ቀጥታ, ትራምፕ ከኢራን ጋር አዲስ ንግግር ዛሬ እንደሚጀመር ጠቆሙ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ሊፈጸም የነበረ “መጠነ ሰፊ” ጥቃት እንዲቀር ካደረጉ በኋላ ዛሬ ሰኞ ከቴህራን ባለሥልጣናት ጋር አዲስ ንግግር እንደሚጀመር ተናገሩ። ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች “ጥቃቱ ምን ያህል የከፋ እንደሚሆን ያውቁታል፤ ምክንያቱም ዐይናቸው ስር የሚሆነው እያዩ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። “በድርድር መልክ እያየተነጋገርን ነው። ነገ [ሰኞ] ከሰዓት በኋላ ይጀምራል።”

ጭምቅ ሃሳብ

ትራምፕ ከኢራን ጋር አዲስ ንግግር ዛሬ እንደሚጀመር ጠቆሙ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩክሬን የሩሲያን ነዳጅ ማጣሪያ እና አየር ማረፊያ መምታቷን ስትገልጽ፤ ሞስኮ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀች

    ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ በመግባት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የአገሪቱን ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ እና የሩሲያ ስትራቴጂካዊ አቪዬሽን የሚገኝበትን አየር ማረፊያ መምታቷን ገልጻለች።

    ከዩክሬን ድንበር 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት የኤንግልስ አየር ማረፊያ እና የነዳጅ ማጣሪያ መመታታቸውን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

    እነዚህ መሠረተ ልማቶች የሩሲያን ጦርነት በገንዘብ ለመደገፍ እንደሚያገለግሉም ጠቅሰዋል። ፕሬዝዳንቱ ኤንግልስ አየር ማረፊያ እና ሳራቶቭ ነዳጅ ማጣሪያንም “ስትራቴጂካዊ ተቋማት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

    ካሉጋ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የነዳጅ ዴፖ እና በብራያንስክ ያለ የድሮን ማስወንጨፊያ ስፍራም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

    ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ስምንት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 635 ድሮኖችን መምታቷን እና መጥለፏን አስታውቃለች።

    በተጨማሪም በሩሲያ ትልቁ የኦንላይን ችርቻሮ ንግድ ኩባንያ የሆነው ‘ዋይልድቤሪስ’ መጋዘን እንደተመታ ተገልጿል።

    በሌላ በኩል ሞስኮ በጥቁር ባሕር የሚገኙ የዩክሬን ወደቦች እና ሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተናግራለች።

    ዩክሬንም በሰሜን ምሥራቅ ካርኪቭ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የፖስታ ተርሚናል ላይ በተፈጸመው የሩሲያ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን ገልጻለች።

    በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የሚገኙ ሠፊ የጦር ግንባሮች እንቅስቃሴ ሳይታይባቸው ባሉበት ቢሆኑም፣ ሁለቱም ወገኖች በዋና ዋና ከተሞች፣ በኤነርጂ መሠረተ ልማቶች እና መጋዘኖች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃት አጠናክረዋል።

    ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የሚመራው የሽምግልና ሂደት እስካሁን ድረስ ውጤት አላመጣም።

  2. ትራምፕ ዛሬ ከኢራን ጋር አዲስ ንግግር እንደሚጀመር ጠቆሙ

    በኢራን ላይ ሊፈጸም የነበረ “መጠነ ሰፊ” ጥቃት እንዲቀር ማድረጋቸውን ያስታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዛሬ ሰኞ አዲስ ንግግር ለመጀመር ከቴህራን ጋር እንደሚቀመጡ ተናገሩ።

    ትራምፕ “ጥቃቱ ምን ያህል ሰፊ እንሚሆን ያውቁታል፤ ምክንያቱም ዐይናቸው ስር የሚሆነው እያዩ ነበር” ሲሉ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “[ከቴህራን ጋር] በድርድር መልክ እያየተነጋገርን ነው። ነገ [ሰኞ] ከሰዓት በኋላ ይጀምራል።”

    ፕሬዝዳንት ይህንን ከማለታቸው አስቀድሞ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የድርድሩ "ማዕቀፎች" ላይ ስምምነት በመደረሱ ኢራን እና የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮች ማንኛውን ጥቃት "እንዲቆም" መጠየቃቸውን ጽፈዋል።

    ኢራን ለትራምፕ አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጦርነቱ ሊጠናቀቅ የተቃረበበት ጊዜ እንደቀረበ በተደጋጋሚ የተናገሩ ቢሆንም ጥቃት እና የአጸፋ እርምጃዎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።

    ትራምፕ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ከቴህራን ጋር ስምምነት የሚደረስበትን የጊዜ ገደብ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

    “ሁኔታው እንዴት እንደሚሄድ እናያለን። በፈለግነው ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን… ሰዎችን መግደል አልፈልግም” ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር ቅዳሜና እሁድ ጥቃት እንዳይፈጸም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል።

    "ሁላችንም ጥቃቱን ለመጀመር ተዘጋጅተን ነበር" ሲሉ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ "አጋሮቻችን ጥቃቱ እንዲዘገይ የጠየቁበት ምክንያት ስምምነት እንዳለ ስለሚያስቡ ነው" ብለዋል። "በሆርሙዝ ላይ ስምምነት አለ፣ እና በኒውክሌር ላይ ስምምነት ይኖራል" ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ይፋ ካደረጉ በኋላ ሰኞ ጠዋት በእስያ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል በ4.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ በ83.98 ዶላር ተሸጧል።

    ኢራን በአሜሪካ እና እስራኤል ለተከፈተባት ጦርነት ምላሽ ስትሰጥ በወሰደችው እርምጃ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አስመዝግቧል።

    በዓለም ላይ ካለው ድፍድፍ ዘይትና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የሚመጣው ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነው።

    የኢራን የዜና ወኪል የሆነው ሜህር፣ ቴህራን አሜሪካ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ ጠይቃለች መባሉን አስተባብሏል። አክሎም የትራምፕ ንግግር "አዲስ ውሸት ብቻ ነው" ብሏል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እሁድ ዕለት በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ከኦማን ጋር የተደረገው ድርድር "ወደ መጠናቀቁ እየሄደ ነው" ማለታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ንግግሩ ሰኞ ዕለት የሚካሄድበትን ቦታም ሆነ ሊሳተፉ የሚችሉ ባለሥልጣናትን እስካሁን ይፋ አላደረጉም።