ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለኢራን ከሰላም ይልቅ የተመጠነ ግጭትን ማስቀጠል ተመራጭ ይሆን?
ኢራን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሠፈር ላይ የፈጸመችው ድንገተኛ የሚሳዔል ጥቃት እንዲሁ ሲታይ ለመረዳት አዳጋች ይመስላል።
ጥቃቱ አሜሪካ እና ኢራን ለጥቂት ቀናት ከተኩስ ልውውጥ ወስደውት የነበረው ፋታ እንዲያበቃ እና ዋሽንግተን ኢራን ላይ ድብደባ መፈጸም እንድትቀጥል አድርጓል። የኢራን እርምጃ ያልተመደ ዓይነት ነበር።
ቴህራን ቀዳሚ ፍላጎቷ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ከሆነ፤ የአሁኑን ጥቃት አስፈላጊነት ማብራራት ከባድ ነው። የኢራን አመራሮች ግምገማ፤ "ከቁጥጥር የማይወጣ ግጭት ማካሄድ የተሻለ ስትራቴጂካዊ የመደራደሪያ አቅም ያስገኛል" የሚል ከሆነ ግን ይህን ውሳኔ ለመረዳት ያቀለዋል።
ኢራን አደጋ ቢኖረውም የተመጠነ ጦርነት ውስጥ መግባት፤ ፍላጎቷን ለማስፈጸም የተሻለ እንደሆነ ልታምን ትችላለች።
አሁን ላይ፤ ሁለቱም ወገኖች ሙሉ ወደሆነ ጦርነት ለመግባት የተዘጋጁ አይመስሉም። አሜሪካ በቀጣናው የሚገኙ የኤነርጂ መሠረተ ልማቶችን አደጋ ላይ ሊጥል፣ ተጨማሪ አገራትን ወደ ጦርነቱ ሊያስገባ፣ የነዳጅ ዋጋን ሊያንር እንዲሁም ወታደራዊ ሀብቷን ይበልጥ ሊለጥጥ ለሚችል መጠነ ሰፊ ቀጣናዊ ግጭት እምብዛም ፍላጎት እንደሌላት አሳይታለች።
ኢራንም በተመሳሳይ ሙሉ በሙሉ ወደሆነ ጦርነት ላለመግባት እየሞከረች ነው። የአየር ኃይል መከላከያዋ በመዳከሙ፣ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቷ ተጋላጭ በመሆኑ እንዲሁም ኢኮኖሚዋ በማዕቀብ በመታነቁ፤ የመልሶ ግንባታ ወጪው ከባድ እና እጅግ ከፍተኛ ይሆንባታል።
ይህ ሁኔታ፣ ኢራን ከወታደራዊ ድል ይልቅ ቀጣይነት ያለው ጫና ማሳደር ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ መከተል የተሻለ ነው ብላ እንድትደመድም አድርጓት ይሆናል።
አሁን ባለው ሁኔታ ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ ተኩስ አቁም፣ ቴህራንን የተዳከመ አቋም ውስጥ ሊከታት ይችላል። አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የጣለችው እገዳ እንዲቀጥል፣ ማዕቀቦች ባሉበት እንዲቆዩ እንዲሁም ኢራን ከዓለም አቀፉ ኤነርጂ ገበያ ውጪ እንድትሆን ያደርጋል።
በሌላ በኩል ኢራን በኢኮኖሚያ ጉዳዮች ተገልላ በምትቆይባቸው ጊዜያት፤ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር እና ሌሎች በቀጣናው የሚገኙ ነዳጅ እና ጋዝ ላኪ አገራት በሂደት ወደ መደበኛ የኤክስፖርት አቅማቸው ሊመለሱ ይችላሉ።
ውስን የሆነ ግጭት ግን ኢራንን ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ያስወጣታል።
ምንም እንኳ ቴህራን ከፍተኛ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዋጋ እየከፈለች ቢሆንም፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞ መስተጓጎሉ እንዲሁም በሁቲዎች አማካኝነት ባብ ኤል ማንደብ ወሽመጥ ላይ የሚፈጠር ግፊት፤ በዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ፣ የኢንሹራንስ ዋጋ እና የኤነርጂ ገበያ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ይቀጥላሉ።
እዚህ ዘርፍ ላይ የሚፈጠር መጠነኛ እርግጠኝነት ማጣት ጭምር መንግሥታት፣ የመርከብ ባለቤቶች እና ምርት አስመጪዎች ለኢራን ጥያቄዎች ትኩረት እንዲሰጡ ያስገድዳል። ኢራን አሁንም የመደራደሪያ አቅም እንዳላት ልታምን ትችላለች።
በተጨማሪም ኢራን የዲፕሎማሲያዊ ውይይቱን ቅርጽ ለመቀየር እየሞከረች ይመስላል። የመርከብ ጉዞ ነጻነት ሊገደብ እንደማይችል መቀበልን ያልመረጠችው ኢራን፤ የመርከቦች ጉዞ እርሷ በተስማማችበት ወይም በምታስተዳድረው ሕግ መሠረት መደረግ እንዳለበት በተደጋጋሚ እየገለጸች ነው።
ይህ ትንተና ትክክል ከሆነ፤ የኢራን ግብ ሆርሙዝ ወሽመጥን ተጽዕኖዋን በምታሳድርበት መልኩ መክፈት እንጂ ከጦርነት በፊት ወደነበረው ሁኔታ በመመለስ አይሆንም። በተመጠነ መልኩ የሚቀጥል ግጭት ደግሞ ኢራን ግቧን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ጫና ማሳደሯን እንድትቀጥል ያስችላል።
