አሜሪካን እየተፋለመች ያለችው ኢራን ከጦርነቱ ለመውጣት ምን አማራጭ አላት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሆርሙዝ ወሽመጥ ቁጥጥር ላይ የበላይነት ለመያዝ ከአሜሪካ ጋር ግብግብ ገጥመው የቆዩት የኢራን መሪዎች አሁን ሦስት አማራጮች ያሏቸው ይመስላል። የትኛውም አማራጭ ግን በግልፅ ወደ ድል አድራጊነት የሚመራ አይደለም።
የመጀመሪያው አማራጭ አሜሪካ ከምትፈልጋቸው ነገሮች ውስጥ አብዛኞቹን መቀበል ነው። ከአሜሪካ ፍላጎቶች አንዱ፣ በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም በማቆም በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከብ ጉዞ ነፃ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ዋስትና መስጠት ነው።
ኢራን ያላትን የበለጸገ ዩራኒየም ክምችት አሳልፋ ትስጥ ወይም ይበረዝ የሚለውም የአሜሪካ ጥያቄ ነው። ኢራን ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኤነርጂ ተቆጣጣሪ ተቋም ለሚያደርገው ጥልቅ ምርመራም ፈቃደኛ እንድትሆን ፍላጎት አላት።
በምላሹም ቴህራን በወደቦቿ ላይ የተጣለው የአሜሪካ የባሕር ኃይል እገዳ ይነሳላታል። የማዕቀብ እፎይታ እና ከተጨማሪ ጥቃቶች እረፍት ታገኛለች።
ምናልባትም ይህ አማራጭ ከሌሎቹ አንጻር አነስተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል፤ በፖለቲካው ረገድ ግን የሚጠይቀው ዋጋ የበለጠ ነው።
ኢራን ይህ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ፣ ሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚሳዔሎቿ፣ ከቀጣናዊ አጋሮቿ ወይም ከኒውክሌር ፕሮግራሟ የበለጠ ውጤታማ የመከላከያ እና የመደራደሪያ አቅም እንደሆናት በርካታ ኢራናውያን ያምናሉ።
አሁን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ላይ የሚኖራት የአስተዳዳሪነት ሚና ዕውቅና ሳይሰጠው ወሽመጡን የምትከፍት ከሆነ፤ ይህንን አቅሟን አሳልፎ መስጠት ይሆንባታል።
እስላማዊቷ ሪፐብሊክ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ በፍጥነት ተጽዕኖ በማሳደር ጠላቶቿ ግዛቷ ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ምላሽ መስጠት እንደምትችል ለመጀመሪያ ጊዜ አሳይታለች።
በሌላ በኩል፣ ኢራን ለረጅም ጊዜያት የኒውክሌር ፕሮግራሟን ተገድዳ የማትተወው መብቷ መሆኑን በግልጽ አሳውቃለች።
ለወራት ከቆየ ጥቃት በኋላ ይህንን የኒውክሌር እንቅስቃሴ በጥብቅ የሚገድብን ጥያቄ መቀበል፣ በአገሪቱ የሚገኙ አክራሪዎች 'የአሜሪካ ወታደራዊ ጫና ሠርቷል' የሚል አቋም እንዲይዙ ዕድል ይሰጣል።
የኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም ላይ እንዲሁም ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ ከኢራቅ የሺዓ ቡድኖች እና ከየመን ሁቲዎች ጋር ስላላ ግንኙነት ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲነሱ በሩን ሊከፍት ይችላል።
ኢራን ያላት ሁለተኛው አማራጭ፤ ግጭቱን ማባባስ ነው። ኢራን በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች፣ በመርከብ ጉዞዎች እና በባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች ልታጠናክር ትችለላች።
ይህንን ማድረጓ፣ የሚያስከትለው የነዳጅ ዋጋ ንረት እንዲሁም መጠነ ሠፊ የአቅርቦት መስተጓጎል አሜሪካ እና አጋሮቿን ለድርድር እንዲቀመጡ ያስገድዳቸዋል የሚል ግምገማ ልትይዝ ትችላለች።
እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ግን ከፍተኛ ወታደራዊ አደጋንም ይጋርጣል። የበርታ ሰዎች ሕይወትን የሚቀጥፍ ወይም በባሕረ ሰላጤው መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ፣ የኢራን ጎረቤቶች ይበልጥ በቀጥታ ግጭቱ ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ይህ ደግሞ ኢራን ሰፊ ጥምረትን እንድትጋፈጥ ያደርጋታል።
ሦስተኛው አማራጭ አሁን ያለውን አለመረጋጋት ባለበት ማቆየት ነው። ይህ አማራጭ፣ ኢራን የመደራደሪያ አቅሟን ለማጠናከር በሚያስችል ደረጃ ብቻ በመርከቦች ጉዞ እና በኤነርጂ ገበያው ላይ ተጽዕኖ እንድታሳደር፤ ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት እንድትመለስ የሚያደርግ እርምጃ እንዳትወስድ የሚያደርግ ነው።
