ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕንድን ባንዲራ የምታውለበልብ መርከብ በየመን ባሕር ዳርቻ ሰመጠች
የሕንድ ባንዲራ የምታውለበልብ መርከብ በየመን ባሕር ዳርቻ ተመትታ መገልበጧን እና መስመጧን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በመርከቧ ውስጥ የነበሩ 14 ሰዎች ሕይወታቸውን ማዳን እንደተቻለ የሕንድ የመርከብ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሳርባናንዳ ሶኖዋል ተናግረዋል።
ከ14ቱ መርከበኞች ውስጥ 13ቱ ሕንዳዊያን ናቸው ተብሏል።
ሚኒስትሩ "ያልተጠበቀ ጥቃት" ያሉትን ክስተት ያወገዙ ሲሆን፤ በቀጣናው የባሕርተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።
መርከቧን የመታት ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ግልፅ አይደለም።
በሕንድ መርከብ ላይ የደረሰው ክስተት በቀይ ባሕር እየተፈፀሙ ካሉ ጥቃቶች መካከል የቅርብ ጊዜው ነው።
በየካቲት ወር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ አንዳንድ መርከቦች ቀይ ባሕርን በአማራጭነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስትር ባወጡት መግለጫ በንግድ መርከቦች ላይ በቀጣናው የሚፈፀመው ጥቃት "በእጅጉ አሳሳቢ" ነው ብለዋል።
"በቀጣናው የንግድ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ መቆም አለበት። በዓለም አቀፍ መተላለፊያ ነፃ እና ያልተገደበ እንቅስቃሴ እና ንግድ የዓለም አቀፍ ሕጎችን ተከትሎ በፍጥነት መመለስ አለበት።"
አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት ወር ኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀሙ ወዲህ በቀጣናው የመርከቦች መተላለፊያዎች ተስተጓጉለዋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ኢራን የዓለም ሁነኛ የነዳጅ መተላለፊያ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን የዘጋች ሲሆን፤ ይህም የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርሷል።
አንዳንድ ነዳጅ የጫኑ የሳዑዲ አረቢያ መርከቦች በቀይ ባሕር አማራጭ መስመሮችን እየተጠቀሙ የነበረ ቢሆንም፤ በየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቅርቡ በሳዑዲ መርከቦች ላይ እየፈፀሙ ያለው ጥቃት በቀጣናው አደጋውን በበለጠ ከፍ አድርጎታል።
በሳዑዲ የሚደገፈው እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት ትራንስፖርት ሚኒስቴር በጀልባዎች ፈንጂዎችን በመጫን በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቶችን እየፈፀሙ ነው ሲል መክሰሱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በጥቃቶቹ ላይ ቡድኑ አስተያየት አልሰጠም።
ሁቲዎች ሳዑዲ በቀይ ባሕር ላይ እንዳትንቀሳቀስ እግድ የጣሉት ባለፈው ሐምሌ አጋማሽ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም የማሪታይም ኤጄንሲ ባለፉት ሳምንታት በቀጣናው በርካታ ጥቃቶች መፈፀማቸውን አስታውቋል።
ጥቃቶች እየተፈፀሙ ቢሆንም የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ከኢራን ጋር ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተስፋ መጫራቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል።
ባለፈው ሰኔ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም እና ወሽመጡን ለመክፈት ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት በተፈረመ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ኢራን መርከቦች ላይ ጥቃቶችን መፈፀሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁሙ እንዳበቃ ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ንግግሮች ፍሬያማ መሆናቸውን እና ሆርሙዝነረ በቀናት ውስጥ ለመክፈት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ገልፀዋል።
ኢራን ከአሜሪካ ጋር እየተደራደረች እንዳልሆነ እና ለመነጋገር ምንም ውጥን እንደሌላት በአንፃሩ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ ገልፃለች።