ሙዚቃ በሱቅ፣ በወጥ ቤት፣ በወፍጮ ቤት፣ በጋራዥ. . . የሚያጫውቱት ዲጄዎች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ከጀላሉ ሱቅ በቅርብ ርቀት ላይ ያለው ነጋዴ 'መወልወያ መወልወያ' ሲል በስሱ ይሰማል። ሸማች 'ኦሞ ስጠኝ' ብላ የሰፈሩን ባለ ሱቅ ትጠይቃለች።

ከሱቅ ወጥተን ወጥ ቤት ጎራ እንበል። ምግብ እየተሰናዳ ነው፤ ድንች ይላጣል፣ ሽንኩርት ይከተፋል፣ ቡና ይቆላል።

በሱቁ ወይም በወጥ ቤቱ ዲጄዎች ለማግኘት አይጠብቁም።

ዲጄ ሲባል መጀመሪያ የሚመጣልን ምሥል ምናልባትም የዳንስ ወለል ላይ ወዝ ወዝ የሚሉ ሰዎች እና ብልጭ ድርግም የሚል መብራት ይሆናል።

እነዚህ ዲጄዎች ግን ማንኛውንም ቦታ ለሙዚቃቸው መዳረሻ ማድረግ የሚችሉ ናቸው።

ጋራዥ፣ ቴአትር ቤት፣ ፀጉር ቤት፣ መጻሕፍት መደብር፣ ልብስ ሰፊ ቤት፣ ግንባታው ያልተጠናቀቀ 40/60 ሕንጻ፣ ሸክላ ሠሪ ቤት፣ ወፍጮ ቤት፣ ውይይት ታክሲ. . . የማይገቡበት የለም።

የቀጨኔ ሸክላ ሠሪ ሴቶች በዝግታ ጀበና ይቀርጻሉ። ዲጄዋ የምታጫውተውን የሙዚቃ ምት የሚከተሉ ይመስላል።

አንዳንዶቹ ሸክላ ሠሪዎች በተቀመጡበት ሆነው በሙዚቃው ይወዛወዛሉ።

ገብረወልድ ወጥ ቤት ደግሞ የምሳ ሰዓት የደረሰ ይመስላል፤ መሰናዶው ተጧጡፏል። ሽንኩርት እና ድንች እየተላጠ ዲጂዋ ሙዚቃ ታጫውታለች።

ሠራተኞቹ እንደ ወግ ባህሉ ቡና ቆልተው ያሸትቷታል።

ሜክሲኮ የሚገኘው ጋራዥ ውስጥ ከዲጄ ጀርባ ጥገና የሚሹ መኪኖች ተደርድረዋል። እሱም ሙዚቃውን ያጫውታል።

ዲጄዎቹን ዩቲዩብ ላይ 'ቀበሌ ራድዮ' ብለው ቢፈልጉ ያገኟቸዋል።

መሥራቾቹ ዲጄዎች ናቸው። አኪላስ እና ሮቤል ይባላሉ።

ግንባታው ባልተጠናቀቀው 'የሙሉጌታ 40/60' ሙዚቃ ያጫወተው ሮቤል ነው። የሰፈር ሱቅ ውስጥ ሙዚቃ ያጫወተው ደግሞ አኪላስ።

የቀበሌ ራድዮ "እናት ድርጅት" ቀበሌ ዜሮ ይባላል።

ቀበሌ ራድዮ ላይ ዲጄዎች በተለያዩ ሥፍራዎች ሙዚቃ ሲያጫውቱ ይታያል።

አኪላስ በሙያው አርክቴክት ነው። ከዩኒቨርስቲ ጀምሮ ዲጄም ነበር።

ሮቤል ጀርመን ነው ተወልዶ ያደገው። ከዲጄነቱ በተጨማሪ የማስታወቂያ ባለሙያ ነው።

ከሦስት ዓመት በፊት ሮቤል እና አኪላስ ከተገናኙ በኋላ የዲጄ መርሃ ግብሮች ማዘጋጀት ጀመሩ። በዚያ የተጀመረ ጓደኝነት ሙያዊ ግንኙነት ሆነ።

'ላይቭ' ሙዚቃን ፈጠራ በተሞላበት መንገድ ማቅረብ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

መገናኛ መስመር ላይ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያስተናግደው ቤታቸው በኮሪደር ልማት ፈርሷል። አሁን የቀበሌ ራድዮ ሙዚቃዎች የሚቀርቡት በበይነ መረብ ነው።

