ግራ ዘመሙ ዲሞክራት አብዱል ኢል-ሳይድ በሚችጋን ግዛት ቅድመ ምርጫ አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ አብዱል ኢል-ሳይድ በሚችጋን ግዛት ዲሞክራቲክ ፓርቲን ለመወከል በተደረገው ቅድመ ምርጫ አሸነፉ።
ይህም የዲሞክራት ፓርቲ የወደፊት አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ክፍፍል ሊፈጥር እንደሚችል ተገምቷል።
የቀድሞ የኅብረተሰብ ጤና ኃላፊ እና የሕዝብ እንደራሴ የነበሩት ለዘብተኛ ዲሞክራት ሄይሊ ስቲቨንስን በጠባብ ድምጽ ልዩነት አሸንፈዋል።
አብዱል ኢል-ሳይድ የሚችጋንን ቅድመ ምርጫ በማሸነፋቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲው ይፋዊ ዕጩ ሆነዋል።
በቀጣይ ከሪፐብሊካን ዕጩ ጋር ተወዳድረው ካሸነፉ የተወካዮች ምክር ቤት ይገባሉ።
ምርጫውን ሲያሸንፉ "መሐመድ ዓሊ እንዳለው 'ዓለምን አናውጠናል' " ሲሉ መናገራቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።
ዝነኛው ቦክሰኛ መሐመድ ዓሊ ይህንን ያለው በ1964 ሶኒ ሊስተንን ሲያሸንፍ ነበር።
አል-ሳይድ በቀጣይ ምክር ቤት ለመግባት የሚፎካከሩት ከሪፐብሊካን እጩ እና የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ማይክ ሮጀርስ ጋር ነው።
ከተመረጡ በአሜሪካ ሴኔት የመጀመሪያው ሙስሊም እንደራሴ ይሆናሉ።
"ንቅናቄው ገንዘብን ከፖለቲካ የማላቀቅ ነው። ገንዘቡን በኪሳችሁ አድርጋችሁ ጠቅላላ የሕክምና ሽፋን (ሜዲኬር) ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን አድርጉ" ሲሉ ንግግር አድርገዋል።
በምርጫው የተሸነፉት ሄይሊ "ኢል-ሳይድ በሴኔት የዲሞክራት እንደራሴ ሆኖ ለመወዳደር የሚያስችለውን ምርጫ ስላሸነፍክ እንኳን ደስ አለህ" ብለዋል።
"ኢል-ሳይድ ሐኪም፣ የማኅበረሰብ ጤና ኃላፊ፣ የሮደስ ምሁር እና ታማኝ የሚችጋን ሰው ነው። ከማይክ ሮጀርስ ጋር ለሚኖረው ፉክክር ሙሉ ድጋፌን እሰጠዋለሁ" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኅዳር ላይ በሚካሄደው የአጋማሽ ምርጫ ለሁለት ዓመት በሴኔት ውክልና የሚኖረው ፖለቲከኛ ይለያል።
ትራምፕ የሚችጋኑ የምርጫ ውጤት "ለሪፐብሊካን ፓርቲ ትልቅ ዜና ነው" ብለዋል።
በትሩዝ ሶሻል ማኅባራዊ ሚዲያቸው "ዲሞክራቶች ፖለቲካቸው ከዚህም በላይ እያበደ ይሄዳል" ሲሉ ጽፈዋል።
የምርጫው ውጤት ይፋ ከመደረጉ በፊት ኢል-ሳይድ ባደረጉት ንግግር "ምንም ቢፈጠር አንድነታችንን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብን። ሪፐብሊካኑ ማይክ ሮጀርስ ሴኔት መግባት የለበትም" ብለዋል።
ኢል-ሳይድ እንደ በርኒ ሳንደርስ እና አሌክሳንድ ኦካዝዮ-ኮርቴዝ ካሉ ግራ ዘመም ፖለቲከኞች ድጋፍ አግኝተዋል።
ብሔራዊ የሕክምና ማዕቀፍ መዘርጋት እና የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ማስወገድን ጨምሮ ሌሎችም ተራማጅ ሐሳቦችን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አስተጋብተዋል።
በምርጫው የተሸነፉት ሄይሊ ስቲቨንስን አማካዩን መንገድ በመከተል ይታወቃሉ። ከሚችጋን አገረ ገዢ ግሪትቸን ዊትመር እና ከቀድሞው የሚችጋን የሕዝብ እንደራሴ ግሬይ ፒተርስ ድጋፍ አግኝተው ነበር።
እጩዎቹ ካልተስማሙበት ነጥብ አንዱ የእስራኤል ጉዳይ ነው።
ኢል-ሳይድ አሜሪካ እስራኤልን መደገፍን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ጣልቃ ገብነት አይደግፉም።
ሄይሊ በበኩላቸው የእስራኤል ደጋፊ ናቸው።
ኢል-ሳይድ በአሜሪካ እና በእስራኤል ግንኙነት ላይ ያላቸውን አቋም ካስታወቁ በኋላ ከሚችጋን የአይሁድ ማኅበረሰብ ድጋፍም ነቀፌታም ተሰጥቷቸዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው የፀረ ሴማዊነትን ጉዳይ እንደ አዲስ ቢያነሱም፣ ኢል-ሳይድ ይህ እውነተኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"ከአይሁዳዊ እህቶቼ እና ወንድሞቼ ጎን እቆማለሁ። ፀረ ሴማዊነትን እያወገዝን ጎን ለጎን ሰዎች አንድነት እንዲያሳዩ ማድረግ እንችላለን፤ ስለሁሉም ሰው ቁስል መናገርም ይቻላል" ብለዋል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት ሚቺጋን ቁልፍ ከሆኑ ውጤት ለዋጭ ግዛቶች አንዷ ናት። በሚችጋን ድምጽ ወደ ዲሞክራቶች ወይም ሪፐብሊካኖች ሊያጋድል የሚችልበት እኩል ዕድል መኖሩ በምርጫ ወቅት ቁልፍ ግዛት አድርጓታል።















