በሰሜን ሸዋ ዞን በምትገኘው ጻድቃኔ ማርያም ገዳም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት 14 ሰዎች ሞቱ

በአደጋው 14 ሰዎች ሞተዋል

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የምስሉ መግለጫ, በአደጋው 14 ሰዎች ሞተዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በሞጃ እና ወደራ ወረዳ በምትገኘው የጻድቃኔ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም ውስጥ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ 14 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በተከሰተው አደጋ ምክንያት አምስት ሰዎች ከባድ እና ሁለት ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደገጠማቸውም የሞጃ እና ወደራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው አዝብጤ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌሊቱን የክረምት ዝናብ ሲወርድ እንዳደረ እና ይህም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ. ም. ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ "የዋሻ ናዳ" ማስከተሉን የአካባቢው ባለሥልጣን ገልጸዋል።

የመሬት መንሸራተቱ በተከሰተበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያኑ ዋሻው በር ላይ ፀሎት ሲደረጉ የነበሩ ምዕመናን ላይ ጉዳቱ መድረሱንም አስረድተዋል።

አምስት ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ደብረአብ ሪፈራል ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና ሁለት ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው በሰላ ድንጋይ ጤና ጣቢያ እየታከሙ እንደሚገኙ አቶ ዳኛቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ "ሌላ ክስትተ ይኖራል ተብሎ" እንደማይታሰብ እና ከዚህ ቀደምም እንዲህ ያለ አደጋ በስፍራው አጋጥሞ እንደማያውቅ አክለዋል።

ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል "አሁን አካባቢውን ከልለናል። ስጋት ሊኖር ስለሚችል ግን ምዕመናል በአካባቢው የሉም" ብለዋል።

በገዳሙ ፀበል ስላለ እና የፍልሰታ ፆም እየገባም ስለሆነ ምዕመናን በሥፍራው እንደሚገኙ አቶ ዳኛቸው ጠቅሰዋል።

"ዛሬ መድኃኔዓለም ስለሆነ ፀሎት ላይ እያሉ የዋሻው አንድ ክፍል የመንሸራተት አደጋ ገጠመው። የክረምቱ በሌሊት ዝናብ ሲዘንብ ነው ያደረው" ብለዋል።

የሞጃና ወደራ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት በማኅበራዊ ገጹ ባወጣው መግለጫ በአደጋው የተሰማውን "መሪር ሐዘን" ገልጿል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ የማነብርሀን ተስፈ እና የወረዳው አመራር እንዲሁም የፀጥታ አመራሮች በቦታው በመገኘት "ነፍስ በማዳን ርብርቡ ላይ ሁለተናዊ ድጋፍ አድርገዋል" ሲልም አስታውቋል።

የሕክምና ባለሙያዎችም በቦታው በመገኘት "ለተጎዱ ወገኖችን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ብርቱ ትግል አድርገዋል" ሲል መግለጫው አክሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት በማኅበራዊ ገጹ አደጋው "ልብ ሰባሪ" መሆኑን አመልክቷል።

የአገረ ስብከቱ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምናጦስ በሥፍራው በመገኘት "ለሞቱት ፀሎተ ፍትሐት፣ ለተጎዱት ፀሎት፣ ላዘኑ ወገኖች የማጽናኛ ትምህርተ ወንጌልና አባታዊ ቃለ በረከት በመስጠት ላይ ይገኛሉ" ሲልም መግለጫው አክሏል።