ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሪ ተወልደ ገብረማሪያም የኤር ኢንዲያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ
የሕንድ ሁለተኛው ትልቁ አየር መንገድ የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፋሚ ተወልደ ወልደማሪያምን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አድርጎ መሾሙን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአስር ዓመት በላይ የመሩት እና አየር መንገዱን ከአፍሪካ ግዙፉ እንዲሁም ቀዳሚው በማድረግ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ በማድረስ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያካሄደውን የባለ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ማስፋፋት እና ባለ ብዙ አውሮፕላኖች ባለቤት እንዲሆን ያስቻሉ መሆናቸው ይነገራል።
አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ላይ ብቻ ሳይሆን ፈተናዎች በገጠሙት ጊዜ ተቋሙ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ በስኬት እንዲያልፍ አድርገዋል።
በተለይም በአየር መንገዱ ታሪክ ውስጥ ከባድ በነበሩት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በርካታ አየር መንገዶች ለኪሳራ እና ከሥራ ውጪ ለመሆን ሲገደዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሥራው ላይ ለውጥ በማድረግ ትርፋማ ለመሆን አስችለውታል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር ተከስክሶ ሁሉም መንገደኞች እና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ከሞቱበት የቦይን 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ወቅት የአየር መንገዱን ጥንካሬ ዝና ጠብቀው ከቀውሱ ለመውጣት መቻላቸው ከሚጠቀሱላችው ስኬቶቻቸው መካከል ናቸው።
አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አሁን የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ቦታ የሚረከቡት ኤር ኢንዲያ አየር መንገድ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት አውሮፕላኑ ተከስክሶ 260 መንገደኞች ከሞቱ በኋላ በከባድ ፈተና ውስጥ ይገኛል።
አየር መንገዱ በተጨማሪም ከፍተኛ የገንዘብ እና የሥራውን የማካሄድ ፈተና የገጠመው ሲሆን፣ ከደረሰበት አደጋ ተያይዞ በአቪየሽን ተቆጣጣሪ አካላት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው።
አቶ ተወልደ የመሪነት ኃላፊነቱን የሚረከቡት ኤር ኢንዲያ በሚያጓጉዛቸው መንገደኞች ብዛት በሕንድ ውስጥ ካሉ አየር መንገዶች ሁለተኛው ትልቁ አየር መንገድ ነው።
ታታ ግሩፕ 75 በመቶ የባለቤትንት ድርሻውን እንዲሁም የሴንጋፖር አየር መንገድ 25 ባለቤትነት ያለው ወደ 200 የሚጠጉ አውሮፕላኖች እና ከ31 ሺህ በላይ ሠራተኞች የሚሰስተደድረው አየር መንገዱ ወደ 90 ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች አሉት።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት በጥር 2003 ዓ.ም. ነበረ።
አቶ ተወልደ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ዘላቂነት ባለው ትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ የአማካሪዎች ቡድን አባል ሆነው ሠርተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አባል በሆነበት የስታር አሊያንስ ዋና የቦርድ አባል፣ የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማኅበር (አይኤቲኤ) የቦርድ አባል በተጨማሪም የአፍሪካ የአየር መንገዶች ማኅበር (ኤኤፍአርኤኤ) የዋና ኮሚቴ አባል በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ተወልደ የአፍሪካ የጉዞ ማኅበር (ኤቲኤ) የቦርድ አባል እና የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት (ኢቲኦ) የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልም ነበሩ።
አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ባገለገሉባቸው በርካታ ዓመታት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ከሽልማቶቹ መካከል የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ምርጥ የአፍሪካ የቢዝነስ መሪ፣ የቀጣናዊ የአየር መንገድ አመራር ሽልማት እንዲሁም ምርጥ ፆታን ያማከለ ሥራ አስፈፃሚ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከዩናይትድ ኪንግደም ኦፕን ዩኒቨርስቲ በንግድ አስተዳደር ያገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬትም ተበርክቶላቸዋል።
አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ከአስር ዓመት በላይ በስኬት የመሩትን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የለቀቁት በጤና ሁኔታን በምክንያት ጠቅሰው በ2014 ዓ.ም. ነበር።