በአበሽጌ ወረዳ በርካቶች የተገደሉበት እና የታገቱበት ጥቃት እንዴት እና በማን ተፈጸመ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ውስጥ ሰኞ ዕለት በተፈፀመ ጥቃት ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፣ በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን እና ሥራውን አጠናቆ ሪፖርት ገና አለማቅረቡን ገልፀዋል።
ጥቃት ፈፃሚዎቹ ራሳቸውን "ፋኖ" ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈፀሙት በወረዳው ዋልጋ ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ሰኞ መስከረም 4/2019 ዓ.ም. መሆኑን ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በበኩሉ በድርጅቱ እውቅና ያለው ታጣቂ ቡድን በአበሽጌ ወረዳ አካባቢ አለመኖሩን እና ለተፈፀመው ጥቃትም ድርጅቱ ኃላፊነት እንደማይወስድ ለቢቢሲ ገልጿል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን እነዚሁ ነዋሪዎች፣ በዕለቱ ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ተፈፀመ ባሉት ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ ታግተው የተወሰዱ ሰዎችም መኖራቸውን ገልፀዋል።
ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ፣ 15 ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ ያስረዳሉ። በከተማዋ "ልዩ ስሙ ወዶ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተገደሉ ቢያንስ 11 ሰዎች በሁለት ጉድጓድ ተቀብረዋል" ያለው ግለሰቡ "ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ 4 ሰዎች ተገድለዋል" በማለት በድምሩ 15 ሰዎች ስለመገደላቸው መረጃ እንዳላቸው አስረድተዋል።
ነዋሪው እንዳሉት፣ ከተገደሉት መካከል እንደቤተሰብ የሚያይዋቸው ሰዎች እና ጓደኞቻቸው ይገኙበታል። ሆኖም "ለቅሶ እንኳን መድረስ አልቻልኩም፤ ፈራሁ፤ ደግሞም ተፈናቅለዋል" ይላሉ።
ከተገደሉት በተጨማሪ 16 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውንም የገለፁት እኚሁ ምንጫችን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ "አራት ሴቶች ታግተዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ስለጥቃቱ ለቢበሲ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ 13 ሰዎች መሞታቸውን እንዳረጋገጡ ገልፀው፣ ነገር ግን "የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል" ብለዋል።
እርሳቸው ባላቸው መረጃ የታጋቾች ቁጥር ደግሞ 17 ነው።
ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ከታጣቂዎች ጋር ድርድር እያደረጉ እንደሚገኙ ሁለቱ ምንጮቻችን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ፣ በሰኞ ዕለቱ ጥቃት ስለደረሰው ጉዳት መንግሥት የተጣራ መረጃ እንዳልደረሰው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ስለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት "የሚያጣራ ቡድን አደራጅተን ልከናል" ያሉት ኃላፊው፣ የተገደሉ እና የታገቱ ሰዎች መኖራቸውን ግን አረጋግጠዋል።
አንደኛዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ስለጥቃቱ ሲያስረዱ፣ ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት ከአካባቢያቸው ለቅሶ ለመድረስ የሄዱ ሰዎች በስፍራው እንደነበሩ አንስተዋል።
"ከቀብር ተመልሰው ለማዕድ ተቀምጠው በነበሩበት አጋጣሚ አካባቢው ላይ ተኩስ ተከፈተ" ሲሉ ስለሁኔታው ያስረዳሉ።
ከዚያም ለቀስተኞች ተደናግጠው በመነሳት "ጫካ ለጫካ እየተሯሯጡ ረቡዕ ዕለት በሦስተኛ ቀናቸው ነው የተመለሱት" ሲሉ ሐሙስ መስከረም 7/2019 ዓ.ም. ያናገርናቸው ነዋሪ ተናግረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ፣ የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች በስጋት ቀያቸውን ለቀው መሸሻቸውንም ያናገርናቸው ግለሰቦች አብራርተዋል።
ምንም እንኳን ከሰኞው ጥቃት በኋላ የተፈፀመ ሌላ ጥቃት ባይኖርም፣ ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ታጣቂዎች "ዳግም ተመልሰው ያጠቁናል" በሚል ስጋት ነው።
"ነዋሪው እጅግ በጣም ንቅል ብሎ ነው የወጣው" የሚሉት አንደኛው ነዋሪ፣ አብዛኛው ተፈናቃይ የዞኑም የወረዳውም መቀመጫ ወደ ሆነችው ወልቂጤ ከተማ ማምራቱን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ደግሞ "መሰንበት ይሻላል ብሎ ሁሉም እየተፈናቀለ ነው። ለቀው እየሔዱ ነው" ብለዋል።
በስጋት ምክንያት ከዋልጋ ከተማ ከሚሸሹት ተፈናቃዮች መካከል አጎራባች ወደ ሆነው የምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሲሔዱ፣ ሌሎች ደግሞ "ወደ ወልቂጤ ነው የሔዱት" ሲሉም አክለዋል።
እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃቱ ወደተፈፀመበት አጎራባች አካባቢ ማቅናታቸውንም ተናግረዋል።
"እኛ ባለንበት ባንክም ሌሎች ተቋማትም አሉ። ለእሱ ሲል ቢያድኑን ነው እንጂ እኛም አቅም የለንም" በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ነዋሪዋ አክለውም "ብዙ ንፁኃን እየተገደሉ ነው፤ አገር እየጠፋ ነው፤ አገርን የሚያቆም መንግሥት ቢመጣልን ደስ ይለን ነበር። አገር ከሞተ ማን ይጠቀማል?" በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል። ከዚህ ቀደምም በወረዳው የብዙ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈፀማቸውንም አስታውሰዋል።
