የትግራይ ኃይሎች የመቀለ አውሮፕላን ማረፊያን "መቆጣጠራቸው" ከተሰማ በኋላ ወደ ክልሉ የሚደረጉ በረራዎች ተቋረጡ

የአሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Geez media

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የትግራይ ኃይሎች ዛሬ ማለዳ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸው ከተሰማ በኋላ ወደ ትግራይ በረራዎች ተቋረጡ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን በረራ "ለጊዜው መቋረጡን" አስታውቋል።

ህወሓት በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ከሥልጣን በማስወገድ የክልሉን አመራርነት ከተቆጣጠረ በኋላ ላለፉት ወራት በክልሉ ውስጥ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል።

እንዲሁም አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ በተጨማሪ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።

ወደ ክልሉ የሚደረገው በረራ የተቋረጠው ህወሓትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች ረቡዕ ማለዳ የትግራይ ኃይሎች በመቀለ የሚገኘውን የአሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ መጣጠራቸውን ገልጸዋል።

የፈረንሳይ የዜና ወኪል እንዲሁ ምንጮችን ጠቅሶ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ መዲና የሚገኘውን ዓለም አቀፉን አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸውን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በትግራይ ክልል በሚገኙ ሦስት ከተሞች የሚያደርገውን በረራ ከረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ማቋረጡን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው በክልሉ "ባለው ወቅታዊ ሁኔታ" ምክንያት ከመግለጽ ውጪ በረራውን ለማቋረጥ ያስገደዱትን ምክንያቶች በመግለጫው ላይ አልጠቀሰም።

የቢቢሲ ምንጮች ዛሬ ማለዳ ላይ ወደ መቀለ፣ አክሱም እና ሽሬ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

አየር መንገዱም በመግለጫው ላይ በእነዚህ ሦስት ከተሞች የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዛቸውን ሲያስታውቅ፣ በረራዎቹ መቼ መልሰው እንደሚጀመሩ ግን አልገለጸም።

የህወሓት መሪዎች የፌደራል መንግሥቱን የመጣል ዓላማ እንዳላቸው በተደጋጋሚ መግለጻቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ትናንት ማክሰኞ ዕለትም በትግራይ አላማጣ ከተማ አካባቢ በተፈጸሙ ተከታታይ የድሮን እና የአውሮፕላን ጥቃቶች ቢያንስ 14 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሞገስ ሽፈራው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከንቲባው አቶ ሞገስ በጥቃቱ "የተገደሉት በሙሉ ሰላማዊ ሰዎች" መሆናቸውን እንዲሁም በታጣቂም ሆነ በጦር መሣሪያ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ሦስት የአካባቢው ነዋሪዎች ከተጎጂዎች መካከል በርካታ ታጣቂዎች መመልከታቸው አስረድተዋል።

ጥቃቱ በዋናነት መለስ ዜናዊ እና ኢያሱ በርሄ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ እንደተፈጸሙ ነዋሪዎችና የከተማዋ ከንቲባ አስረድተዋል።

በሁለቱ ትምህርት ቤቶችና ዙርያቸው ደረሰ በተባለው የድሮን ጥቃት ከትናንት ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር በተለያዩ ሰዓቶች እንደተፈጸመና ቢያንስ ከ10 ያላነሱ የድሮን ምልልስ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

በጉዳዩ ላይ ከፌዴራል መንግሥት መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የአውሮፕላን በረራዎች ቢቀጥሉም ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ለአጭር ቀናት ተቋርጦ ነበር።