ትራምፕ ያገዷቸው የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሐውስ መግባት ተከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚዲያ ተቋማቱን ከዋይት ሐውስ ማገዳቸውን ካሳወቁ በኋላ፣ የፖሊቲኮ፣ ሲኤንኤን እና ኤምኤስ ናው ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
የኤምኤስ ናው ዘጋቢ እና ፎቶግራፍ አንሺ ቅዳሜ ጠዋት ወደ ዋይት ሐውስ ግቢ ለመግባት ሲሞክሩ፣ የመግቢያ ካርዳቸው እንዳልሰራላቸው እና አንድ የጥበቃ ኃላፊ ካርዳቸውን እንደወሰደባቸው ተቋሙ ዘግቧል።
ሲኤንኤን እና ፖሊቲኮም እንዲሁ ቅዳሜ ጠዋት ዘጋቢዎቻቸው ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር እና የመግቢያ ካርዶቻቸውም እንደተወሰዱ ገልጸዋል።
ትራምፕ፣ ስለ መንግሥታቸው "ልብ ወለድ ወይም ውሸት" ይጽፋሉ ብለው የከሰሷቸውን እነዚህን ሦስት ዋና ዋና የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ከዋይት ሐውስ እንደሚያግዱ ዓርብ ዕለት ገልፀዋል።
የኤምኤስ ናው ዘጋቢ አካይላ ጋርድነር "የጥበቃ ኃላፊው የመግቢያ መታወቂያ ካርዴን እንድሰጠው ጠየቀኝ። ካርዱ እንዳይሰራ ተደርጓል አለኝ" ብላለች። ለምን ወደ ውስጥ መግባት እንዳልቻለች ስትጠይቀው፣ "ይህ ከእኔ በላይ የሆነ ውሳኔ ነው" የሚል ምላሽ እንደሰጣት ተናግራለች።
ጋርድነር በተጨማሪም የራሷና የባልደረባዋ ካርድ እንዳይሰራ ቢደረግም፣ የተቋሙ ባልደረባ የሆነች ፕሮዲዩሰር ግን ካርዷን በመጠቀም መግባት እንደቻለች ገልፃለች። ሆኖም የእርሷ ካርድ ለምን እንደሠራ ምንም ማብራሪያ አልተሰጣትም ብላለች።
የሲኤንኤን ዘጋቢ ቤትሲ ክላይንም አንድ የምስጢራዊ አገልግሎት (ሴክሬት ሰርቪስ) ወኪል የመግቢያ መታወቂያ ካርዷ እንደተሰረዘ እንደነገራት ገልፃለች።
የፖሊቲኮ ጋዜጠኛዋ ቼየን ሃስሌትም እንዲሁ ወደ ስፍራው እንዳትገባ መከልከሏን እና የአሜሪካው ምስጢራዊ የጥበቃ አገልግሎት ፈቃዷን መሰረዙን ተቋሙ ዘግቧል።
ሦስቱም የዜና ተቋማት፣ ትራምፕ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት የተጠበቁትን ንግግር እና የፕሬስ ነጻነት መብቶቻቸውን እየጣሱ ነው በማለት በውሳኔው ላይ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
የኤምኤስ ናው ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ "ዋይት ሀውስ የአሜሪካ ሕዝብ ንብረት ነው፣ በውስጡ የሚደረጉ ውሳኔዎችም በእኛ የግብር ገንዘብ የሚደገፉ ናቸው" ብለዋል።
በተጨማሪም "በሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያ ማሻሻያ የተጠበቁ መብቶቻችንን እና የዴሞክራሲያችን አካል የሆነውን የነጻና ገለልተኛ ጋዜጠኝነት ወሳኝ ሚና ለመከላከል የሚያስፈልጉ ሁሉንም እርምጃዎች እንወስዳለን" ብለዋል።
የፖሊቲኮ ዋና አዘጋጅ ጆናታን ግሪንበርገር ለውስጥ ሠራተኞች በላኩት ኢሜይል፣ ድርጅታቸው ከጋዜጠኞቹ ጎን እንደሚቆም እና የሕገ መንግሥቱን የመጀመሪያ ማሻሻያ መብቶቻቸውን "በብርቱ እንደሚከላከል" ገልፀዋል።
ሲኤንኤን በበኩሉ "ዘገባችንን ያለ መንግሥት ክልከላ ወይም ጣልቃ ገብነት የመስራት መብት በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ተጠብቆልናል፤ ይህ ክልከላ በዚህ መሠረታዊ መብት ላይ የተፈጸመ ሕገ-ወጥ ጥቃት ነው" ብሏል።
ትራምፕ በሦስቱ የብዙኃን መገናኛዎች ላይ የክልከላ እርምጃ ያስከተሉ ዘገባዎች የትኞቹ እንደሆኑ ውሳኔውን ሲያሳልፉ አልጠቀሱም። ሆኖም እርምጃው "ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከማቹ ዘገባዎች ድምር ውጤት ነው" ሲሉ ዘግይተው አሳውቀዋል።
ትራምፕ አክለውም "ከእነሱ ጋር ሊቀላቀሉ የሚችሉ ሌሎችም ይኖራሉ" ያሉ ሲሆን ነገር ግን ተጨማሪ የዜና ተቋማትን ለማገድ ግልጽ መመሪያ አልሰጡም።
የታገዱትን የሚቀላቀሉ "ሌሎችም ይኖራሉ" ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ በአንድ ጋዜጠኛ የተጠየቁት ትራምፕ "ከሐሰተኛ ዜና አንጻር የሚቀላቀሏቸው ሌሎች? እናንተ ታውቃላችሁ፤ ኒው ዮርክ ታይምስ ሐሰተኛ ዜና ነው፣ ዋሽንግተን ፖስትም ሐሰተኛ ዜና ነው" ሲሲሉ መልሰዋል።
የዋይት ሀውስ ዘጋቢዎች ማኅበር፣ የትራምፕ አስተዳደር የጋዜጠኞቹን የመግቢያ ፈቃድ "በአስቸኳይ እንዲመልስ" ጠይቋል። እርምጃው በአሜሪካ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ ማሻሻያ የተጠበቁ መብቶችን የሚጥስ መሆኑንም ማኅበሩ አስታውቋል።
የፕሬስ ነጻነትን ለመከላከል የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችም የትራምፕ አስተዳደር የጣለውን ክልከላ ሕገ-ወጥና ሕገ መንግስቱን የሚቃረን ነው ሲሉ ተችተዋል።
ይህ እርምጃ ትራምፕ ይተቹኛል በሚሏቸው የመገናኛ ብዙኃን ላይ ከወሰዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች ውስጥ የቅርብ ጊዜው ነው። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል በአሜሪካ እና በዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ላይ የተጀመሩ የሕግ ክሶችም የሚገኙ ሲሆን፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እና ቢቢሲ ከተከሰሱት መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ከእነዚህ ክሶች አንዳንዶቹ፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱ በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ክፍያ እንዲፈፅሙ በሚያስገድዱ ስምምነቶች ተቋጭተዋል።
ትራምፕ በቢቢሲ ላይ ያቀረቡት ክስ ግን አሁንም በሂደት ላይ ይገኛል።