በቴህራን ዐይን ሲታይ፤ ማዕቀቦች፣ እገዳዎችን እና ኢኮኖሚያዊ መገለሎች ባሉበት እንዲቆዩ የሚያደርግ ተኩስ አቁምን ከመቀበል ይልቅ፤ ቀጣናዊ ቀውሱን ሙሉ ጦርነት ከሚባል ደረጃ በታች አድርጎ ማስቀጠል ተመራጭ ነው።
የአገር ውስጥ ጉዳይም ስሌቱ ውስጥ ሊገባ ይችለል። ኢራን ከፍተኛ የዋጋ ጋሽበት፣ ሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ችግር እና የሕዝብ ቅሬታ እያጋጠማት ነው። ብዙውን ጊዜ መንግሥት ከውጭ አገራት ጋር ጦርነት በሚደረግባቸው ጊዜያት፤ በቀላሉ የአገር ውስጥ ተቃውሞዎችን ማፈን፣ ጥብቅ የደኅንነት እርምጃዎችን መውሰድ እና በአገር መከላከያ ሠራዊት ዙሪያ ደጋፍ ማሰባሰብ ይቀላቸዋል።
እነዚህ እርምጃዎች ኢራን ያሉባትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አያስወግዱም። በችግሮቹ ምክንያት የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ጫናዎችን ግን መቀነስ ያስችላታል።
ይህ ስትራቴጂ የሚያስከፍለው ዋጋ የለም ማለት ግን አይደለም። ኢራን ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃቶች እየደረሱባት እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ውስጥ እየገባች ነው። የመቋቋም አቅሟ በዚሁ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ የለም።
በአሁኑ ወቅት ካልተሟላ ሰላም ይልቅ በቁጥጥር ስር ያለ ግጭትን ማስቀጠል የተሻለ የመደራደሪያ አቅም ሊያስገኝ ይችላል። ነገር ግን ከቁጥጥር ስር ናቸው የሚባሉ ግጭቶች ከቁጥጥር የመውጣት ልማድ አላቸው።
ኢራን ሙሉ ወደሆነ ጦርነት ሳትገባ በአሜሪካ፣ በዓለም የኤነርጂ ገበያ እና በቀጣናው ዲፕሎማሲ ላይ ጫና ለማሳደር በሚያስችል መጠን ግጭቱን በጥንቃቄ መቆጣጠር እንደምትችል እምነት ሊኖራት ይችላል።
ነገር ግን ይህ ስሌት ከፍተኛ አደጋን ያዘለ ነው። መጠነ ሠፊ ወደሆነ ጦርነት ከመግባት ባሻገር፤ መቋጫ ምልክት የማይታይበት ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ የተራዘመ ግጭት በሂደት ኢራን ላይ ለሚወሰድ ጠንካራ እርምጃ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል።
ጦርነቱ አድማሱን እያሰፋ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። መጀመሪያ ላይ በቀጥታ ከመሳተፍ ተቆጥባ የነበረችው ሳዑዲ አረቢያ፤ ኢራን ውስጥ በሚገኙ የኢራን አጋር የሺዓ ቡድኖች ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ሁቲዎች ላይም ወታደራዊ እርምጃ ወስዳለች።
በዓለም ንግድ እና የኤነርጂ ገበያ ላይ የተፈጠረው መስተጓጎል የሚቀጥል ከሆነ፤ እስካሁን አቋም ላለመያዝ ወስነው የነበሩ አገራት ኢራን ላይ የሚደርሰው ጫና እንዲጨምር ለሚያደርግ እርምጃ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ።
አንዳንድ መንግሥታት፤ በዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ እና የኤነርጂ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ቀውሶችን በተደጋጋሚ ከማስተናገድ ይልቅ፤ ኢራን ላይ የሚወሰድ እርምጃ የሚያስከፍለውን ዋጋ መቋቋም የተሻለ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ የሚችሉበት ዕድል አለ።
ተጨማሪ አገራት ግጭቱ ውስጥ በቀጥታ ይሳተፋሉ የሚለውን ጨምሮ እነዚህ ቢሆኖች ትክክል የመሆናቸው ጉዳይ የተረጋገጠ አይደለም።
አብዛኛው ጉዳይ የሚወሰነው፤ ቴህራን የአሜሪካ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ስሌቶች መሠረታዊ በሆነ መልኩ እንዲቀየር የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ሳትገባ የምትወስዳቸውን የተመጠኑ እርምጃዎችን ማስቀጠል ትችላለች ወይ የሚለው ላይ ነው።
ኢራን በቀጣይ ልትወስድ የምትችለው ድንገተኛ ጥቃት ግጭቱ የቱን መንገድ ይከተላል የሚለውን ሊወስን ይችላል።