ጉግል የሠራው ጄሚኒ ኤአይ ሦስት ኩባንያዎች ላይ የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

ጉግል የሠራው ጄሚኒ ኤአይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጉግል የሠራው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴል የሆነው ጄሚኒ የሦስት ኩባንያዎችን የበይነ መረብ ደኅንነት ከለላ ጥሶ ማለፉ ተገለጸ።

ጄሚኒ የበይነ መረብ ደኅንነት ክህሎቱ ላይ ፍተሻ እየተደረገበት ሳለ በራሱ ተነሳሽነት ኩባንያዎቹን 'ሀክ' ማድረጉን ወይም መጥለፉን ጉግል አስታውቋል።

የበይነ መረብ ጥቃቱን የፈጸመው ትዕዛዝ ሳይሰጠው በራሱ ፈቃድ ሲሆን፤ እንዲህ ያለ ክስተት የመጀመሪያው እንደሆነም ተገልጿል።

ጉግል ለቢቢሲ እንደገለጸው ጄሚኒ "በበይነ መረብ ላይ ለሕዝብ ይፋ የሆነ መረጃን በመጠቀም የይለፍ ቃሎችን ገምቶ ከደረሰባቸው በኋላ" ወደ ድረ ገጾቹ ገብቷል።

ጄምኒ ላይ የበይነ መረብ ደኅንነት ሙከራ እየተደረገበት ሳለ ድርጊቱን እንደፈጸመ ተገልጿል። ድረ ገጾቹ የሙከራው አካል እንደሆኑ አስቦ ሰርጎ መግባቱንም የጉግል ኃላፊ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የኤአይ ሞዴሉ ወደ ድረ ገጾቹ ከገባ በኋላ "መቆሙን" ኃላፊው አክለዋል።

መረጃውን የበይነ መረብ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ኩባንያዎች ማሳወቁን ጉግል ገልጿል።

ባለፉት ሳምንታት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች ተጠናክረዋል። ኤአይ እየሄደበት ያለው ፍጥነት እንዲገታ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችም እየጠየቁ ይገኛሉ።

ኤአይ ለሰው ልጆች ኅልውና አስጊ ነው የሚለው ዜና መውጣቱን ተከትሎ በዘርፉ ቁጥጥር መደረግ አለበት የሚለው ጫና በርትቷል።

የኤአይ ሞዴሉ የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸሙን መጀመሪያ ላይ የዘገበው ዋል ስትሪት ጆርናል ነው።

ግንቦት ላይ አንድ ገለልተኛ ተቋም የበይነ መረብ ፍተሻ እያደረገ ሳለ ጥቃቱ መድረሱን ዘገባው ያሳያል።

የጉግል የደኅንነት ክፍል ምክትል ፕሬዝዳንት ሄዘር አድኪንስ ለቢቢሲ "ለሦስቱ ኩባንያዎች መረጃ ሰጥተናል" ብለዋል።

ክስተቱ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥልጠና ሲሰጥ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያሳየ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ያለፈው ሐምሌ ላይ የአንትሮፒክ የኤአይ ሞዴል ክላውድ በሙከራ ላይ ሳለ ለሕዝብ ይፋ የሆነ መረጃን በመጠቀም አንድ ኩባንያ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።