ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር አወዛጋቢውን የዓለም ዋንጫን ለግል ባለሀብቶች የመሸጥ ዕቅድ ሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም ዋንጫ የንግድ ድርሻን ለግል ባለሃብቶች ለማስተላለፍ ታስቦ የነበረው ፕሮጀክት መሰረዙን ይፋ አደረጉ።
ኢንፋንቲኖ ፕሮጀክቱ በግልጽ "መከፋፈል መፍጠሩን" ተረድተናል ካሉ በኋላ በመጀመርያው ዓላማ ላይ "አሁን ፍላጎት የለንም" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም "በዚህም የተነሳ ዕቅዱ ተግባራዊ አይሆንም" ብለዋል።
ኢንፋንቲኖ የማኅበሩ 211 አባላት የወንዶች እና የሴቶች ዓለም ዋንጫን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና ጨዋታዎችን ለግል ባለሃብት ለማስተላለፍ የቀረበውን ዕቅድ የሚደግፉ ከሆነ 40 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።
እስከ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ዕቅዱን የሚቀበሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የመጀመሪያውን 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኙም ተናግረው ነበር።
የእስያ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ሼክ ሳልማን ቢን ኢብራሂም አል ካሊፍ የዕቅዱን መሰረዝ ደግፈውታል።
"የዓለም አቀፍ እግር ኳስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሁሌም ቢሆን ትክክለኛ ምክክርን፣ የጋራ ውይይትን እና ለስፖርታችን የተዘረጋውን የአስተዳደር መዋቅር ማክበርን መሠረት በማድረግ ሊቀረጽ ይገባል" ሲሉ ሼክ ሳልማን ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር 55 አባላት ፊፋ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ራሳቸውን ለማግለል ድምጽ ሰጥተው ነበር።
የፊፋ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬቨን ላሞር እግር ኳስን የሚያስተዳድረው አካል በዚህ ፕሮጀክት "ተጭበርብሯል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ላሞር አክለውም "ፕሮጀክቱ የፊፋ ሳይሆን የሕግ አሰራርን ያልተከተለ የአንድ ሰው ፍላጎት ብቻ ነው" ሲሉ ተችተውታል።
የኢንፋንቲኖ የቅርብ አማካሪ እና የቀድሞው የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካርሎስ ኮርዴሮ "ይህ ለእግር ኳስ አደገኛ ውል ነው" በማለት ከተናገሩ በኋላ "የእግር ኳስን መጻዒ ጊዜ በዕዳ ማስያዝ ነው" ብለው ከሥልጣናቸው ለቅቀዋል።
ሁለት ሌሎች ከፍተኛ የእግር ኳስ ባለሥልጣናትም ዕቅዱን ተቃውመው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የማዕከላዊ አሜሪካ እና የካሪቢያን አገራት የእግር ኳስ ባለሥልጣናት በበኩላቸው አባላቶቻቸው ዕቅዱን "ውድቅ" ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አክለውም በርካታ በቀጣናው የሚገኙ ማኅበራት በኢንፋንቲኖ ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል ብለዋል።
የእስያ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከአውሮፓ እና ሌሎች የእግር ኳስ ማኅበራት ጎን እንደሚቆም አስታውቋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ኢንፋንቲኖ የዓለም እግር ኳስ ማኅበርን ለመምራት "ትክክለኛው ሰው አይደሉም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የ56 ዓመቱ ኢንፋንቲኖ ለአራተኛ ጊዜ ለመመረጥ እየተዘጋጁ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል።
ለእግር ኳስ ባላቸው "የጋራ ፍላጎት መንፈስ፣ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ሁሉ ዳግም አንድ ላይ ለማምጣት" እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢንፋንቲኖ አቅርበውት የነበረው ዕቅድ፣ ፊፋ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የሚያዘጋጃቸው ዋና ዋና ውድድሮችን የሚመራ የንግድ ድርጅት እንዲቋቋም የሚያደርግ ነበር። አሁን በተሰረዘው ዕቅድ መሠረት የውጭ ባለሀብቶችም የዚህን ድርጅት ድርሻዎች መግዛት ይችላሉ።
በፕሬዝዳንቱ ዕቅድ መሠረት "ሦስተኛ ወገን" ባለሀብቶች 'ፊፋ ፎርዋርድ ኢንተርፕራይዝ' የሚል ስያሜ ይሰጠዋል የተባለው ድርጅት ውስጥ እንዲገዙ የሚጋበዙት "አነስተኛ እና ተቆጣጣሪነት እንዲኖራቸው የማያደርጉ" ድርሻዎችን ነው።















