ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩኬ በሽብር የተከሰሰ አንድ ሶማሊያዊ አይኤስን ለመቀላቀል ኤአይን መጠቀሙ ተነገረ
በዩናይትድ ኪንግደም በሽብር የተከሰሰ ሶማሊያዊ ሰማዕት ለመሆን በኤአይ አይኤስን ለማግኘት ሙከራ ማድረጉን ፍርድ ቤት ገለፀ።
ሞሐመድ ሞሐሙድ የተባለው የ22 ዓመት ግለሰብ እ.አ.አ ከ2024 እስከ 2025 ድረስ ባለው ጊዜ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት አድርጓል በሚል ተከስሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ዐቃቢ ሕግ ናኦሚ ፓርሰንስ ተጠርጣሪው ከሶማሊያ እናቱን እና ወንድሙን ለመቀላቀል በ2020 ወደ ዩናይትድ ኪንግደን እንደመጣ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ሞሐሙድ በ2025 ሶማሊያ ከደረሰ በኋላ የሽብር ቡድኑን ለመቀላቀል "አጋዥ" በማጣቱ "ሙጀኸዲንን [የጅሃድ ታጋዮች] መቀላቀል" በሚል የኤአይ መልዕክት መለዋወጫን መጠቀሙን ገልፀዋል።
ፍርድ ቤት በሶማሊያ አስተርጓሚ ታግዞ የቀረበው ተጠርጣሪው ክሱን ውድቅ አድርጓል።
ዐቃቢ ሕጓ ተጠርጣሪው ዩኬ መኖር ከጀመረ ከሆነ ጊዜ በኋላ ፅንፈኛ እንደሆነ ገልፀዋል። የእስላሚክ እስቴት (አይኤስ) አስተሳሰብን መቀበሉን ተናግረዋል።
ይህም ወደ ሶማሊያ ተመልሶ የሽብር ቡድኑን እንዲቀላቀል ከፍተኛ ጉጉት እንዳሳደረበት አስረድተዋል።
'ሙጀኸዲን' የተባሉት ታጣቂዎች በሶማሊያ ፑንትላንድ ክልል ቦሳሶ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
ሞሐመድ ሞሐሙድ አይኤስን ለመቀላቀል ጠንካራ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሕይወት ግዴታው አድርጎ ተመልክቶታል ሲሉ ዐቃቤ ሕግ ፓርሰንስ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው ከሰሜናዊ ሶማሊያ ፑንትላንድ ግዛት መጥቶ በዩኬ ብሪስቶል ይኖር ነበር።
ሞሐመድ ሞሐሙድ ዩናይትድ ኪንግደም እያለ የሽብር ቡድኑን ለመቀላቀል መገናኛ መስመር ፈልጎ እንዳልተሳካለት ከዚያም መመለሻ ያለው ትኬት ቆርጦ እ.አ.አ ጥር 30/ 2025 ወደ ሶማሊያ ተጉዟል።
ምንም እንኳ የመመለሻ ትኬቱ መጋቢት የነበረ ቢሆን ሞሐመድ ሞሐሙድ ለመመለስ ምንም እቅድ አልነበረውም ብለዋል ዓቃቢ ሕጓ።
"የመልዕክት ልውውጦች እንደሚያሳዩት ሞሐመድ ሞሐሙድ ወደ ዩኬ የመመለስ ፍላጎት አልነበረውም። አይኤስን የመቀላቀል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሰማዕት የመሆንም ምኞት ነበረው" ብለዋል።
ተጠርጣሪው የመመለሻ ትኬት የቆረጠው ከቤተሰቦቹ ጥርጣሬ ለማምለጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"ቤተሰቦቹ እየተጠራጠሩት ነበር። እናቱ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው ሌላ የሽብር ቡድን በሆነው በአልሸባብ አስተሳሰብ አዕምሮው ተማርኳል ብለው ስለማሰባቸው ነግረውታል" ብለዋል።
ሞሐመድ ሞሐሙድ ሶማሊያ ሲደርስ የፑንትላንድ መንግሥት የፀረ ሽብር ተልዕኮዎችን እየፈፀመ ነበር።
ዐቃቤ ሕግ ፓርሰንስ መልማዮች 'ጦርነት ላይ ነን፤ በጣም የከፋ ሁኔታ ነው' ማለታቸውን ተከትሎ ቡድኑን መቀላቀል አዳጋች መሆኑ የተነገረው ተጠርጣሪው ተመልሶ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መብረሩን ተናግረዋል።
ወደ ዩኬ ከተመለሰ በኋላም ከመልማዮች ጋር ግንኙነት በማድረግ በፈለጉት ጊዜ እንደሚመለስ መናገሩን ገልፀዋል።