በፕሬዚዳንት ትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ አቅራቢያ መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

A sign for Trump's golf course overlooks a bluff in California

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሎስ አንጀለስ የሚገኘው እና በዶናልድ ትራምፕ ባለቤትነት የተያዘው የጎልፍ መጫወቻ አቅራቢያ ፕሬዚዳንቱ ለገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ከመገኘታቸው በፊት መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የካሊፎርኒያ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የ38 ዓመቱ ጂኒን ጆን ታሌ፣ በራንቾ ፓሎስ ቨርዴስ በሚገኘው የትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ አካባቢ ሽጉጥና ሕገ ወጥ ጥይት ይዞ መገኘቷን መርማሪዎች ተናግረዋል።

እንደ ሎስ አንጀለስ ፖሊስ ዘገባ ከሆነ ግለሰቡ "በጎልፍ ሜዳው ውስጥ ፎቶግራፍና ቪዲዮ ሲያነሳና የደህንነት እንቅስቃሴዎችን ሲከታተል ታይቷል"።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው እሁድ ከሰዓት በኋላ ነው። ትራምፕ ማክሰኞ በሚካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ የገንዘብ ማሰባሰቢያ እራት ላይ ለመገኘት ካሊፎርኒያን እየጎበኙ ነው።

ታሌ የጦር መሳሪያ ደብቆ በመያዝ እና የተከለከለ ጥይት ይዞ በመገኘት ክስ ተመስርቶበት ታስሯል።

ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ታሌ በቁጥጥር ስር የዋለው ሲቪል የለበሱ የደህንነት አባላት በቀኑ አጋማሽ ላይ አጠራጣሪ ሰው መመልከታቸውን ለአካባቢው ባለሥልጣናት ካሳወቁ በኋላ መሆኑን ተናግሯል።

ፖሊስ ሰውየውን በቁጥጥር ስር አውሎ ማንነቱን ሲያጣራ ከራንቾ ፓሎስ ቨርዴስ በስተሰሜን 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የኤል ሴጉንዶ በተፈጸመ የዝርፊያ ተግባር እየተፈለገ መሆኑን መረዳት ችለዋል።

ባለሥልጣናት ፍተሻ ሲያካሄዱ ጥይቶችን መያዙን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በጎልፍ መጫወቻው አካባቢ በቆመው ተሽከርካሪው ውስጥ የተቀባበለ ሽጉጥ እና ተጨማሪ ጥይቶችን አግኝተዋል።

በአሜሪካ ውስጥ በጣም ጥብቅ የሆኑ የጦር መሣሪያ ሕጎች ካሏቸው ግዛቶች መካከል አንዷ ካሊፎርኒያ ናት።

በሎስ አንጀለስ አካባቢ በምትገኘው ዳውኒ ከተማ የሚገኘው የተጠርጣሪው ቤት ሰኞ ዕለት በኤፍቢአይ አባላት እና በሎስ አንጀለስ ካውንቲ የፖሊስ ባልደረቦች ተፈትሿል።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ብርበራው የተካሄደው "በጉዳዩ ዙሪያ ባለው የደህንነት ስጋት ምክንያት" መሆኑን አስታውቋል።

በቤቱ ውስጥ "ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የተሰራ ጠመንጃ" ሰውነትን ከጥይት መከላከያ፣ በርካታ የሽጉጦችና የጠመንጃ ጥይቶች እና "አሳሳቢ መልዕክቶችን የያዙ" በርካታ ማስታወሻ ደብተሮችን አግኝተዋል።

ምርመራው ከአሜሪካ የደህንነት ቢሮ ጋር በመሆን መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣናት ግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ክሶች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ፖሊስ "በማኅበረሰባችን ላይ ምንም ዓይነት ተዓማኒነት ያለው ስጋት" አለማግኘቱን ጨምሮ ገልጿል።

"ይሁን እንጂ፣ ይህ ጉዳይ ሁኔታዎችን ንቁ ሆኖ መከታተል አስፈላጊ መሆኑን፣ ከአካባቢው፣ ከክልሉ እና ከፌዴራል የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ እና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን በመለየት እና በመመርመር ቅድመ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል" ብሏል።

ትራንፕን የጫነች የዋይት ሐውስ ሂሊኮፕተር በካሊፎርኒያ የጎልፍ ሜዳ ላይ ስታርፍ ታይታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራንፕን የጫነች የዋይት ሐውስ ሂሊኮፕተር በካሊፎርኒያ የጎልፍ ሜዳ ላይ ስታርፍ ታይታለች

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ፕሬዝዳንቱ ካሊፎርኒያን በሚጎበኙበት ወቅት ነው። ዶናልድ ትራምፕ በጎልፍ መጫወቻ ስፍራ በሪፐብሊካኖች የገንዘብ ማሰባሰቢያ እራት ላይ ለመገኘት አቅደዋል።

እንደ ዋይት ሐውስ መረጃ ከሆነ ትራምፕ በ2028 ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እያቀዱ እንደሆነ በሰፊው የሚነገረውን የካሊፎርኒያ ገዥ ጋቪን ኒውሶምን የሚተች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ረቡዕ ዕለት ትራምፕ በአንድ የቁማር መጫወቻ ስፍራ ንግግር ለማድረግ ወደ ላስ ቬጋስ ይጓዛሉ።

ትራምፕ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከሦስት የግድያ ሙከራዎች አምልጠዋል።

ባለሥልጣናት ራንቾ ፓሎስ ቨርዴስ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ትራምፕን ለመጉዳት ስለማሰቡ እስካሁን አልገለጹም።

በተጨማሪም ከዚህ ዓይነት ክሶች ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም።