አሜሪካ እና ዴንማርክ ትራምፕ እጠቀልላታለሁ ባሏት ግሪንላንድ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እና ዴንማርክ በግሪንላንድ የደኅንነት ጉዳይ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን አስታወቁ። ስምምነቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ግዛቷን በኃይል እንደሚጠቀልሏት ከዛቱ በኋላ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ የሚፈታ ነው ተብሏል።
ትራምፕ ስምምነቱ አሜሪካ የደኅንነት እና ሌሎች ፍላጎቶቿን በዘላቂነት እንድታስጠብቅ ያስችላል ብለዋል።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ስለጠቀሱት የስምምነቱ ዝርዝር ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ስምምነቱ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ ባሕር ያለውን ደኅንነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
አገራቱ ስምምነቱ ላይ የደረሱት ትራምፕ ለመከላከያ ዓላማ እና ለማዕድናት ሃብት ስትራቴጂያዊ ቦታ እንደሆነች በመጥቀስ በብሔራዊ ስጋት ምክንያት ግሪንላንድን እንደሚጠቀልሉ ሲዝቱ ከቆዩ ከወራት በኋላ ነው።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ስምምነት ላይ የተደረሰው "አሜሪካ ምንም ዓይነት ዋጋ ሳትከፍል እንደሆነ" ገልጸው፣ የግሪንላንድን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ከጥቃት ለመከላከል አሜሪካ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ እንድታደርግ ያስችላታል ብለዋል።
ይህም "ማንኛውም የአሜሪካ ጠላት በግሪንላንድ ወታደራዊ ስምሪት ማድረግ ወይም ያለ እኛ ግልጽ ፈቃድ በግሪንላንድ ኢንቨስት ማድረግ አይችልም የሚል ሕግን እንደሚያካትት" ትራምፕ አክለዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስምምነቱን " ታሪካዊ" እና "ለአሜሪካ እና ሕዝቦቿ ትልቅ ድል" ብለውታል።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚት ፍሬደሪክሰን ስምምነቱን በሚቀጥለው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በፊርማቸው እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስምምነቱ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ አካባቢ ያለውን የጋራ ደኅንነት ያጠናክራል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቷን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም የግሪንላንድ ሕዝቦችን በራስ እድል በራስ የመወሰን መብትን ያከበረ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም ስምምነቱ በሕግ አውጪዎች መጽደቅ እንደሚኖርበት ገልጸው፣ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ በሆኑ የፓርላማ ሒደቶች እንደሚያልፍ ጠቅሰዋል።
የግሪንላንድ አስተዳደር መሪ ጂንስ ፍሬደሪክ ኒልሰንም ስምምነቱን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ "የግሪንላንድን፣ የዴንማርክን እና የአሜሪካን ደኅንነት የሚያረጋግጥ እና የሚያጠናክር ስምምነት ላይ መደረስ መቻሉ የሚያስደስት ነው" ብለዋል።
"ስምምነቱ ለግሪንላንድ ፍላጎቶች እና በዓለም አቀፍ ትብብር ውስጥ ቦታ እንዳለን እውቅና የሰጠ ነው፤ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ ለሌሎች ጠላቶች የተጋለጠች ናት በማለት በማዕድን የበለፀገችውን በዴንማርክ ሥር የምትተዳደረውን ግዛት በገንዘብ ለመግዛት ወይም በኃይል ወደ አሜሪካ ለመጠቅለል ለወራት ሲዝቱ ቆይተዋል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ በግሪንላንድ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያስፈራሩም የቆዩ ሲሆን ይህም ከዴንማርክ እና ከሌሎች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ቁጣን አስከትሏል።
አሁን ላይ የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ይፋ አልተደረገም። ቢቢሲ የዴንማርክ ኤምባሲን እና ዋይት ሃውስን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
ሆኖም ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተዋል።
እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው ግሪንላንድ ወደፊት ራሷን የቻለች አገር ብትሆንም ስምምነቱ በጊዜ የተገደበ እንዳልሆነ ይገልጻል።
ከዚህም በተጨማሪ ለአሜሪካ ያለ ግሪንላንድ እና ዴንማርክ ፈቃድ ተጨማሪ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል የተናጠል ሥልጣን ይሰጣል። ይህም "በፈለገች ጊዜ ወደ ግዛቷ መግባትን፣ የጦር ሠፈር መመስረትን እና የበረራ መብቶችን" ያካትታል።
ስምምነቱ በ1951 ከዴንማርክ ጋር ከተደረሰው እና አሜሪካ እንደፈለገች ወደ ግሪንላንድ ወታደሮችን መላክ ከሚያስችላት ስምምነት የሚለየው በምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
አሜሪካ በግዛቷ ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ በሚገኘው ፒቱፊክ የጦር ሠፈር በቋሚነት የሰፈሩ ከ100 በላይ ወታደሮችን አሏት።
ትራምፕ አሜሪካን ከሩሲያ እና ቻይና ከሚፈፀሙ የሚሳኤል ጥቃቶች ለመጠበቅ ያለመ የጎልደን ዶም መከላከያ ሥርዓት ለመገንባት ለያዙት እቅድ ግሪንላንድ ወሳኝ መሆኗን ተናግረዋል።
ደሴቷ በጣም በዙ እና ያልተነካ ብርቅዬ ማዕድናት ያላት ሲሆን አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና የኤሌክትሪክ መኪናን ጨምሮ ለቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ወሳኝ ናቸው።















