በትግራይ ያገረሸው ግጭት ነዋሪዎችን "ዳግም ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጋልጧል" ሲል አምነስቲ አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በትግራይ ክልል ግጭት ማገርሸቱ ነዋሪዎችን "እንደ አዲስ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጋልጧል" ሲል አስጠነቀቀ።
የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እንደ የንጹኃንን ደኅነንት ማስጠበቅ ላሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች እንዲገዙም ጠይቋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ይህንን ያለው በሳምንቱ መጨረሻ የተከሰውን ግጭት በተመለከተ ትናንት ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች "ሸረሪና" በተባለ የሱዳን አዋሳኝ ሥፍራ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ከተለያዩ ምንጮች የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
እሁድ ዕለትም ቀጥሎ የነበረው ይህ ግጭት "በከባድ መሣሪያ እና ድሮን" የታገዘ እንደነበር አንድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምንጭ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል። የዓይን እማኞችም ቅዳሜ ዕለት ፍንዳታዎችን፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ እና የአውሮፕላኖችን ድምጽ ሲሰሙ እንደነበር ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ሥልጣን የተቆጣጠረው እና በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ ፌደራል መንግሥት "ግልፅ ጦርነት ከፍቷል" ሲል ከስሷል።
ፌደራል መንግሥት እስካሁን ስለክስተቱ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።
ቢቢሲ ከመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም ከመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እንዲሁም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ሥፍራ ግጭት መነሳቱን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች "ጦርነት እንደከፈቱ" ከስሰው፤ "ይህ ጦርነት ከወዲሁ ካልቆመ. . .የከፋ ጉዳት ይከተላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ከዚህ ክስተት በኋላ ትናንት ምሽት መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ክልሉ ዳግም ወደ ግጭት መግባቱ የፈጠረውን ስጋት ገልጿል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "በትግራይ በድጋሚ ግጭት መጀመሩ ነዋሪዎችን እንደ አዲስ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያጋልጣቸዋል" ብለዋል። ማኅበረሰቦች ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙ ጥሰቶች "ፍትሕ እና ተጠያቂነት" አለማግኘታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
አሁን ውጊያ ያገረሸው "በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የትጥቅ ግጭቶች" በቀጠሉበት ሁኔታ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ "ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት የምርመራ መንገዶችን መዘርጋት" እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ "ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን መመዝገብ መቀጠሉን" አንስተዋል።
በትግራይ ጦርነት ወቅትም "የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን" መሰነዳቸውን አስታውሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ "ኢትዮጵያ ተአማኒነት ያላቸው ምርመራዎች እና ጥፋት ፈጻሚዎች ላይ የሚካሄዱ የክስ ሂደቶች አለመኖርን በጭራሽ እንደ መደበኛ ነገር መውሰድ የለባትም" እንዳሉ መግለጫው ያስረዳል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ "የፌደራል እና የትግራይ ባለሥልጣናት የንጹኃን ጥበቃን ጨምሮ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ደረጃዎችን እንዲያከብሩ እና [ለእነርሱ] እንዲገዙ" ጥሪ አቅርቧል።
ባለሥልጣናቱ፤ ለገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ተከታታዮች እና የሰብዓዊ ድጋፍ ተዋናዮች በእነዚህ አካባቢዎች "ያልተገደበ እንቅስቃሴ" እንዲፈቀድላቸውም ጠይቋል።
በፌደራል እና ትግራይ ኃይሎች ግጭት ውስጥ መግባታቸው የተሰማው፣ ለወራት ውጥረቱ ሲባባስ ከቆየ በኋላ ነው። በዚህ ግጭት ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን በግልጽ አልታወቀም።
ክስተቱን ተከትሎ ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሊያን እና የተጎዱ ተዋጊዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን መሸሻቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።














