ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋዛ ለፍልስጤማውያን መፈናቀል ምክንያት እየሆነ ያለው የእስራኤል ቢጫ መስመር
"ከቦታ ቦታ ስንፈናቀል ነው የቆየነው፤ አሁን ልንሄድበት የምንችል የቀረ ቦታ የለም" ትላለች ኡም መሐመድ አል ሻዊሽ።
አል ሻዊሽ፣ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምትቆጣጠረውን ቦታ ለማመልከት የተቀመጡ ቢጫ ግንቦችን እያንቀሳቀሰች በመሆኑ የምትኖርበት ሌላ ቦታ እየፈለገች ነው።
በጋዛ በስተሰሜን በምትገኘው አል ቱፋህ የሚገኙ ነዋሪዎችም ምልክቱ ተነስቶ በምዕራብ አቅጣጫ ሰሜን እና ደቡብን በሚያገናኘው ሳላህ አል ዲን መንገድ ላይ መቀመጡን ተመልክተዋል።
በአቅራቢያው በተቀመጠው ሦስት ሜትር ከፍታ ባለው ኬላ ላይ የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብም ነበር።
የአል ሻዊሽ ቤተሰብ መኖሪያ በጦርነቱ የወደመ ሲሆን የእስራኤል ጦር በአቅራቢያው በሚገኝ ሕንጻ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም ካስጠነቀቀ በኋላ በድጋሚ አካባቢውን ለቅቀው ወጥተዋል።
ብቸኛው መጠለያቸው የነበረው ድንኳንም በጥቃቱ ተቀዳዷል።
"እዚሁ ልንሞት ነው" ስትል ስጋቷን የገለፀችው አል ሻዊሽ፣ "ከዚህ ውርደት ሞት ይሻላል፤ ከእኛ ጋር የቆመ ማንም የለም" ብላለች።
በአሜሪካ አሸማጋይነት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት፣ እስራኤል ወታደሮቿን ከጋዛ በማስወጣት ምልክት (ቢጫ መስመር) ወደተደረገበት ክልል ለመውሰድ ተስማምታለች።
ስምምነቱ እስራኤል ከቢጫው መስመር ጀርባ ያለውን እና የጋዛን ግዛት 53 በመቶ የሚሆነውን አካባቢ በጊዜያዊነት እንድትቆጣጠር የሚፈቅድ ነው።
ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያምን ኔታንያሁ በቅርቡ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከ60 በመቶ በላይ የሆነ ቦታ መቆጣጠሩን ተናግረዋል።
ግንቦት ወር ላይም ለወታደሮቻቸው ትዕዛዝ የሰጡት 70 በመቶውን እንዲቆጣጠሩ እንደነበር በይፋ ተናግረዋል።
ሐማስ በበኩሉ እስራኤል ቢጫ መስመሩን ወደ ምዕራብ በኩል በመግፋት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲል ከስሷል።
አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣንም፣ "እስራኤል ሐማስ ያቀረበውን ክስ 'ከእውነት የራቀ' ስትል ውድቅ ማድረጓን" ተናግረዋል።
"የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሥምሪት እና የደኅንነት መስመሮች፣ የእስራኤል ዜጎችን ለመጠበቅ እና ሐማስ የሽብር ጦሩን እንደገና እንዳይገነባ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው። እስራኤል ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ላይ እርምጃ መውሰዷንም ትቀጥላለች" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር፣ መጀመሪያ ላይ ቢጫው መስመር ላይ በኮንክሪት በተሠሩ ግንቦች ምልክት አድርጎበት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን አንዳንድ ምልክቶችን ወደ ጋዛ አስጠግቷል።
የተወሰኑ ኬላዎችን የገነባችውም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ ብዙም ሳይቆይ ነበር።
ኬላዎቹ በአጠቃላይ 42 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ የተገፉ ሲሆን 85 በመቶ የእስራኤልን ቢጫ መስመር ይሸፍናሉ። ረዥሙ 13. 8 ኪሎ ሜትር ወደ ጋዛ ዘልቆ የገባ ነው።
ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል እያደረገች ያለው ነገር ሰርጡን ለረዥም ጊዜ የመያዝ ዕቅድ እንዳላት ያመለክታል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰኑ ኬላዎች ከቢጫው መስመር አልፈው ወደ ጋዛ ዘልቀው የገቡ ናቸው። ይህም የጋዛ ነዋሪዎች የሚገደሉበትን የጉዞ ክልከላ የበለጠ እንዲጨምር አድርጎታል።