የእስላማዊቷ ሪፐብሊክ መዋቅራዊ አመለካከት ለዚህ አማራጭ የሚስማማ ይመስለል። ኢራን ጠላቷ ላለመዋጋት አስኪወስን ድረስ ጦርነቱ ውስጥ መቆየት ከቻለች፣ ጠንካራ ጠላት ላይ ድል መቀናጀት አያስፈልጋትም።
ጦርነቱን ተቋቁሞ መትረፍ ብቻውን እንደ ድል ሊቆጠር ይችላል። ነገር ግን የተጣሉባት ማዕቀቦች፣ ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት እና የዋጋ ግሽበት አገር ውስጥ ያለውን ጫና እያባባሱት ነው።
ጊዜ ሲሄድ፣ ተቃርኖው እየጎላ መምጣቱ አይቀርም። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደ መሣሪያ መጠቀም በቀጠለች ቁጥር፤ አገራት ነዳጅ እና ሌሎችን ምርቶችን ከቀጣናው ማስወጣት የሚችሉባቸው አዳዲስ መንገዶችን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የወሽመጡን ተጽዕኖ አሳዳሪነት ይቀንሳል።
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ይህንን ተቃርኖ ከዚህ ቀደም አንስተውታል። የሆርሙዝ ዋጋ የሚተመነው በወሸመጡ በሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በመጨመር እንጂ በመቀነስ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የባሕር መተላለፊያ ሁሌም ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ከሆነ፣ መርከቦች ኢራን የማትደርስበት አማራጮች እንዲፈልጉ ያበረታታል።

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ውሳኔውን የሚያስተላልፈው ማነው?
ጉዳዩን ይበልጥ ከሚያወሳስቡ ነገሮች አንዱ የኢራን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ምን አይነት ቅርጽ አለው የሚለው ላይ እርግጠኝት አለመኖሩ ነው።
በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት በተገደሉት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የሥልጣን ዘመን በምርጫ በመጡ ፖለቲከኞች፣ በሃይማኖታዊ ተቋማት እና በእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኙት በጠቅላይ መሪው ነበር።
ለወራት ጦርነት ውስጥ በቆየችው ኢራን እና በኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ አዲስ አስተዳደር ውስጥ ግን ይህ የኃይል ሚዛን በግልጽ አይታይም።
ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን እና ዲፕሎማቶቻቸው የኢኮኖሚ ጫናው እንዲቃለል እና መረጋጋትን እንዲመለስ ሲባል ስምምነት መደረጉን ሊደግፉ ይችላሉ።
ፓርላማ ውስጥ የሚገኙ አክረሪዎች፣ ኃይለኛ በምርጫ ያልመጡ ተቋማት እና ወግ አጥባዊ መገናኝ ብዙኃን ደግሞ በተቃራኒው፣ ከኢራን ዋነኛ አቋሞች ፈቀቅ ማለት የእስላማዊቷ ሪፐብሊክን ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረቶች ያናጋል፤ እንዲሁም ከዋነኛ ደጋፊዎቿ ይነጥላታል የሚል ፍርሃት ይገባቸው ይሆናል።
ትልቁ ጥያቄ የሚነሳው ከታጣቂ ኃይሎች በተለይም ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ጋር በተያያዘ ነው። አብዮታው ዘብ በኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም፣ ቀጣናዊ አጋርነቶቿ እና ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በምትከተለው ስትራቴጂ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው።
የአብዮታዊ ዘቡ የአዛዦች ግጭት መቀጠልን ወይስ ድርድር ማድረግን የተመለከቱ ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ወቅት ግን ምን ያህል ጫና ማሳደር ይችላሉ የሚለው ግልጽ አይደለም።
ቴህራን ያሏት ሦስት አማራጮች በሥርዓቱ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚያስከትሉት ዋጋ አንድ ዓይነት አይደለም። ተራማጅ አካላት ስምምነት ላይ መድረስን ሊመርጡ ይችላሉ።
የአክራሪዎች ምርጫ ሁኔታውን መቋቋም ሊሆን ይችላል። ሌሎች ወታደራዊ አዛዦች ደግሞ ግጭቱን ማባባስ የኢራንን የድርድር አቅም ያጠናክራል የሚል ግምገማ ሊኖራቸው ይችላል።
ስለዚህ ጥያቄው 'የትኛው አካል ምርጫውን የመወሰን ሥልጣን አለው?' የሚለው ጭምር እንጂ 'ኢራን የትኛውን መንገድ ትምረጥ?' የሚለው ብቻ አይደለም።
ኢራናውያን ምን ይላሉ?