ኢትዮጵያውያንም ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የፈጠራ ሥራቸውን የሚያሳዩበት ቦታ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ቀበሌ ራድዮ የተፈጠረው የተለያዩ አርቲስቶች፣ ሙዚቀኞች እና ዲጄዎች የፈጠራ ሥራቸውን የሚያሳዩበት መድረክ እንዲሆን ነው።

የድሮ መጋዘንን ወደ ፈጠራ ሥፍራ ከለወጡ በኋላ በወራት ውስጥ በኮሪደር ልማት መፍረሱን አኪላስ ያስታውሳል።

"ቀበሌ ዜሮ እንደ መዳረሻ ሥፍራ ቢያከትምም" ወደ በይረ መረብ መሻገራቸውን ይናገራል።

ቀበሌ- ከከተማው ለከተማው

ሮቤል ነው ስሙን ያወጣው። ሐሳባቸው ለፈጠራ ባለሙያዎች የሚሆን ቦታ መፍጠር ነበር።

"በተቻለው መጠን ለከተማው እንዲሆን ነው ያሰብነው። ከከተማው ለከተማው" ይላል ሮቤል።

ሐሳቡ የመጣው ከቀበሌ መዝናኛ ነው። በእርግጥ ብዙዎች ቀበሌ ሲባል መጀመሪያ የሚያስቡት ጉዳይ ለማስፈጸም መጉላላትን ነው።

የቀበሌ መዝናኛ ግን የተለየ ነው። ሰርግ አለ፤ ጌሞች መጫወት ይቻላል፤ መሰባሰቢያ ነው፤ ሙዚቃ አለ፤ የሰፈሩን ክንውኖች ያስተናግዳል፤ ማኅበራዊ የስበት ማዕከል ማለት ይቻላል።

እናም ቀበሌ ዜሮ የሚለው ስያሜ ጸና።

የቀበሌ ራድዮ ሌላው አጋር ገብርኤል አበበ ባልቻ ሲሆን፤ ቀበሌ ራድዮ በሸገር ኤፍኤም ስቱዲዮ እና በቀበሌ ዜሮ ጥምረት ይዘጋጃል።

አኪላስ እና ሮቤል ቀበሌ ዜሮ "በአዲስ መንገድ ቀበሌን የሚያሳይ መንገድ" እንደሆነ ያምናሉ።

ቀበሌ ሲባል "ቢሮክራሲንም መዝናኛንም" ማሰብ ይቻላል።

"ቀበሌ ዜሮ ሲባል ሰዎች የፈጠራ ቦታ አድርገው ቢያስቡት ደስ ይለኛል። መነሻችን የሆነው ቀበሌ ማኅበራዊ ገጽታ አለው። የራሳችንን ትርጉም ሰጥተነዋል" ይላል አኪላስ።

ሁላችንም መሠረታችን ማኅበረሰቡ እንደሆነ የሚናገረው አኪላስ "ማኅበራዊ ነን፤ ያለ ማኅበሰረብ መኖር ከባድ ነው፤ ስለዚህ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል" ሲል ይገልጻል።

አሁን ላይ ማኅበራዊነታች ወደ ዲጂታሉ ዓለም እየሄደ ነው። በከተማው ያሉ ዋነኛ መዳረሻዎች ዲጂታል ቅርጽ እየያዙ መጥተዋል።

"ግባችን ገንዘብ አይደለም፤ የምንፈልገው ፈጠራ ማነሳሳት እና ለአገር ውስጥ ፈጠራ ቦታ መስጠት ነው" ይላል አኪላስ።

ሮቤል "መፍጠር የፈለግነው የማኅበረሰብ መሰብሰቢያ ቦታ ነው" ይላል።

ትኩረታቸው ማኅበረሰብ እንደመሆኑ ቀበሌ ሲታሰብ ማኅበሰረባዊ ስሜትን መፍጠር እንደሚፈልጉ ይናገራል።

"የሰፈር ሌንስ"

ቀበሌ ራድዮ በስሙ ልክ እንዲሆን የከተማው ነዋሪዎች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚጠቀሙባቸውን ቦታዎች ለማካተት እንዳሰቡ ሮቤል ይናገራል።

አዲስ አበባን አዲስ አበባ የሚያደርጓት ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?

ሰዎች አዲስ አበባን በትዝታ ሲያስቡ የሚያስቧቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?

ሱቅ፣ አትክልት ቤት፣ ወፍጮ ቤት. . . ይጠቀሳሉ።

ሮቤል እንደሚለው እነዚህ ቦታዎች በቪድዮዎች አይታዩም። ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው ለአዳዲስ አንጸባራቂ ሥፍራዎች ነው።

አዲስ አበባ "ለውጥ ላይ" ያለች ከተማ እንደመሆኗ አሁን የተለመዱ የሚመስሉን ሱቆች ከዓመታት በኋላ ይኖሩ ይሆን? ማን ያውቃል?