በአል ማዋሲ ካምፕ አቅራቢያ የሚገኘው አንድ ቦታ ላይ ምልክቱ ከቢጫው መስመር ከ1.5 ኪሎ ሜትር በላይ የገባ ነው።
ሌላኛው በኻን ዩኒስ ያለው ደግሞ ከ500 ሜትር በላይ ወደ ውስጥ ገብቷል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል፣ "ቦታውን በግልጽ እና በሚታይ መልኩ እየሠራሁ ነው" ብሏል። ቀደም ብሎም ቢጫው መስመር በጦሩ እየተጣሰ ነው እንዲሁም መስመሮቹ ተገፍተዋል በሚል የቀረቡትን ሁሉንም ክሶች አስተባብሏል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ጦሩ ከተኩስ አቁሙ በኋላ ቢጫ ምልክቶችን ፍልስጤማውያን እየኖሩባቸው ወዳሉ አካባቢዎች በማስጠጋቱ በጋዛ ተጨማሪ መፈናቀሎችን ማስከተሉ ተዘግቧል።
ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም. በርካታ ቤተሰቦች ዕቃቸውን ጭነው በሞተር ሳይክል ምሥራቃዊ የጋዛ ከተማ የሆነችውን ዚታውን አካባቢን ለቅቀው ወጥተዋል።
አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በእስራኤል መከላከያ ኃይል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው እና ይህም ቢጫው ምልክት ድጋሚ እንደተገፋ እንደሚያሳይ የጋዛ ነዋሪዎች ተናግረዋል። አንዳንዶች ባዶ እጃቻቸውን ነበር በፍጥነት አካባቢውን ለቅቀው የወጡት።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ ድሮኖች እና መድፎች እንደተተኮሰባቸውም ገልጸዋል።
"ጦርነቱ አላበቃም። አብቅቷል የሚባለው ትልቅ ውሸት ነው። በየቀኑ ጥቃቶች፣ መፈናቀሎች እና ስደቶች አሉ" ብሏል እስማኤል ካሽኮ።
ወታደሮች እየቀረቡ ስለሆነ በእስራኤል ተኩስ እንዳመይቱ ቤተሰቦቹ ስጋት ላይ እንደወደቁም ገልጿል።
"በቤት ውስጥ አይደለም የምንኖረው፤ በድንኳን ውስጥ ነው። የሚከላከልልን ምንም ነገር የለም" ብሏል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ከሆነ በዚይታውን 30 የሚሆኑ ቤተሰቦች ድንኳ ናቸውን ያጡ ሲሆን፣ በቂ እርዳታ እያገኙ አልነበረም። የሳተላይት ምሥሎች እንደሚያሳዩትም ሐምሌ ወር ውስጥ በርካታ ጊዜያዊ መጠለያዎች ከአካባቢው ጠፍተዋል።
የዚይታውን ነዋሪዎችም በምሥራቅ በኩል የእስራኤል ጦር አዲስ ሰፈር እና መንገዶችን በሚገነባባቸው አካባቢዎች መቆፈሪያ ማሽኖችን እና ከባድ መሣሪያዎችን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የመከላከል አቅማቸው የደኅንነት ዞን፣ ኬላዎች፣ የደኅንነት ብቃት፣ ቴክኖሎጂ እና የዘመቻ እንቅስቃሴን እንደሚያካትት ለቢቢሲ ገልጿል።
እነዚህ እርምጃዎቹ "ሰርጎ ገብነት እና አደገኛ እንቅስቃሴን ለመከላከል ያለመ እንዲሁም ወታደሮችን እና በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ ለመጠበቅ ያለመ እንደሆነ" ገልጿል።
ለፀጥታ ዘመቻዎቹ "ሥምሪትን፣ የኬላዎችን መስመር እና ስፋትን በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር አንሰጥን" ብሏል።
በማዕከላዊ ከተማ ዴር አል ባላህ ምሥራቃዊ ክፍል ነዋሪዎች፣ በእርሻ መሬት ላይ እየኖሩ የነበሩ ቤተሰቦች አካባቢው ከመውደሙ በፊት ለቅቀው እንዲወጡ በእስራኤል ጦር የሁለት ቀናት ጊዜ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
የሳተላይት ምሥሎችም በአካባቢው ታንኮችን የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች እና የፈራረሰ አካባቢ አሳይተዋል።
ከቢጫ መስመሩ ከ500 ሜትር በላይ ገባ ብሎ የሚገኘው የወይራ ዛፍ እርሻ መውደሙንም ምሥሎቹ አመልክተዋል።
በቢቢሲ በተረጋገጡ ቪዲዮዎች ላይም ሦስት ቢጫ የግንብ ኬላዎች በቅርብ ቦታ ተቀምጠው ታይተዋል። እነዚህ ኬላዎች ከተኩስ አቁሙ በኋላ ከተሰመረው ቢጫ መስመር 300 ሜትር አልፈው የገቡ ናቸው።