የኢራን አመራር ሁኔታውን መቋቋም በማለት የሚያቀርበው ገለጻ፤ ዳፋው የሚደርስባቸው ነዋሪዎች ከሚገልጹት ጋር እጅግ የተለያየ ነው።
ኢራን እና አሜሪካ ባለፈው ሰኔ ላይ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ማስቆም፣ ሆርሙዝን መክፈት እንዲሁም በ60 ቀናት ውስጥ ጦርነቱ የሚቋጭበት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በር የሚከፍት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ነበር።
ስምምነቱ ከተፈጸመ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ግን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተኩስ አቁሙ "ማብቃቱን" አውጀዋል። ትራምፕ ይህንን ያሉት ኢራን በሆርሙዝ ይጓዙ የነበሩ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ፤ አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች በኋላ ነው።
አንዲት የኢራን ነዋሪ ውጊያው እንደገና ሲጀመር "እጅግ፣ እጅግ ማዘኗን" ለቢቢሲ ፐርሺያ ተናግራለች።
የመግባቢያ ስምምቱ ሁለቱ ወገኖች የቀሩ የግጭት መስንዔዎችን እንዲፈቱ እና መረጋጋት እንዲመለስ ጊዜ ይሰጣል የሚል ተስፋ ነበራት። አሁን ግን የሚያሳስባት የሚደርሰው የመሠረተ ልማት ውድመት እንዲሁም የሲቪሎች እና ወታደሮች ሞት ነው።
በኢራን ሥርዓት አክራሪዎች አውዳሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረጋቸውን በማንሳት የምትከሰው ይህቺ ነዋሪ፤ በውጭ አገር የሚገኙ የተቃዋሚዎችም ጦርነትን አበረታትተዋል በማለት ትወቅሳለች።
ሌላ የቴህራን ነዋሪ ደግሞ ትሠራበት የነበረው የውጭ ኩባንያ በመዘጋቱ የዶክትሬት ዲግሪ እና የ17 ዓመት ልምድ እያላት ላለፉት ስድስት ወራት ሥራ አጥ መሆኗን ታስረዳለች።
"ማንም ምን እንደሚፈጠር ስለማያውቅ ሰው የሚቀጥር የለም" ትላለች። የዋጋ ንረት መኖሩን፣ ኤሌክትሪክ እና ውሃ እንደሚቋረጥ፣ ዝርፊያ መበራከቱን እንዲሁም አልፎ አልፎ በምሽት የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ትናገራለች።
ሁለቱ ነዋሪዎች የሚያቀርቡት ገለጻ፤ ወደ አንድ ፖለቲካዊ ድምዳሜ የሚያደርሱ አይደሉም። በውጭ አገራት ጥቃት መፈጸሙ የእስላማዊው ሪፐብሊክ ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች እንኳ በአሜሪካ እና በእስራኤል እንዲናደዱ ሊያደርግ ይችላል።
በሌላ በኩልም ግን በትግል ስም ነዋሪዎች መቋጫ የሌለው ችግርን ተቋቁመው እንዲቆዩ መጠየቅም ቅሬታን ይፈጥራል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም በተመሳሳይ ከባድ ምርጫዎች ፊታቸው ተደቅነዋል።
ያላቸው አማራጭ ጦርነቱን ማስፋፋት፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ማስቀጠል ወይም ኢራን ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የተገደበ የሲቪል ኒውክሌር ፕሮግራም እንዲኖራት የሚፈቅድን ስምምነት መቀበል ነው።
ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ የትኛውም በግልጽ ለድል አድራጊነት የሚያበቃ አይደለም።
ጥቃቶች እየደረሱ፥ የማሸማገል የጥረቶች እየተደረጉ እና ጊዜያዊ ተኩስ አቁሞች እየተደረሱ ይህ ግጭት ለወራት ሊቀጥል ይችላል።
ወሳኙ ጥያቄ፣ የኢራን መሪዎች ሙሉ ጦርነትን ሳይቀሰቅሱ፣ አዲስ ሕዝባዊ አመፅ ሳይነሳባቸው ወይም ሆርሙዝ ወሽመጥን ወሳኝነት የሚቀንሱ ሌሎች አማራጭ ሳይገኙ ለምን ያህል ጊዜ አሁን ያለውን ሁኔታ ማስቀጠል ይችላሉ የሚለው ነው።












