ጥምረት መመሥረታቸውን ስላስታወቁት ታጣቂ ቡድኖች ምን እናውቃለን?

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን መንግሥት ከሥልጣን ማስወገድ ዓላማው ያደረገ ነው የተበላው "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረቱ ይፋ ሆኗል።
የጥምረቱ ሰብሳቢ በተባለው እና የአማራ ፋኖ መሪ በሆነው ዘመነ ካሴ ከቀረበው መግለጫ በተጨማሪ የጥምሩ አባል ቡድኖች ባጋሩት መገለጫ ላይ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በማስወገድ "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ አለው።
ይፋ በተደረገው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው "ትብብር ለኅልውና" በተባለው ጥምረት ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ጠብመንጃ አንስተው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል ሳባቱ ተካትተዋል።
እነዚህም የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አፋብን)፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦነብግ)፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው።
እነዚህ በአንድ ጥምረት ውስጥ መሰባሰቸባው የተገለጹት ታጣቂ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በጠላትነት የሚተያዩ የነበሩ ሲሆን፣ የቀደመ አለመግባባታቸውን በምን መልኩ ፈትተው ከስምምነት እንደደረሱ አልተገለጸም።
በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች ውስጥ መሠረታቸውን ያደረጉት እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች ታሪካዊ ዳራ ምን ይመስላል?
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ50 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው አንጋፋ ከሚባሉት የፖለቲካ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።
የተመሠረተው የደርግ ወታደራዊ መንግሥትን ተቃውመው ወደ ደደቢት በረሃ በወረዱ ሰባት አባላቱ እንደሆነ ይነገራል።
ህወሓት ለ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ቆይቶ ከሌሎች ብሔር ላይ ከተመሠረቱ ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመመሥረት ወታደራዊውን መንግሥት ገርስሰው በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ሥልጣንን ተቆጣጥረዋል።
ከዚያም ለሦስት አስርተ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ኢህአዴግ የሚባለው የአራት ድርጅቶች ግባር አስኳል በመሆን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ወሳኙን ሚና ሲጫወት ቆይቷል።
ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ ወሳኝ ፓርቲነቱ ያበቃው በውስጡ በተፈጠረ ለውጥ በ2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው። በዚህም በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ የነበረውን የበላይነት አጥቷል።
በኢህአዴግ ውስጥ የህወሓት የበላይነት አብቆቶ በግንባሩ ውስጥ የነበረው ሚና በተዳከመበት ጊዜ በህወሓት መሪዎች እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተካርሮ ወደ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።
ብዙም ሳይቆይ በህወሓት ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት በትግራይ ውስጥ ተካሄደ። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን በሽብርተኝነት ፈርጆ ሕገወጥ ቡድን አደረገው።
ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የሽብር ቡድንነት ፍረጃው የተነሳለት ቢሆንም ሕጋዊ ዕውቅናው አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። ህወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ሕጋዊ ዕውቅናውን አጥቷል።
ህወሓት ሕጋዊ ዕውቅና ባይኖረውም በፌደራል መንግሥቱ የተመሠረተው ጊዜያዊ አስተዳደር በቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ሆኖ ቆይቶ ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ህወሓት በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ የክልሉን ሥልጣና ተቆጣጥሯል። ይህም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ለወራት በቆየ ፍጥጫ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ባለፉት ወራት የፌደራል መንግሥቱን የሚቆጣጠረውን ብልጽግናን ለማስወገድ መዘጋጀቱን ሲገልጽ ቆይቶ አሁን ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመሆን ዓላማውን ለማሳካት ጥምረት መፍጠሩን ገልጿል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተገንጥሎ የወጣ ታጣቂ ቡድን ሲሆን፣ ኦነግ ከቀደምት የኢትዮጵያ በብሔር ከተደራጁ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች አንዱ ሲሆን፣ የመጀመሪያ የኦሮሞ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባል ነው።
