በስሪላንካ የ572 ሰዎች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ተከትሎ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Ranjan Arun Prasadh, BBC
በሰሜናዊ ስሪላንካ ባለፈው የካቲት ወር የ572 ሰዎች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ተከትሎ ምርመራ ተከፈተ።
የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ጃፍና ክልል ቺማኒ በተባለ አካባቢ ሠራተኞች ለአስክሬን ማቃጠያ ሥፍራ ማስፋፊያ ቁፋሮ በሚያካሂዱበት ወቅት የሰው አስክሬን ካገኙ በኋላ ነበር።
እስከ ነሐሴ ወር ድረስ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በሥፍራው የቁፋሯቸውን ሦስተኛ ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ ታዳጊዎችን እና ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ የ572 ሰዎችን አፅም አግኝተዋል።
ከአፅሞቹ በተጨማሪም የትምህርት ቤት ቦርሳዎች፣ ጡጦ እና ሌሎች ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች አብረው ተገኝተዋል።
መቃብሩ በስሪላንካ የተገኘ ትልቁ የጅምላ መቃብር ሥፍራ እንደሆነ ይታመናል።
በአካባቢው የጅምላ መቃብር እንደሚገኝ ከዚህ በፊት ሲወራ ነበር።
በአገሪቷ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት አንድ ሴትን የደፈረ እና የገደለ ግለሰብ በፍርድ ሒደቱ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለተቀበሩበት የጅምላ መቃብሩ ተናግሯል። የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ደብዛቸው የጠፋ ሰላማዊ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልነበረም።
አሁን ላይ ያጋጠመው ክስተት አስከፊ ቢሆንም ለአስርተ ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ወቅት ቤተሰቦቻቸው ለጠፉባቸው ሰዎች ተስፋ ሰጥቷል።
ጂያሩቢይ ጂያባላን ደብዛቸው ከጠፋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አባቷ የሚገኙበት ሲሆን እርሷ እና ቤተሰቦቿ ለዘመናት መልስ ላጡበት ጉዳይ ምላሽ እናገኛለን ብለው ተስፋ አድርገዋል።
በርካታ የታሚል ብሔር ተወላጆች መቃብሩ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ወቅት በጅምላ የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበት እንደሆነ ያምናሉ። በመሆኑም ምርምራ እንዲደረግ እና ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በርካታ የታሚል ብሔር አባላት በሚኖሩበት የስሪላንካ ሰሜናዊ አካባቢ ለአስርተ ዓመታት በዘለቀ ግጭት ከፍተኛ ቀውስ አጋጥሞታል።
ከአውሮፓውያኑ 1983 እስከ 2009 የዘለቀው ይህ ጦርነት ደሴታማዋን አገር በብሔር ከፍፍሏል።
የታሚል ታይገር አማጺያን ሲንሃልስ በተባለው ብሔር በተያዘው መንግሥት ስልታዊ አድልዎ እየተፈፀመ ነው በማለት በአገሪቷ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ራሱን የቻለ አገር ለመመስረት ታግለዋል።
ለ26 ዓመታት በዘለቀው በዚህ ግጭት ወደ 100 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአብዛኛው የታሚል ብሔር ተወላጆች የሆኑ 23 ሺህ ገደማ ሰዎች ጠፍተዋል።
ለዚህም የጸጥታ ኃይሎች እና የታሚል ታይገር ታጣቂ ቡድን ይከሰሳሉ።
እአአ በ1995 ግጭቱ ከቆመ በኋላ የስሪላንካ ጦር በ'ታሚል ታይገር ኢሌማ ነፃ አውጭ' ተይዞ የነበረውን ጃፍና ሰርጥ ተቆጣጥሯል። ይህም የጦሩነቱ ወሳኝ እጥፋት ተደርጎ የታየ ሲሆን እአአ በ2009 በታይገሮች ሽንፈት ጦርነቱ ተጠናቋል።















