የፊፋ ፕሬዝዳንት በአወዛጋቢው እቅዳቸው ምክንያት ለተፈጠሩ "ስህተቶች" ይቅርታ ጠየቁ

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ለመጀመሪያ ጊዜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ከ10 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ባቀረቡት አወዛጋቢ እቅድ ላይ ለተፈጠሩ "ስህተቶች" ይቅርታ ጠየቁ።

ይሁን እንጂ ኢንፋንቲኖ በሞሮኮ በተካሄደው የአመራሮች ስብሰባ ላይ የከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎችን ድጋፍ በማግኘታቸው በፊፋ ፕሬዝዳንትነት ይቀጥላሉ።

ውድቅ እንዲሆን በተደረገው እቅድ ምክንያት ከፍተኛ ወቀሳ የቀረበባቸው ፕሬዝዳንቱ፤ ትናንት ረቡዕ የፊፋ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን የሞስኮ ዋና ከተማ ራባት ውስጥ በሚገኘው የፊፋ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት ሰብስበዋል።

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪው ፊፋ ከስብሰባው መጠናቀቅ አራት ሰዓታት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ ለፕሬዝዳንቱ ያለውን ድጋፍ ገልጿል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበራት ህብረት (ዩኤፋኤ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ በፕሬዝዳንቱ ኢንፋንቲኖ ላይ እምነት ማጣቱን አስታውቆ ነበር።

የፊፋን ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስተዳድር እና የግል ባለሀብቶች ድርሻ የሚይዙበት 'ፊፋ ፎርዋርድ ኢንተርፕራይዝ' የሚል ኩባንያ ለማቋቋም የቀረበውን እቅድም "በጀርባ የተፈጸመ እና የተሸፈነ ስምምነት" ሲል ተቃውሞታል።

ይህ እቅድ ውድቅ ካልተደረገም አባል አገራቱ ፊፋ በሚያዘጋጃቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንደማይሳተፉ ገልጿል። የሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስን የሚያስተዳድረው ኮንካካፍም እቅዱ ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዞ ነበር።

ኢንፋንቲኖ ከሚመሩት ፊፋ ውስጥም በርካታ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የፊፋ ዋና ጸሐፊ ማቲያስ ግራፍስትሮም ማክሰኞ ዕለት ለተቋሙ ሰራተኞች በላኩት የውስጥ ማስታወሻ፣ ሁኔታውን "አሳዛኝ እና ወቀሳ የሚያስነሳ" ሲሉ ገልጸውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከትናንቱ ስብሰባ በኋላ ግን ዋና ጸሐፊው እና ሌሎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለኢንፋንቲኖ ፕሬዝዳንትነት "ያላቸውን ሙሉ ድጋፋ እንደሚያረጋግጡ" አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ኢንፋንቲኖ እና ዋና ጸሐፊው ግራፍስትሮም ለፊፋ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ለምክር ቤቱ እንዲሁም ለ211 አባል አገራት በላኩት ደብዳቤ ለተፈጠሩት ስህተቶች "ከልብ የመነጨ ይቅርታ" ጠይቀዋል።

ይህ አይነቱ ጉዳይ "በድጋሚ እንደማይፈጠርም ቃል መግባታቸውን" ቢቢሲ ከደብዳቤው ተመልክቷል።

ሁለቱ አመራሮች በራባት ከተማ ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ውድድር ላይ ታድመው ታይተዋል።

ኢንፋንቲኖ፤ የወንዶች እና ሴቶች የዓለም ዋንጫን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የግል ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት እንዲኖርባቸው የሚያድርውን እቅድ ለሚደግፉ የፊፋ አባል አገራት 40 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።

ፊፋ በረቡዕ ዕለቱ ስብሰባ ላይ ሊቋቋመው በታቀደው ኩባንያ ዙሪያ "ስህተቶች" መፈጠራቸውን "እውቅና" ሰጥቶታል። የፊፋ ምክር ቤት እና አባል አገራት "ከሂደቱ እንደተገለሉ እንዲሰማቸው ማድረግ ታስቦ የተደረገ እንዳልሆነ እና ሂደቱ በተለየ መንገድ መያዝ እንደነበረበት" አምኗል።

የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካሉ "እቅዱ ወደ መገናኛ ብዙኃን ሾልኮ ከወጣ በኋላ ስህተቶች መፈጸማቸውን" አክሏል። የኢንፋንቲኖን እቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው የዩናይትድ ኪንግደሙ ጋዜጣ 'ዘ ታይምስ' ነበር።

ይሁን እንጂ ፊፋ ከአሁን ወዲህ በተቋሙ "መልካም አስተዳደር፣ ሂደቶች ላይ የሚሰነዘሩ ማንኛውም እንደማይታገስ እንዲሁም ስሙን እና ዝናውን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንደሚወስድ" አስታውቋል።

ተቋሙ ይህንን ከማለቱ አስቀድሞ 'ዘ ታይምስ ጋዜጣ' ባወጣው ዘገባ ኢንፋንቲኖ ሞሮኮ ድጋፏን የምትሰጣቸው ከሆነ በምላሹ የ2030 ዓለም ዋንጫን የፍጻሜ ጨዋታን የማስተናገድ እድልን እንደሚሰጧት ቃል እንደገቡ አስነብቦ ነበር።

ፊፋ ክሱን "ሐሰተኛ እና አሳሳች" ሲል ውድቅ አድርጎታል። ሞሮኮ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመሆን የምታዘጋጀው ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ የሚካሄድበት አገር "ሂደቱን ጠብቆ" ውሳኔ እንደሚያገኝ ገልጿል።