ኦነግ የትጥቅ እንቅስቃሴ የጀመረው የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሳለ ነው። ኦነግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቶ በደርግ መውደቂያ አቅራቢያ ከኤርትራው ህግሓኤ እና ከህወሓት ጋር ግንባ ር በመፍጠር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም እና አሁን ያለው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በማዘጋጀት ጉልህ ሚና ነበረው።
ከደርግ መውደቅ በኋላ የመጀመሪያው ምርጫ ሊካሄድ ሲቃረብ ከህወሓት ጋር ፉክክር እና አለመግባባት ውስጥ በመግባቱ ኦነግ ታጣቂዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ አመራሮቹም ከአገር ተስድደው መቀመጫቸውን አሥመራ በማድረግ የትጥቅ እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለዋል።
በስደት እና በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆየው ኦነግ በአመራሩ መካከል በተለያዩ ጊዜያት አለመግባባቶች ተፈጥረው ከግንባሩ የወጡ መሪዎቹ ሌላ ድርጅት አቋቁመዋል።
በዳዉድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ለዓመታት በኤርትራ ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ አመራሩን እና በኤርትራ የነበሩትን ታጣቂዎቹን ወደ አገር ቤት መልሶ ነበር።
ሆኖም በግምባሩ የፖለቲካ እና የወታደራዊ አመራሮች መካከል በተከሰተ አለመግባባት አንደኛው ክንፍ 'የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት' በሚል የሚታወቀውን መንግሥት 'ሸኔ' የሚለውን ቡድን ለይቶ መንቀሳቀስ ጀመረ።
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ወቅትም ይህ በመሮ ድሪባ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) የፌደራል መንግሥቱን ለመጣል ብዙም ያልዘለቀ ጥምረት ከህወሓት ጋር መሥርቶ እንደነበረ ይታወሳል።
ቡድኑ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈፀም የሚከሰስ ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጇል።
ጃል መሮ በሚል ስም የሚታወቀው መሮ ድሪባ የሚመራው ታጣቂ ቡድን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ በማድረግ፣ እገታዎችን በመፈፀም እና የአካባቢ ባለሥልጣናትን በመግደልም ይከሰሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሚቀርቡበትን ክሶች በተደጋጋሚ አስተባብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)
ፋኖ በአማርኛ ቋንቋ የሆነ ምክንያት አስገድዷቸው ትግል ለሚያደርጉ ወጣቶች የሚሰጥ ስያሜ ነው። ከ1930ዎቹ አንስቶ የጣልያን ወራሪዎችን ለመዋጋት ፈቃደኛ ተዋጊዎች የአፄ ኃይለሥላሴን ጦር ከተቀላቀሉ በኋላ ስሙ ይበልጥ ይታወቃል።
በኢህአዴግ የሚመራው የፌደራል መንግሥትን ያዳከመው ሕዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተጠናከረበት ጊዜ መታየት የጀመረው የፋኖ እንቅስቃሴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ተጠናክሯል።
በተለይ በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ አማራ ክልል ሲዛመት፣ የትግራይ ኃይሎችን ግስጋሴ ለመግታት በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች በክልሉ አስተደዳር ጭምር እየተደራጁ ይንቀሳቀሱ ነበር።
በትክክል የትኛው የፋኖ ቡድን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የፌደራሉ እና የክልል ኃይሎች ወደ ትግራይ ዘልቀው በገቡበት ጊዜ የፋኖ ኃይሎችም እንደነበሩ እና በደሎችን ስለመፈጸማቸው በመብት ተቋማት ሳይቀር ሲገልጽ ነበር።
አሁን ያለው የፋኖ እንቅስቃሴ በይፋ የወጣው ግን የትግራይ ጦርነት አብቅቶ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና በሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ እንዲካተቱ እርምጃ በወሰደበት ጊዜ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመወገን የትግራይ ኃይሎችን ከወጋ በኋላ መንግሥት ቡድኑን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑ "የመካድ እና ለጥቃት ተጋላጭ" እንዳደረገው በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱን በመቃወም ወደ ጫካ ገብቷል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ስር የነበሩ እና ትጥቅ እንዲፈቱ መታዘዛቸውን የተቃወሙ በርካታ አባላት ከነትጥቃቸው የፋኖን እንቅስቃሴ መቀላቀላቸው በወቅቱ ተዘግቧል።