እነዚህን ቦታዎች በበይረ መረብ መሰነድ (Visual Archiving) እንደሚያስፈልግ ሮቤል ይናገራል።

"የሰፈር ሌንስ" እንዲኖረን ሰፈርን ሰፈር የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚለውን የሚገልጹ ቦታዎችን ይመርጣሉ።

አኪላስ እንደሚለው፤ ቀበሌ የሚይዛቸው ቦታዎችን እና የሰዎችን ትውስታ ያገናኛሉ። እንደ ሥጋ ቤት፣ ሱቅ እና ፖስታ ቤት ያሉ የጋራ ቦታዎችን "የማኅበረሰቡ ቅጥያ" ይላቸዋል።

እንዲህ ባሉ ሥፍራዎች ሙዚቃ መቅረጽ ማኅበረሰቡን ማሳየት እና መሰነድም ነው።

ቀረጻው ሁሌም አልጋ በአልጋ አይደለም። ለምሳሌ ሱቅ ሄደው ለአንድ ሰዓት ሙዚቃ እናጫውት? ብለው ሲጠይቁ ባለ ሱቆቹ ግራ ተጋብተው ነበር።

ሐሳቡ እንግዳ ከመሆኑ ባሻገር ብዙዎች ቪድዮ መቀረጽ እምብዛም ምቾት አይሰጣቸውም።

ፀጉር ቤት ሄደው ለመቅረጽ ሲጠይቁ "ለምን ፀጉር ቤት ይቀረጻል?" ተብለው ተጠይቀዋል።

ግን ሒደቱን አስደሳች እንደሆነ ሮቤል እና አኪላስ ይናገራሉ። ቀረጻው ምን እንደሚመስል፣ ግባቸው ምን እንደሆነ ካስረዱ በኋላ ይሁንታ ያገኛሉ።

". . .የአዲስ አበባ ፀጉር ቤት ምን ይመስላል? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ቪድዮው አለ። የሰፈር ፀጉር ቤት እንጂ ቅንጡ ቦታ አይደለም የቀረጽነው። ደስ የሚሉት እና የራሳቸው ውበት ያላቸው የሰፈር ፀጉር ቤቶች ናቸው" ይላል አኪላስ።

የግንባታ ቦታ፣ ወጥ ቤት፣ ሱቅ በመሳሰሉት ቦታዎች ሙዚቃ ማጫወት ከባድ ቢሆንም ደስ የሚልም ነው።

አዲስ አበባን የሚገልጹ፣ ታሪካዊ መልክ ያላቸው ሌሎች ቦታዎችም መፈለጋቸውን ቀጥለዋል።

ሙዚቃን በ40/60 ወይም በሱቅ ማጫወት ምን ስሜት ይፈጥራል?

ሮቤል በግንባታ ላይ ባለ 40/60 ሙዚቃ ማጫወት "ለራስ ሙዚቃ እንደማጫወት ነው" ሲል ይገልጸዋል። ታዳሚ የለም።

ሙዚቃ የሚያጫውትበትን ቦታ ከግምት አስገብቶ የሙዚቃዎቹን ዓይነት ይመርጣል። ያደገበት በርሊንን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ ተሞክሮዎች የተለመዱ ናቸው።

በእርግጥ የሸክላ ሥራ ቦታ፣ ወጥ ቤት ወይም ልብስ ሰፊ ቤት ዲጄ ባይኖርም ራድዮ ከፍተው ሙዚቃ ይሰማሉ። ሙዚቃው በዲጄ ሲሆን ግን የተለየ ገጽታ አለው።

አኪላስ ሙዚቃ ሱቅ ውስጥ ማጫወትን ሲገልጽ ከሮቤል ጋር ተመሳሳይ ዕይታ አለው። ታዳሚ የለም። ከባለ ሱቁ እና ከውስን ሸማቾች ውጭ።

"ለራሴ ነው ሙዚቃ የማጫውተው። ግን ሱቁ ደስ የሚል ቦታ ነው፤ የተለመደ አይደለም። ሙዚቃውን ሳጫውት በየትኛውም የዓለም ጥግ ያሉ ሰዎች እንደሚሰሙት እያሰብኩ ነው።"