በደቡብ በኩል ደግሞ አል ማዋሲ አቅራቢያ ቢጫ መስመሩ ላይ ምልክት ለማድረግ የተቀመጠ ኬላ ወደ መጠለያ ካምፓቸው እንዲጠጋ መደረጉን ፍልስጤማውያን ተናግረዋል።
በየቀኑ የሚደረጉ የእስራኤል ታንኮች እንቅስቃሴ፣ ተኩስ እና ረዣዥም የአሸዋ ግድቦች እንዳሉም ገልጸዋል።
የደኅንነት መረጃዎችን የሚተነትነው ተቋም - ኤምኤአይኤአር- መሥራች ቶኒ ሪቭስ፣ የሳተላይት ምሥሎችን የተነተኑ ሲሆን በጋዛ አንድ ቦታ ላይ የተቀመጠው ኬላ ሰባት ሜትር ከፍታ አለው ብለዋል።
የተረጋገጡ ቪዲዮዎች እና የሳተላይት ምሥሎች የተቆፋፈሩ መንገዶች እና ለመንገዶች ሲባል የፈራረሱ ሕንፃዎችን አሳይተዋል።
እስራኤል ከተኩስ አቁሙ ስምምነት በኋላ በጋዛ ዙሪያ የማውደም ዘመቻዋን ቀጥላለች።
ሰኔ ወር ላይ በደቡባዊ ራፋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ኬላ ግንባታ ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የእስራኤል ወታደሮች በመንገዱ ላይ ያሉትን መዋቅሮች እና መስመሮች ማውደማቸውን የሳተላይት ምሥሎች አሳይተዋል።
በአቅራቢያው በሚገኘው ኻን ዩኒስ በድሮን በተቀረጹ ምሥሎች ቢጫው መስመሩን አልፈው ሕንፃዎች የፈረሱበትና የታጠሩ ቦታዎች ታይተዋል።
ሐምሌ ወር ላይ በአቅራቢያው ኬላ የተገነባ ሲሆን ብዙ ተጨማሪ ሕንፃዎች ፈርሰዋል።
የሳተላይት ምሥሎች እንዳሳዩት በሐምሌ ወር ብቻ በኻን ዩኒስ፣ ዲር አል ባላህ፣ ዚይታውን እና በስተሰሜን በሚገኙት ጃባሊያ እና ቤት ላሂያ ከተሞች ከቢጫ መስመሩ አልፎ በርካታ ሕንፃዎች ወድመዋል።
ጦሩም ከኬላው ጀርባ በርካታ ሰፈሮችን፣ ካምፖችን እና ማማዎችን ገንብቷል ።
ከጥቅምቱ ተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ በግንባታ ላይ ያሉ ሁለት ቦታዎችን ጨምሮ አስራ አራት ቦታዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከስምምነቱ በፊት ተገንብተው የነበሩ ሌሎች ሰባት ቦታዎች ደግሞ ፈርሰዋል ወይም ተዘግተዋል።
ቢጫ መስመሩ በመጣስ ስለሚካሄደው የማፍረስ እርምጃ የተጠየቀው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።
"በደቡብ ዕዝ ሥር ያሉ የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደሮች በስምምነቱ መሠረት በቢጫ መስመሩ አካባቢ ተሰማርተዋል" ብሏል።
በእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጡረተኛው እስራኤላዊ ብርጋዲየር ጄነራል አሳፍ ኦሪዮን፣ የኬላዎች ግንባታ እና የጦር ሠፈሮች ግንባታ "ሐማስን ትጥቅ ለማስፈታት ጥቂት ለውጥ በታየበት ሁኔታ (ይህም ካለ ነው)፣ ጦሩ ቢጫ መስመሮቹን ተከትሎ ለረዥም ጊዜ ለመቆየት እየተዘጋጀ መሆን ያመለክታል" ብለዋል።
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የፀጥታ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንድሪያስ ክሬግ በበኩላቸው የቢቢሲ የምርመራ ውጤቶች እስራኤል ጊዜያዊ ወሰኑን በማለፍ ወደ ውስጣዊ ድንበር እየቀየረች እንደሆነ እንደሚያመልክት ተናግረዋል።
በጋዛ ያሉ ሰዎችም ቢጫ መስመሩ መገፋት ከባድ ውጤት እያከስተለ እንደሆነ እና በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኝ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ወደ ጠባብ ሥፍራ እንዲሰበሰብ እያደረገ ነው ብለዋል።
"ቢጫው መስመር ከዕለት ወደ ዕለት እየተገፋ ነው" ብለዋል ከጋዛ ከተማ የተፈናቀሉት አቡ ካሚል ሃማሚ።
"ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ያለማቋረጥ እየተዘዋወርን ነው። ሁሉም ቦታ በሰዎች፣ በድንኳኖች እና በተፈናቃዮች መጠለያዎች የተጨናነቀ ነው" ሲሉም ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።