በአዲስ አበባ ተማሪዎችን ከፍተኛ ክፍያ ከሚጠይቁት ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት የሚሰጥ ትምህርት ነጻ ሲሆን፣ የግል እና አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ክፍያ ግን እንደ ትምህርት ቤቱ ዓይነት እና ከሚሰጡት ትምህርት አንጻር ከሺዎች እስከ ሚሊዮኖች ብር ይደርሳል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ተማሪ በዓመት ከሚያስከፍሉት ክፍያ አንጻር ከፍተኛ የሚባሉ ዋጋዎችን ያስቀምጣሉ።
በአውሮፓውያኑ 2026/27 የትምህርት ዘመን የወጡ የክፍያ መረጃዎች እነዚህ ትምህርት ቤቶች በዓመት እስከ 37 ሺህ ዶላር በላይ ወይም ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ብር እንደሚያስከፍሉ ያመለክታሉ።
ትምህርት ቤቶቹ እንደ ተማሪው ዜግነት፣ የክፍል ደረጃ እና የክፍያ ዓይነት የተለያየ ተመንም አላቸው።
ከዓመታዊ የትምህርት ክፍያ በተጨማሪም፣ የምዝገባ፣ የፈተና፣ የመጽሐፍት እና የትምህርት ቁሳቁሶች የመሳሰሉ ተጨማሪ ወጪዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
ከፍተኛ ክፍያ ከሚጠይቁት ውስጥ ለማሳያ ያክል ሦስት ትምህርት ቤቶችን የመረጥን ሲሆን፣ የትምህርት ቤቶቹን ክፍያ በተመለከተ መረጃ ለማግኘት የተለያዩ ምንጮችን እና የትምህርት ቤቶቹን ድረ ገጾች ተጠቅመናል።
ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል (ICS Addis)፣ ለ2026/27 የትምህርት ዓመት እንደ ተማሪው የትምህርት ደረጃ የተለያየ የዓመት ክፍያ ይፋ አድርጓል።
ትምህርት ቤቱ በድረ-ገጹ እንዳመለከተው፣ ክፍያዎቹ በዶላር የሚሰሉ ሲሆን፣ ከ3 እስከ 4 ዓመት ላሉ ልጆች የሙሉ ቀን ትምህርት ዓመታዊ ክፍያ 19 ሺህ 495 ዶላር ወይም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።
ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ እንደየ ክፍል ደረጃው የክፍያው መጠን ጨምሮ፣ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የክፍያ መጠን ደግሞ 37 ሺህ 215 ዶላር ወይም 5,982,914 ብር በዓመት ይደርሳል።
ለትርፍ ያልተቋቋመ እንደሆነ የሚገልጸው ትምህርት ቤቱ ከዓመታዊ የትምህርት ክፍያው በተጨማሪ፣ ለምዝገባ 300 ዶላር ወይም ከ48 ሺህ ብር በላይ ክፍያ ይጠይቃል።
እንደ የክፍል ደረጃው ደግሞ አዳዲስ ተማሪዎች እስከ 10 ሺህ ዶላር ወይም 1,633,544 ብር ለትምህርት ቤቱ ማሻሻያ እና ሌሎችም ወጪዎች የሚውል ክፍያም መክፈል አለባቸው።
ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል በአውሮፓውያኑ 1964 የተመሠረተ ሲሆን፣ የ3 ዓመት እድሜ ካላቸው ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ይቀበላል። ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ትምህርት ለማብቃት ያለመ ዓለም አቀፍ የትምህርት ሥርዓት እንደሚከተል ይጠቅሳል።
ከመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም በተጨማሪ፣ በተማሪዎች ፍላጎት እና ፍጥነት ላይ የሚያተኩር የትምህርት አቀራረብ እንደሚከተልም በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በተጨማሪም ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ያሉ እንደ የስፖርት፣ ሥነ-ጥበብ ፕሮግራሞች እና ዝግጅቶች እንዲሁም ለተማሪዎች የተለያዩ ልምዶችና የመማር ዕድሎችን እንደሚያቀርቡ ያስታውቃል።
የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት፣ ለአውሮፓውያኑ 2026/27 የትምህርት ዘመን የተለያዩ የክፍያ ደረጃዎችን በድረ ገጹ ላይ አስቀምጧል።
ትምህርት ቤቱ እንደሚገልጸው፣ ቢያንስ 75 በመቶ የትምህርት ክፍያቸው ወላጆች በሚሠሩባቸው ተቋማት የሚሸፈንላቸው የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዓመት 20 ሺህ 803 ዩሮ ወይም ከ3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ይከፍላሉ።
ከ5ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ደግሞ ዓመታዊ ክፍያው 3.6 ሚሊዮን ብር ነው።
በራሳቸው የሚከፍሉ ወላጆች የሚከፍሉት ግን ከዚህ ያንሳል። ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል 8 ሺህ 808 ዩሮ ወይም 1.6 ሚሊዮን ብር ገደማ፣ ከ5ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ 8 ሺህ 439 ዩሮ ማለትም ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በዓመት ይከፍላሉ።
ከዓመታዊ የትምህርት ክፍያ በተጨማሪ፣ የአስተዳደር ክፍያ ይኖራል። የትምህርት መጽሐፍት እና ቁሳቁሶችም በተለየ ክፍያ ይገኛሉ።
የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት የጀርመን መንግሥት የትምህርት ሥርዓትን ይከተላል። ለከፍተኛ ትምህርት ለማብቃት ያለመ ዓለምአቀፍ የትምህርት ሥርዓትንም እንደሚከተል ይገልጻል።
ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ፣ ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥነ-ጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በድራማ እና በስፖርት በመሳሰሉ የተለያዩ ተግባራት ይሳተፋሉ።