ጠባብ የንግድ ቦታ ቢሆንም ከጀርባ የሚታየው ሸቀጥ ለቀረጻው ውበት ያላብሳል።

ሙዚቃውን ያጫወተው እሑድ ቀን ስለነበር "ስሜቱን እና በቦታው ያለውን ሰው" በማሰብ ሙዚቃዎቹን መርጧል።

ሸማቾች ሲገበያዩም ቀረጻው አይቋረጥም። የመደበኛው ቀን አካል ስለሆነ ንግግሮቹ ለቀረጻው ተፈጥሯዊ ስሜት ሰጥተዋል።

ዲጂታል ስነዳ ለትዝታ

አዲስ አበባ እየተለወጠች ነው፤ ያውም በፍጥነት። ዓመታት አሻግሮ "ከተማዋን መሰነድ እና ትውስታን መጠበቅ" የአኪላስ እና ሮቤል ሕልም ነው።

ሮቤል "ጊዜን ባለበት ማቆም" ሲል ይገልጸዋል።

ሰፈሮቹ ባሉበት ሆነው ይቀጥላሉ? ወይስ ቴክኖሎጂ ይለውጣቸዋል? ፀጉር ቤቱ፣ ሱቁ እንደዚህ ሆኖ ይቀጥል ይሆን?

"በምሥል የተቀመጠ ነገር ለትዝታም ይረዳል፤ ወደዚያ ጊዜ መንጥቆ ይወስዳል" ይላል ሮቤል።

የአንድን ዘመን ትዝታ ሰንዶ ማስቀመጥ አንድ ቀን ትውስታን ለመቀስቀስም ይውላል።

"አካባቢው ምን እንደሚመስል በመቅረጽ ምሥል ከሳች እንዲሆን እንፈልጋለን። ዘመንንም ይሻገራል።"

አኪላስ ከስነዳ በተጨማሪ ደስ የሚል ሙዚቃ ስብስብ ማሰማትን ያስባል። በዐይን የምትታየው አዲስ አበባ ብትሆንም፤ ሙዚቃዎቹ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚደመጡ ናቸው።

በዚህ ቦታ እንዴት ይሄን ሙዚቃ አጫወቱ የሚል ውይይት በፈጠራው ዓለም መፍጠርም ይፈልጋሉ።

"ለወደፊት የአዲስ አበባ የከተማ ሥሪት (Urban Fabric) ምን ይመስል እንደነበር ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ደስ ይላል። አዲስ አበባ በለውጥ ውስጥ ሳለች ነው እየቀረጽን ያለነው" ይላል አኪላስ።

ሮቤል እንደሚናገረው፤ ዲጄዎች ሲመርጡ በየትኛው ቦታ ምን ዓይነት ሙዚቃ ሊያጫወቱ እንደሚችሉ በማሰብ ነው።

"መጀመሪያ ላይ ዲጄዎቹ እንግዳ ነገር ሆኖባቸው ነበር። አሁን ግን ለመሳተፍ እየጠየቁን ነው። ምክንያቱም ልዩ ሐሳብ ነው። እዚህ ቦታ ብናጫወት የሚሉንም አሉ።"

አኪላስ "ከዚህም በላይ ብዙ ዲጄዎች እንዲኖሩ እንፈልጋለን" ይላል።

ሮቤል ከሰዎች የሚሰጣቸው አስተያየት "ቀና" እንደሆነ ይናገራል። ሐሳቡ መወደዱ ለቀጣይ ቀረጻዎች "አነሳሽ" መሆኑንም ይጠቅሳል።

ከቪድዮዎቹ አንዱ በሐረር ቤት የተቀረጸ መሆኑን በማንሳት ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ መዳረሻዎችን ማካተት እንደሚፈልጉ ይገልጻል።

ኢንስታግራም ላይ "ጎንደር ከመጣችሁ" "ድሬ ከመጣችሁ" እኔ ቤት ትቀርጻላችሁ የሚሏቸው መበራከታቸውን ሮቤል እና አኪላስ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያዊ እና ዳያስፖራ ዲጄዎችም ሰፈር እና ማኅበረሰብ የሚሰጣቸውን ስሜት የሚያንጸባርቁበት እንዲሆን ይፈልጋሉ።

የተነሱት "በትንሽ እቃ እና ቡድን" ነው።

እቃ እየተዋሱም፣ እየተከራዩም በአነስተኛ ቡድን ጀምረው እዚህ ደርሰዋል። ጥሩ አቀባበል እና ፍቅር ማግኘታቸው እንደሚያበረታቸውም ይናገራሉ።

አሁን ላይ ዕቅዱ ባይኖራቸውም "ገንዘቡ ከተገኘ" ምናልባት አንድ ቀን ቀበሌ ዜሮን ከበይነ መረብ አሻግረው ወደ 'ፊዚካል ስፔስ' ይመልሱት ይሆናል።