ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ እየዛቱበት ያለው ምስጢራዊው የኢራን 'ፒካክስ ተራራ' ምን ይዟል?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርብ ጊዜ ኢራን ላይ ባሰሙት ዛቻ፤ እምብዛም የማይታወቀውን ሌላኛውን የአገሪቱ የኒውክሌር ጣቢያን ጠቅሰዋል።
ቴህራን የዩራኒየም ማብላያ ማሽኖችን ወደ 'ፒካክስ' ተራራ አዘዋውራለች የሚሉ ዘገባዎች ስለመውጣታቸው ተጠይቀዋል። ፕሬዝዳንቱም አሜሪካ "ምናልባትም በቅርብ" ጊዜ ውስጥ ይህንን ከመሬት በታች ባለ ተቋም ላይ "እጅግ ከባድ" ጥቃት እንደምትፈጽም ተናግረዋል።
ኢራን፣ በጠንካራ ሁኔታ የተመሸገው እና ገና ግንባታ ላይ ያለው ይህ ተቋም፣ ከዋና ከተማዋ ቴህራን በስተደቡብ 220 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በኢስፋሃን ግዛት፣ ናታንዝ ውስጥ የሚገኘውን የኒውክሌር ተቋም ለመተካት እንደሚገነባ ትናገራለች።
ናታንዝ ውስጥ የሚገኘውን ተቋም ዘመናዊ የዩራኒየም ማብላያ ማሽን (ሴንትሪፊውጅ) ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ማዕከልን የያዘ ነው።
በግምት የተቀመጠው የተቋሙ ስፋት፣ የዋሻዎቹ ጥልቀት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የደኅነንት ቁጥጥር መርማሪዎች ዝግ መሆኑ፤ ፒክአክስ ተራራ ተጨማሪ አገልግሎት ሊኖረው ይችላል የሚል ጥርጣሬ ፈጥሯል። እንዲሁም ስፍራው በከፍተኛ መጠን ከበለጸገው የኢራን የዩራኒየም ክምችት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተውበታል።
ኢራን በዚህ ተቋም ይተካል ያለችው በናታንዝ የሚገኘው የኒውክሌር ተቋም በአውሮፓውያኑ በሐምሌ 2020 ፍንዳታ አጋጥሞታል። ኢራን ክስተቱን "አሻጥር" ስትል የጠራችው ሲሆን፣ የተለያዩ ዘገባዎችም እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። እስራኤል ግን ለፍንዳታው ኃላፊነት አልወሰደችም።
ከወራት በኋላ ከናታንዝ በቅርብ ርቀት ያለ ተራራ ውስጥ "የበለጠ ዘመናዊ፣ ትልቅ እና አጠቃላይ" ምትክ ጣቢያ ለመገንባት መታቀዱን በወቅቱ የኢራን የአውቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት አሊ አክበር ሳሌሂ ይፋ አድርገዋል።
ከዚያም በዚያው ዓመት ደቡብ አቅጣጫ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ 'ኮላንግ ጋዝላ' ወይም 'ፒክአክስ' ተብሎ በሚጠራው ተራራ ውስጥ የግንባታ ምልክቶች መታየት ጀመሩ።
በቅርብ የተነሱ የሳተላይት ምሥሎች ደግሞ በተራራው ምሥራቃዊ እና ምዕራባዊ ክፍሎች ላይ ሁለት የዋሻ መግቢያዎችን አሳይተዋል። በደቡባዊ የተራራው ክፍልም መተላለፊያ ወይም መግቢያ ይታያል።
ከባህር ጠለል በላይ 1,608 ሜትር ገደማ ከፍታ የሚገኘው ፒክአክስ ተራራ፣ በምድር ስር የሚገነቡ በርካታ ወለሎችን ሊይዝ እንደሚችል መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። ይሁን እንጂ የግባታው ንድፍ ሳይመለከቱ ስፍራው የሚኖሩትን ወለሎች ብዛት በቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም።
ኢራን፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ከእስራኤል ጋር ከተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት በኋላ ወደ ስፍራው ለመግባት የሚቻልበትን መንገድ ይበልጥ አጥብቃለች። 'ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ' በተባለው ተቋም መረጃ መሠረት፣ ኢራን ግንባታ የሚካሄድበት ስፍራ ሙሉ ዙሪያውን በአጥር ከልላዋለች።
የሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ኢንስቲትዩት በየካቲት የመረመራቸው የሳተላይት ምሥሎች ላይ የዋሻ መግቢያዎች እየተጠናከሩ መሆኑን አሳይተዋል።
አንዱ የሳተላይት ምስል ከአንዱ መግቢያ በላይ አዲስ ኮንክሪት የሚመስል ቅርጽ መገንባቱን አመልክቷል።
ተቋሙ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የገባ እንደማይመስል ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ኢንስቲትዩት በቅርብ ጊዜ ባደረገው ትንተና ገልጿል።
በሰኔ መጨረሻ የተነሳ ምሥል ላይ አንዳንድ መግቢያዎች ክፍት እና መግባት የሚቻልባቸው ሆነው ይታያሉ።
በሌላ በኩል አሜሪካ እና እስራኤል የደበደቧቸው በናታንዝ፣ ፎርዶው እና ኢስፋሃን የሚገኙ ሌሎች የኢራን የኒውክሌር ተቋማት የመልሶ ግንባታ ምልክት እንደማይታይባቸው የሳተላይት ምሥሎች ጠቁመዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ፒካክስ ተራራ ላይ የሚደረግ ምንም ዓይነት የኒውክሌር እንቅስቃሴ እንደሌለ አስታውቋል።
በሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ኢንስቲትዩት ግምት መሠረት፤ ስፍራው አነስተኛ መጠን ያለው የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋም እንዲሁም ከፍተኛ አቅም ያላቸው ዘመናዊ የማብላያ ማሽኖችን መያዝ ይችላል።
ይህም ከፍተኛ አቅም ያላቸው ዘመናዊ የማብላያ ማሽኖቹን በመጠቀም በትንሽ ስፍራ ላይ ሌሎች የኒውክሌር ጣቢያዎች የሚያከናውኑትን ማሳካት ያስችላል ማለት ነው። ነገር ግን እነዚህን ማሽኖች መተከላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ የለም።
በተጨማሪም ስፍራው የማሽኑን አካላት፣ ጥንቃቄ የሚሹ መሣሪያዎችን ወይም የኒውክሌር ነዳጅ ቁሳቁሶችን ከጥቃት ለመጠበቅ ሊውል ይችላል።
በኒውክሌር መሣሪያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ የዩራኒየም ብረቶችን ሊይዝ እንደሚችልም የሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ኢንስቲትዩት አመልክቷል። ይህም ቢሆን ግን እስካሁን ማስረጃ አልተገኘበትም።
ከዚህም ባሻገር በስፍራው የተነሱ የሳተላይት ምሥሎች ላይ ከኒውክሌር ማብላያ ግንባታ ጋር የተያያዙ መገልገያዎችን እንደማያሳዩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ተራራ ስር የሚገኘው ይህ ስፍራ ለምን እንደሚውል ማረጋገጥን አስቸጋሪ ያደረገው ዋነኛ ጉዳይ፣ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ወደ ስፍራው እንዲገባ ፈቃድ አለማግኘቱ ነው። ኢራንም ከግንባታው ንድፍ ጋር የተያያዘ መረጃም አላቀረበችም።
ኢራን ስፍራው ለኒውክሌር ዓላማ ሊውል እንደሚችል የሚጠቁም መግለጫ ማውጣቷን ተከትሎ፤ መጋቢት ላይ የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ የተቋሙ ተቆጣጣሪዎች ወደ ስፍራው መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ኢራን በበኩሏ የኒውክሌር ቁሳቁስ ወደ ተቋሙ እስካልገባ ድረስ ለተቆጣጣሪዎች ፈቃድ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ትከራከራለች።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋም የቅርብ ጊዜ ግምገማ እንደሚያሳየው የ12 ቀኑ ጦርነት እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ እስከ 60 በመቶ የበለፀገ 440.9 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ነበራት። የኢራን ዩራኒየም የጥራት ደረጃ የኒውክሌር መሣሪያ ለመሥራት ለሚያስፈልገው የ90 በመቶ ጥራት ጥቂት የቀረው ነው።
