል የሚወርዱት ሁለት ዋነኛ ወንዞች የሚገናኙበት አማካይ ስፍራ ነው።

ዒራዒሮ በኤርትራ ነጻነት የትጥቅ ትግል ወቅት የመጀመሪያው የዳቦ መጋገሪያ ቦታ የተተከለት የነበረ ሲሆን፣ እንዲሁም በወቅቱ ጊዜያዊ እስር ቤት እና የኤርትራ ህዝባዊ ግንባር ለነፃነት ድረጅት ጽህፈት ቤትም እንደነበረ ይነገራል።

አካበቢው ከታኅሣሥ እስከ መጋቢት ዝናብ ያሚያገኝ ቢሆንም የሙቀት መጠኑ ከግንቦት አጋማሽ እስከ ነሐሴ መጨረሻ አስከ 45 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚደርስ፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በአካባቢው ይኖር የነበረው ጋዜጠኛ ብርሃነ ገብረትንሳኤ ዘግቧል።

ዒራዒሮ ምን ይመስላል?

ጥብቅ ቁጥጥር እና ጥበቃ የሚደረግለት፣ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙበት ዒራዒሮ እስር ቤት በሦስት የተለያዩ ግቢዎች ውስጥ 61 ክፍሎች አሉት።

በአቅራቢያው ካለው ከወንዝ በስተደቡብ 28 ክፍሎች፣ ከወንዙ በስተሰሜን ሁለት ግቢዎች፣ በአንዱ 18 ክፍሎች እና በሌላኛው 15 ክፍሎች እንዳሉት በአንድ ወቅት ከኤርትራ የሸሸው የእስር ቤቱ ጥበቃ አባል የነበረው ኢዮብ ባህታ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሮ ነበር።

የሳተላይት ምሥል እንደሚያሳየው ጣሪያው በሙሉ 3.5 ሜትር በ2.6 ሜትር ውጫዊ ልኬት እና በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ከአንድ ሰው ቁመት በላይ 2.6 ሜትር በ1.9 ሜትር ኮሪደር ይገኝበታል።

ኢዮብ በአስር ዓመት በፊት በሰጠው ቃለ ምልልስ ባለሥልጣናቱ እና ጋዜጠኞቹ እዚያ እንደነበሩ እና ለየብቻ በአንድ ክፍል ውስጥ እጆቻቸው ታስረው በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ፀሐይ እንዲሞቁ ይፈቅድላቸው እንደነበረ ተናግሯል።

ይህ እስር ቤቱ ጠባቂ የነበረው ግለሰብ ክፍሎቹ የእስረኞቹን ስም ሳይሆን ቁጥሮች (ኮድ) እንደተሰጣቸው እና እስረኞቹ በተለያዩ ጊዜያት ክፍሎች እንደሚቀይሩም ገልጿል።

እስካሁን ድረስ የኤርትራ መንግሥት በመስከረም 1994 ዓ.ም. ስለታሰሩት እና በሰኔ ወር ከእምባትካላ ወደ ዒራዒሮ ስለተዛወሩት ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም ጋዜጠኞች ስላሉበት ሁኔታ መረጃ አልሰጠም።

በተጨማሪም እነዚህ በኤርትራ ፖለቲካዊ ለውጥ በመጠየቅ ያለፍርድ የታሰሩት ሰዎች በሚገኙበት ዒራዒሮ እስር ቤት ውስጥ በሚገኙት 61 ክፍሎቹ ውስጥ ምን ያህል እስረኞች እንዳሉ፣ የሞቱ እና በሕይወት ያሉ እነማን እንደሆኑ በይፋ የሚታወቅ መረጃ የለም።

እስር ቤቱን ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኙ ሁለት አቧራማ መንገዶች አሉ። አካባቢው ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች እና ከመንግሥት ታጣቂዎች ውጪ ማንም እንዲንቀሳቀስበት የማይፈቀድበት እና በጥብቅ ክልከላ ስር ያለ መሆኑን የቀድሞው የእስር ቤቱ ጠባቂ ኢዮብ ባህታ ተናግሯል።

ዒራዒሮ እስር ቤት ለምን?

የቀድሞ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋዜጠኛ ብርሃኔ ገብረትንሳኤ-ማንጁስ "የሥርዓቱ ፈላጭ ቆራጭ ሰዎች እና የእስር ቤት ዋና አስተዳዳሪዎች ቦታውን የመረጡበት ምክንያት 'እነዚህ ሰዎች በሕይወት እያሉ ፍዳቸውን እንዲያዩ እና እንዲሰቃዩ' ለማድረግ በማለም ነው" ብሎ ያምናል።

ዒራዒሮ በእስር ላይ ለሚገኙት ቀድሞ ታጋዮች ምን ያህል አስቸጋሪ ቦታ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንደሚያውቁ የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ የመንግሥታቸውን ገመና አደባባይ አውጥተዋል፣ ሥልጣናቸውን ተቃውመዋል ያሏቸውን ጓዶቻቸውን "መከራ ሊያዩ ይገባል" በሚል ስሜት ለስቃይ ዳርገዋቸዋል ብሏል።

የቀድሞ ታጋይ ሞገስ ብርሃነ በበኩሉ "ጭካኔው እንዳለ ሆኖ እነዚህ ሰዎች ሲታሰሩ አንዳንድ ሰዎች በማንኛውም መንገድ በድብቅ ሊያስወጧቸው ስለሚችሉ በቅርብ ሊደርሱበት የማይችሉ ሩቅ ስፍራ፣ እጅግ ጥብቅ በሆነ እስር ቤት" እንዲታሰሩ ለመደረጋቸው ግምቱን አስቀምጧል።

በነጻነት ትግሉ ወቅት ዒራኢሮ ያለበትን አካባቢ በደንብ እንደሚያውቀው የሚናገረው ሞገስ ቦታው የተመረጠበትን ዓላማ "ያለው ሙቀት እና ቃጠሎ ለሰብአዊ ፍጡር ከባድ እና ለሚቋቋም አስቸጋሪ በመሆኑ፤ ሰዎቹ እዚያ ገብተው እንዲሰቃዩ እና እንዲሞቱ ማድረግ ነው" ብሏል።