"ሥርዓት አልበኝነት በርትቷል" የሚሉት ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ፣ በኮማንድ ፖስት የሚመራው በዚሁ የአበሽጌ ወረዳ አካባቢ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መኖራቸውን አረጋግጠው፣ ሆኖም ታጣቂዎቹ "ከፀጥታ ኃይሉ አቅም በላይ ናቸው" ይላሉ።
የጥቃቱ ፈፃሚዎች ራሳቸውን "ፋኖ" ብለው እንደሚጠሩ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ሆኖም ዓላማቸው "ዘረፋ መፈፀም" እንደሆነ ነው የሚገልፁት።
በተለይ ጥቃቶች የበረቱት ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ እንደሆነ የገለፁት አንድ ምንጫችን፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ከሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በፊት የነበረውን ጥቃት ተከትሎ የተከሰተው መፈናቀል ለችግሩ ዋናው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ለዘረፋ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት፣ ከኖኖ ተፈናቅለው ወደ አበሽጌ ከገቡት መካከል የሆኑ ሰዎች ናቸው። "መሬታችንን ተቀምተን ውጡ ተባልን፤ ምን ሠርተን እንብላ የሚሉ ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት" ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሎቹ የመንግሥት አካላት እርስ በርስ እንዲሁም ከታጣቂዎቹ ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ካልቻሉ፣ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ተባብሰው ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ስጋት አላቸው።
ጥቃቱ አድራሾቹን "በአካባቢው ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሽፍታ ኃይል" ሲሉ የገለፁት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ተመስገን ካሳ፣ "የፀጥታ አካላት ያልተሰማሩበትን አሳቻ ቀጣናን ተጠቅሞ ድንገተኛ ጥቃት ማኅበረሰቡ ላይ ፈፅሞ ነው የወጣው" በማለት ከስሰዋል።
ታጣቂው ቡድን ራሱን "ፋኖ ነኝ" እንደሚል ገልፀው "እኛ ግን ፋኖ ብለን አልፈረጅንም" ብለዋል። ቡድኑ አማራ ክልል ካለው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው ስለመሆኑ "ተጨባጭ መረጃ የለንም" ሲሉም ተናግረዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በበኩሉ በአበሽጌው ጥቃት ላይ ተሳትፎ የለኝም ብሏል።
የአፋብን ቃል አቀባይ አስረስ ማረ ዳምጤ፣ የድርጅቱ እንቅስቃሴ "በአማራ ክልል ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ" ገልፀው፣ "አበሽጌ ወረዳ በንፁሃን ላይ ተፈፀመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ግን እንደ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ኃላፊነት አንወስድም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአበሽጌም ይሁን በሌላ አካባቢ "ራሳቸውን ለመከላከል የሚደራጁ በፋኖነት ራሳቸውን የሚጠሩ ወጣቶች እንዳሉ እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
ይሁን እንጂ፣ የአበሽጌውን "ጥቃት ፈፀሙት ተብሎ ክስ እየቀረበባቸው ያሉ ሰዎች በድርጅታችን 'ቼይን ኦፍ ኮማንድ' [የዕዝ ሰንሰለት] ስር የምናውቃቸው አይደሉም" በማለት አፋብን እውቅና የሰጠው ታጣቂ ቡድን በስፍራው አለመኖሩን አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ተመስገን፣ ታጣቂዎቹ በደርግ ዘመነ-መንግሥት በሰፈራ ከሔዱ የእዚያው አካባቢ ነዋሪዎች የተውጣጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
"ዘረፋ እና እገታ በመፈፀም በጉልበት ገንዘብ የማግኘት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል" ያሏቸው ታጣቂዎቹ፣ ለመንግሥት መረጃ ይሰጣሉ የሚሏቸውን ሰዎችን እየመረጡ ግድያ እና ሌሎች ጥቃቶችን እንደሚፈፅሙ ነው ያብራሩት።
መሰል ጥቃቶች ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲፈፀሙ እንደቆዩ እና መንግሥት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉንም አስረድተዋል። በዚህም ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በትጥቅ እንቅስቃሴያቸው በቀጠሉት ላይ ግን መንግሥት እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የሰኞውን ጥቃት ተከትሎም "ተመጣጣኝ የሆነ የሕግ እርምጃ ለመውሰድ የፀጥታ ኃይሎች በቀጣናው ላይ በተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው" ብለዋል።
ታጣቂዎች ጥቃት የፈፀሙበት የአበሽጌ ወረዳ፣ በቅርቡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሦስት ወጣቶችን ከመኪና አውርደው ከፍርድ ውጪ የገደሉበት ስፍራ ነው። ይህ ግድያ መፈፀሙን ቢቢሲ በወቅቱ ከአካባቢው ምንጮች አረጋግጧል።
የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ግድያውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ እርምጃ የተወሰደው "የመንግሥት የሰላም አማራጭን አንቀበልም ባሉ ሽፍቶች ላይ ነው" ብለው ነበር።
ሆኖም ቢቢሲ በወቅቱ እርሳቸውን ጨምሮ ከአካባቢው የመንግሥት አካላት አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።