ትምህርት ቤቱ በድረ ገጹ እንዳስቀመጠው፣ ተማሪዎች በሳይንሳዊ ሙከራዎች፣ በስፖርት፣ ምርቶችን ድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል የመሰሉ ፕሮጀክቶች እና በእጅ ሥራዎች ይሳተፋሉ። እነዚህ ተግባራት በየትምህርት ዘመን አጋማሹ በተማሪዎች ፍላጎት መሠረት ሊለዋወጡ ይችላሉ።
ለኢትዮጵያዊ ዜጎች ክፍያው በብር የሚፈጸም ሲሆን፣ የሚከፈለው መጠን በወቅቱ ባለው የጀርመን ኤምባሲ የዩሮ እና የብር ምንዛሪ ተመን ይሆናል።
የተጠቀሱት ክፍያዎች ግን የአስተዳደር፣ የመጽሐፍት እና የትምህርት ቁሳቁሶች ተጨማሪ ክፍያዎችን አያካትቱም። ሌላው ተማሪዎች ከትምህርት ቤት በሚወጡበት ሰዓት ቢያንስ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ድረስ ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ ካልወሰዳቸው ከ11፡30 ጀምሮ በሚታሰብ በየሰዓቱ 18 ዩሮ ወይም 3300 ብር ገደማ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።
የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት ታሪክ የሚጀምረው ከአውሮፓውያኑ 1926 ነው። ወቅቱም የጀርመን ሚሲዮናውያን የመጀመሪያውን ማኅበር የመሠረቱበት ነበር።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ትምህርት ቤቱ ከተዘጋ በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 1954 እንደገና ተከፍቶ ከተለያዩ ዓለም የመጡ የውጭ አገር ዜጎችን ጭምር በማስተማር ሥራውን ቀጥሏል።
ሊሴ ገብረ ማርያም
ሌላው በአዲስ አበባ የሚገኘው ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ክፍያ ከሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ በአውሮፓውያኑ ለ2026/27 የትምህርት ዘመን እንደ ተማሪው ዜግነት እና የትምህርት ደረጃ የተለያየ ክፍያ አስቀምጧል።
በኢትዮጵያዊ ዜጎች እና የኢትዮጵያ ዜግነት መብት መታወቂያ ላላቸው ተማሪዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ ዓመታዊ ክፍያ 401 ሺህ 800 ብር ሲሆን፣ ለሁለተኛ ደረጃ 420 ሺህ ብር ነው።
ለፈረንሳይ ዜጎች ደግሞ የዓመት ክፍያው ለመጀመሪያ ደረጃ 6,750 ዩሮ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7,150 ዩሮ ነው። ይህም አሁን ባለው ምንዛሪ በብር ከ1.2 ሚሊዮን እና 1.3 ሚሊዮን በላይ ነው።
ከፈረንሳይና ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ ዜግነት ያሏቸው ተማሪዎች ደግሞ ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች 8,800 ዩሮ ወይም 1.6 ሚሊዮን በላይ ብር ሲሆን፣ ለሁለተኛ ደረጃ 9,550 ዩሮ ወይም 1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ይከፍላሉ። ይህም በ2026/27 በሰንጠረዡ ላይ ከተመዘገቡት የትምህርት ክፍያዎች ከፍተኛው ነው።
ከዓመታዊ የትምህርት ክፍያ በተጨማሪ፣ ትምህርት ቤቱ ለምዝገባ፣ ለትምህርት ቁሳቁስ፣ ለፈተና እና ለምስክር ወረቀት ክፍያዎችንም ለይቶ አስቀምጧል።
ለኢትዮጵያዊ ተማሪዎች እና የኢትዮጵያ ዜግነት መብት መታወቂያ ላላቸው ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች 296,400 ብር ነው።
በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፈረንሳይ እና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል የተደረገውን የሁለትዮሽ ስምምነት ተከትሎ፣ ትምህርት ቤቱ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1948፣ 176 የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን በመቀበል ነበር ሥራውን የጀመረው።
ሊሴ ገብረ-ማርያም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በፈረንሳይ ትምህርት ሥርዓት ዕውቅና ያገኘ ትምህርት ይሰጣል።
ትምህርት ቤቱ ከፈረንሳይ ውጭ የፈረንሳይኛ ቋንቋን እና ባህልን ለማስፋፋት በሚሠራው ድርጅት የሚተዳደር የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ የጋራ ተቋም ሲሆን፣ ከ1,800 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ተቋሙ ይገልጻል። ከእነዚህም 70 በመቶዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አጽብሃ አብርሃ እንደሚናገሩት በከተማዋ 1,500 ያህል የግል ትምህርት ቤቶች አሉ።
ትምህርት ቤቶቹ የመምራን ደመወዝ ለመክፈል፣ የመምህራን እና የአስተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን እና የትምህርት ግባዓቶችን ለማሟላት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳሉ።
"ለአንዳንድ ሰዎች እነዚህ ትምህርት ቤቶች ዝም ብለው ብር እያፈሰሱ ሊመስል ይችላል እውነታው ግን ሌላ ነው" የሚሉት አቶ አጽብሃ፤ የትምህርት ቤት ባለቤት መሆን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ነው ይላሉ።
ቢቢሲ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች የትኞቹ ናቸው የሚለውን ለማሳየት እነዚህን ትምህርት ቤቶች አቀረበ እንጂ በሚሊዮኖች ብር የሚያስከፍሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ቁጥር ጥቂት የሚባል እንዳልሆነ ባደረገው ዳሰሳ ተረድቷል።















