አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት እያደረገች ነው መባሉን አስተባበለች

 ማሳድ ቡሎስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ አንድ የአፍሪካ ቀንድ አገርን በተመለከተ ከኤርትራ ጋር ድርድር እያደረገች ወይም ምሥጢራዊ ስምምነት ለመድረስ እየሞከረች ነው መባሉን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ አስተባበሉ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሐፍ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር በመሆን በየትኛውም የቀጣናው አገር ላይ እንደማታሴር ገልጸዋል።

አማካሪው እንዳሉት አሜሪካ "ከአንድ የቀጣናው አገር በተቃራኒ ከኤርትራ ጋር ድርድር እያደረገች ነው ወይም ምሥጢራዊ ስምምነት ለመድረስ እያሳበች ነው መባሉ ፍጹም ሐሰት ነው" በማለት አስፍረዋል።

ማሳድ ቡሎስ በኤክስ ጽሑፋቸው ላይ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረገች መሆኑን በተመለከተ ሃሳቡ ከማን እንደተሰነዘረ እና የቀጣናው አገር የተባለው ማን እንደሆነ በስም አልጠቀሱም።

ጨምረውም እንዲህ ያለ ስምምነት አለመኖሩን እና ይህንንም በተመለከተ ንግግር እየተደረገ አለመሆኑን ገልጸው፤ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ዓላማ "በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው" ብለዋል።

ጨምረውም ስምምነቶችን ወይም ሌሎች ክስተቶችን በተመለከተ የሚቀርቡ ሐሰተኛ እና አሳሳች መግለጫዎች፣ ስምን የሚያጠፉ ግምቶች እና መሠረት የሌላቸው ክሶች "በቅን ልቦና የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በማዛባት ዘላቂ ሰላማን የማስፈን ተስፋን አደጋ ላይ ይጥላሉ" በማለት ወቅሰዋል።

መንግሥታቸው ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መከተሉን እንደሚቀጥል የጠቀሱት ቡሎስ፤ የአገራቸው ዋነኛ ትኩረት የቀጣናው ዘላቂ ሰላም መሆኑን አመለክተዋል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ እንዲህ ያለውን ማስተባበያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲጽፉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ከሁለት ሳምንት በፊት ካይሮ ውስጥ ከኢትዮጵያ አንጻር የጋራ ትብብር ከመሠረቱት ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ውይይታቸው ፀረ ኢትዮጵያ ዓላማ እንዳልነበረው አሳውቀው ነበር።

አሁንም ባለሥልጣኑ አይጥቀሱት እንጂ አሜሪካ ከቀጣና አገራት አንዷን በተመለከተ ከኤርትራ ጋር ንግግር ወይም ምሥጢራዊ ግንኙነት እያደረገች ነው ሊባል የሚችለው ግንኙነታቸው ተበላሽቶ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል ከተባለው ከኢትዮጵያ አንጻር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪው ማሳድ ቡሎስ ካይሮ ውስጥ ውይይት ካደረጉ በኋላ ባለፈው ሳምንት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ከአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ንግግር "ተገቢ ያልሆነ ገጽታ ተሰጥቶት" ተዘግቧል ሲሉ ተቃውመውታል።

ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ እንዲሁም ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ ጋር ካይሮ ውስጥ በተናጠል የተገናኙት ከፍተኛ አማካሪው፤ ስለ አፍሪካ ቀንድ "ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት" መነጋገራቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር።

በዚያው ወቅት የግብፅ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ ላይ ከተገናኙ በኋላ የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" እንደሆነ በመግለጽ ኢትዮጵያ ካነሳችው የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ አንጻር አቋማቸውን አሳውቀው ነበር።

ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት የምትወዛገበው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ስጋት የፈጠረባት ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከደረሰች በኋላ ውዝግብ ውስጥ ገብታ የነበረችው ሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ ትብብር ፈጥረው እንደነበረ ይታወሳል።

የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ ላይ መገናኛኘታቸውን ተከትሎ የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ማሳድ ቡሎስ፤ ከሚኒስትሮቹ ጋር መገናኘታቸውን በመጥቀስ ውይይቱ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የተደረገ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች ተሰምተዋል።

ነገር ግን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ በኤክስ ገቸጻው ላይ በሰጡት ምላሽ ዘገባዎቹን "ሐሰተኛ እና አሳሳች" በማለት የአሜሪካን ዲፕሎማሲ "ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ" አቅርበዋል ብለዋል።

ዘገባዎቹ "አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ 'ፀረ ኢትዮጵያ ትብብርን' ለመደገፍ ሙከራ እንደምታደርግ" ተደርጎ መቅረባቸው የተዛባ መሆኑን በመግለጽ ይህም "ትክክል ያልሆነ እና አላስፈላጊ ማጋጋል" ነው በማለት ወቅሰዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪው ጨምረውም አገራቸው "ከኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በቀይ ባሕር ቀጣና ከሚገኙ ሁሉም አገራት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ" እንደምትሠራ ገልጸዋል።

በዚህም ከአንድ የቀጣናው አጋር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከሌላው አገር ጋር መቃረን ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት ማሳድ ቡሎስ "የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ተቀናቃኝ ቡድኖችን መፍጠር ወይም ልዩነቶችን ማስፋት ሳይሆን ግጭቶችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር በገንቢ ሁኔታ መሥራት ነው" ብለዋል።

የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ቡሎስ ከግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ከተገናኙ በኋላ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከባለሥልጣናቱ ጋር ያደረጉትን ውይይት "ፍሬያማ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ይፋ መሆንን ተከትሎ ሁለቱ አገራት፤ ቀይ ባሕር ከዳርቻው አገራት "ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር" እንዳለው በመጥቀስ "የቀይ ባሕር አጎራባች ያልሆነ አካል ቀይ ባሕርን በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባት የለበትም" ማለታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋ መግለጹ ይታወቃል።

ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ ትብብር አሥመራ ላይ የመሠረቱ ሲሆን፣ በወቅቱ ግብፅ ኢትዮጵያ በገነባቸው የሕዳሴ ግድብ፣ ኤርትራ ኢትዮጵያ ባነሳችው የባሕር በር ጥያቄ እንዲሁም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት ተቃቅረው ነበር።