የፋኖ ቡድኖች በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች የተደራጁ ሲሆኑ አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሁሉም በራሱ አመራር ስር ሆነው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
የጎጃም፣ የወሎ፣ የጎንደር እና የሸዋ ፋኖ በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂ ቡድኖች በቅርቡ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በሚል አንድ ቡድን መመሥረቱን ገልጸዋል።
ቡድኑ ወጥ የሆነ አደረጃጀት እና አመራር ባይኖረውም በቅርቡ ሁሉንም ቡድኖች ወደ አንድ ጥላ ያመጣ ነው የተባለውን ንቅናቄ የሚመራው አሁን የጥምረቱ ሰብሳቢ በተባለው በዘመነ ካሴ ነው።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ክፍል ከ30 ዓመታት በላይ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል።
ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ያደርጉ ከነበሩ አማጺ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ኦብነግ የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 1984 ነበር።
አማፂው አብነግ የኦጋዴን ሕዝብ ብሎ የሚጠራውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር በፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።
ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ የሽብርተኝነት ፍረጃው ተነስቶለታል።
ኦብነግ የትጥቅ እንቅስቃሴውን በመተው ወደ አገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ ፖለቲካ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
ኦብነግ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ጋር በመዋሃድ የሶማሊ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን መሥርተው ነበር።
ነገር ግን በፓርቲው ውስጥ ከፍፍል ተፈጥሮ የተወሰነው ቡድን በአገር ውስጥ ሲቀር የተቀረው ወገን ደግሞ ወደ ስደት ተመልሶ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ እያካሄደ ነው።
አሁን መንግሥትን ለመጣል ጥምረት መፍጠራቸው ከተገለጸው ቡድኖች መካከልም አንዱ የሆነው ክንፍ ግንባሩን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አብዲራህማን ማህዲ ናቸው።
የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር
የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር "አጉጉሞ" በመባል ይታወቃል። አጉጉሞ በአፋርኛ ቋንቋ ትርጉሙ 'አብዮት' እንደማለት ነው።
ግንባሩ የአፋር ሕዝብን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ መብቶች ለማስከበር የተቋቋመ የፖለቲካ እና ትጥቅ ትግል የሚያደርግ ቡድን መሆኑን ይናገራል።
ድርጅቱ የአፋርን ሕዝብ የራሱን መብት በራሱ የመወሰን መብት፣ የክልሉን ሃብት ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ውክልና እንዲጠናከር እንደሚታገል ይገልጻል።
በአፋር ፖለቲካ ውስጥ ተቃዋሚ ኃይል በመሆንም ይታወቃል።
የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀስ እና በዋናነት የበርታ ብሔረሰብ አባላትን መነሻ ያደረገ ታጣቂ ቡድን ነው።
ቡድኑ በክልሉ የሚገኙ ተወላጆች መብት እንዲከበር እና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ እንደሚታገል ይገልጻል።
ክልሉ ከደርግ አስተደዳር መውደቅ ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በትጥቅ ትግል እና በፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ ቆይቷል።
ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከክልሉ እና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሰላም ስምምነቶችን ተፈራርሞ ነበር።
ሆኖም በክልሉ በተደጋጋሚ በሚፈፀሙ ጥቃቶች እና ግድያዎች ይከሰሳል። አሁን ደግሞ መንግሥትን ለመጣል ጥምረት የፈጠሩ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ተቀላቅሏል።
በዚያው ክልል የሚንቀሳቀሰው የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ጥምረቱን ከተቀላቀሉት ታጣቂ ቡድኖች መካከል ይገኝበታል።
ይህም ጥምረቱ ውስጥ ተካትተዋል ከተባሉት ሰባት ቡድኖች መካከል ሁለቱ ከቤኒሻንጉል የመጡ እንዲሆን አድርጓል።













