ከሦስት ዓመት በፊት በእስራኤል ጥቃት ለተገደሉ 112 ፍልስጤማውያን በጋዛ ቀብር ተፈፀመ

አስከሬን አጠገብ ቁጢጥ ያለ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በጋዛ ጦርነት የመጀመሪያ ወራት እአአ በ2023 የእስራኤል ጦር በመኖሪያ መንደር ላይ በፈጸመው ጥቃት በአብዛኛው ሴቶች እና ሕፃናት ለሆኑ ሟቾች በጋዛ የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፀመ።

አስከሬኖቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለት ቤተሰቦች አባላት እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን ለሁለት ሳምንታት በወሰደ ተልዕኮ ከፍርስራሾች ውስጥ መውጣታቸው ታውቋል።

አስከሬኖቹ ተደርድረው የሚያሳይ ምሥል ይፋ የሆነ ሲሆን፤ ዘመዶቻቸው ተሸክመው ከማንሳታቸው በፊት እያንዳንዳቸው በፍልስጤም ባንዲራ እና በሟቾቹ ፍሮግራፍ ተሽፍነው ታይተዋል።

የቀብር ሥነ ስርዓቱ በጋዛ ከተካሄዱ ተመሳሳይ ቀብሮች ውስጥ ትልቁ እንደሆነ ተነግሯል።

አሊ አቡ ሻሪያ የተባሉ ሐዘንተኛ "ይህ ስሜት እንዲሰማን ነው የተፈለገው፤ የሕመም ስሜት፣ የሐዘን እና የማጣት" ብለዋል።

"ማውጣት ከቻልን እና ከቀበርናቸው በኋላ ሁላችንም አሁንም እየኖርንበት ያለው የሕመም እና የማጣት ስሜት ቢኖርም ምናልባት ከፊል እፎይታ ይሰማን ይሆናል።"

የሞቱት ሰዎች የአንድ ጎሳ አባላት ከሆኑ ሁለት ቤተሰቦች የተገኙ 44 ሕፃናት፣ 38 ሴቶች እና ሰባት አካል ጉዳተኞች መሆናቸው በዝርዝር ተጠቅሷል።

ሟቾቹ የተገደሉት እ.አ.አ ኅዳር 22/2023 እስራኤል በጋዛ ከተማ ሳብራ መኖሪያ መንደር ጥቃት በመፈፀሟ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህ ሰዎች የተገደሉት ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በተፈፀመ ከባድ ድብደባ ነው።

ቢቢሲ የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ዒላማውን በተመለከተ መረጃ ጠይቆ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ ቢያንስ 73,377 ሰዎች በጋዛ መገደላቸውን ሐማስ መራሹ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ይህ አሃዝ በመንግሥታቱ ድርጅት ትክክለኛ ነው በሚል የሚታመን ነው።

በጋዛ የአስከሬን ፍለጋ ስራው 'የሲቪል መከላከያ' በተባለ በሐማስ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ስር በሚገኝ ተቋም እየተሰራ ነው። የተቋሙ ጥረት በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የተደገፈ ነው።

የቀይ መስቀል ቃል አቀባይ ፓትሪክ ግሪፊተስ "የቁስ ድጋፍ እናደርጋለን። ጓንቶች፣ አካፋዎች፣ የመከላከያ ቁሳቁሶች እና የሚጠቀሟቸውን የአስከሬን ከረጢቶች እናቀርባለን" ብለዋል።

የሟቾቹን ክብር በጠበቀ መልኩ የአስከሬን ፍለጋ ስራው እንዲሰራም ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን እንደሚሰጡ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

"የትኛውም ቤተሰብ የሚወዱት የቤተሰብ አባላቶቻቸው እንደተገደሉ መስማት የሚፈልጉት አይደለም" ሲሉም አክለዋል። "ሆኖም በራሳቸው መንገድ እርማቸውን እና ሐዘናቸውን ለመወጣት ወሳኝ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ወር ከሳብራ የአስከሬን ማውጣት ተልዕኮው ሲጀመር ቢቢሲ ዘግቧል።

በርካታ ወለሎች ባለው የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ 180 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መካከል 90 በመቶዎቹ መገደላቸውን የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ባሳል ተናግረዋል።

በአካባቢው ተጨማሪ አስከሬኖችን እንዳሉም ይታመናሉ።

በጋዛ ሰርጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የገቡበት አይታወቅም። የበርካቶቹ አስከሬን በጦርነቱ ወቅት የእስራኤል ጦርነት ሲበረታ በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረዋል ተብሎም ይታመናል።