የአምናው ጦርነት ከተነሳ በኋላ የዓለም አቀፉ ተቋም ተቆጣጣሪዎች ፈቃዳቸውን ተገፍፈዋል።
የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም 60 በመቶ የበለፀገው አብዛኛው የኢራን ዩራኒየም የተመረተው በፎርዶው እና ናታንዝ እንደሆነ መረጃ አለው። ይህ ግን ዩራኒየሙ አሁንም በእነዚህ ስፍራዎች ይገኛል ማለት ላይሆን ይችላል።
የኢስፋሃን የኒውክሌር ተቋማት የኒውክሌር ቁሳቁሶች ተቀምጦባቸው ሊሆን እንደሚችል ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ተቆጣጣሪ ጠቁሟል። ምናልባትም ከ200 ኪሎ ግራም በላይ የሚሆነው የበለጸገ ዩራኒየም ከመሬት በታች በተገነባ ተቋም ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሩ ራፋኤል ግሮሲ ተናግረዋል።
ኢራንን ዩራኒየም በተመለከተ በሚሰጡ ግምቶች ውስጥ ስሙ የሚነሳው አንዱ ስፍራ ፒካክስ ተራራ ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ባወጣቸው የስለላ ሰነዶችም ሆኑ የተረጋገጡ የሳተላይት ምሥሎች ይህንን መላምት አያጠናክሩም።
አሜሪካ ከመፈንዳቱ በፊት የአፈር፣ የድንጋይ እና የተጠናከረ ኮንክሪት ንጣፎችን ጥሶ መግባት የሚችለውን ጂቢዩ-57 ቦንብ በመጠቀም የኢራንን ፎርዶው የኒውክሌር ተቋም ደብድባለች።
የእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ስኬታማነት ግን ስፍራው በተገነባበት የድንጋይ ዓይነት፣ ተቋሙ ተራራ ውስጥ በሚገኝበት የጥልቀት መጠን እንዲሁም ቦንቡ በሚያርፍበት አቅጣጫ ላይ ይወሰናል። ይህ ጥቃት የተፈጸመው አሜሪካ እና እስራኤል ስለ ፎርዶው የኒውክሌር ጣቢያ ለዓመታት መረጃ ሲያሰባስቡ ከቆዩ በኋላ ነው።
በማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኒውክሌር ተመራማሪ የሆኑት ማቲው ሻርፕ ለዎል ስትሪት ጆርናል እንደተናገሩት፤ አሜሪካ ፒካክስ ተራራ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በፎርዶው ላይ በታየው መጠን ስኬታማ እንዲሆን ላትጠብቅ ትችላለች።
የዚህኛው ተቋም ግንባታ የበለጠ ጥልቅ መሆኑ እና ስለአቀማመጡ ብዙም አለመታወቁን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በፒካክስ ተራራ ጥቅል ስፍራ ውስጥ የተከማቹ የኒውክሌር ቁሳቁሶች ካሉ፣ በአየር ጥቃት ሊወድም ይችል እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይሁን እንጂ በሚፈጸም ጥቃት ምክንያት ወደ ስፍራው መግባት እና መውጣት ላይቻል ይችላል።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የዋሻ መግቢያዎች፣ መተለላፊያዎች እንዲሁም የኃይል እና የአየር ማቀዝቀዣ ሥርዓቶች ለእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም ከባሰ ሕንጻው ወደፊት ጥቅም ላይ እንዳይውል የማድረግ ዕድል አላቸው።
ምናልባትም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ፒካክስ ተራራ ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም የዛቱት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ይችላል።