ቀጥታ, ትራምፕ የሰላም ዕቅድ ካቀረቡ በኋላ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት ተስማማ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን እና ጋዛን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንደሚያደርግ አስታወቁ። ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ምሽት ከስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ይህም ያቀረቡትን የሰላም ዕቅድ ወደ ተግባር ለማስገባት ከፍተኛ እምርታ ነው ተብሏል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተሰነዘረውን የጥቃት ሙከራ ተከትሎ ዋሽንግተን ኢራን ላይ "ከፍተኛ" ድብደባ ፈጸመች
  • ሩሲያ በዩክሬን ባደረሰችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ተገደሉ
  • ታዋቂው ደራሲ ሳልማን ሩሽዲን ለመግደል የሞከረው ግለሰብ በሽብር ወንጀል ተፈረደበት

የቀጥታ ሽፋን

  1. በግብጽ የደረሰ የድሮን ጥቃት በሲዊዝ ካናል የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ፈጠረ

    በግብፅ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ በሚገኘው የዳሚዬታ ወደብ ላይ በሚገኙ ሁለት የጋዝ ማጓጓዣ መርከቦች ላይ እሳት ያስነሳው የድሮን ጥቃት፣ በስዊዝ ካናል በኩል የሚደረገው የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ አዲስ ስጋት ፈጠረ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል እየተባባሰ በመጣው ግጭት ወቅት የስዊዝ ካናል ለሳዑዲ ነዳጅ ንግድ ከቀሩት ዋና ዋና መስመሮች አንዱነው።

    በዳሚዬታ ወደብ በሁለት መርከቦች ላይ እሳት እንዲነሳ ያደረገው የድሮን ጥቃት መሆኑን የግብፅ ካቢኔ ሐሙስ ዕለት አስታውቆ ነበር።

    እስካሁን ድረስ ጥቃቱን በተመለከተ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

    ወደቡ ሜዲትራኒያን እና ቀይ ባህርን የሚያገናኘው የስዊዝ ካናል አቅራቢያ ይገኛል።

    የድሮን ጥቃት የአሜሪካ ንብረት በሆነው እና 'ኤነርጎስ ዊንተር' በተሰኘ የጋዝ ማከማቻ መርከብ ላይ ከደረሰ በኋላ እሳት የተነሳ ሲሆን ቃጠሎው ወደ ሌላ መርከብ መዛመቱን የዓይን እማኞች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ኢራን በዳሚዬታ በተፈጸመው ጥቃት ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት ገልጻለች።

    "ግብፅ በቀጣናው ውስጥ አስፈላጊ ወዳጅና አጋር ስትሆን፣ ደህንነቷም ለእኛ እጅግ ወሳኝ ነው" ሲሉ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

    "የቀጣናውን ሰላም ለማናጋት ታቅደው በሚከናወኑ የእስራኤል ሴራዎች እና የማጭበርበሪያ ድርጊቶች ላይ ሁላችንም ንቁ መሆን አለብን።"

    አምስት ወር የሞላው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴን በመግታት የዓለም ኤነርጂ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

    በኦማን እና በኢራን መካከል የሚገኘው ይህ መተላለፊያ ከግጭቱ በፊት የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ይጓጓዝበት ነበር።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚካሄደው የሰላም ድርድር ወቅት ማነቆ ጉዳዮች መካከል አንዱ የወሽመጡ ጉዳይ ይገኝበታል።

  2. ስለ ሐማስ ትጥቅ መፍታት የምናውቃቸው እና ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ “ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት” መስማማቱን አስታውቀዋል።

    ትጥቅ መፍታቱ በጋዛ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችንም የሚጨምር ሲሆን የእስራኤል ወታደሮችም ሰርጡን ለቅቀው እንደሚወጡ ተገልጿል።

    ትራምፕ ስምምነቱ የተደረሰው በሰላም ቦርዱ አማካኝነት መሆኑን ገልጸው “ጋዛ በአዲስ የፍልስጤም መንግሥት እንድትመራ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለውታል።

    ቢቢሲ የተመለከተው ባለ አራት ገጽ ፍኖተ ካርታ ሐማስ ትጥቅ የሚፈታበትን ጊዜያት ያስቀመጠ ሲሆን እስራኤልም ቀስ በቀስ አካባቢውን ለቅቃ ትወጣለች ይላል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት እያንዳንዱ ምዕራፍ በአግባቡ መፈጸሙ “ይረጋገጣል” ብለዋል።

    አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን ቡድኑ በዕቅዱ ላይ መስማማቱን ገልጸው ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ደግሞ እስራኤል ጋዛን ለቅቆ ለመውጣት የማትስማማ ከሆነ ትራምፕ “በጣም ቅር ይሰኛሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።

    እስራኤል በስምምነቱ ላይ ያላት አቋም ወይንም በድርድሩ ላይ ተሳታፊ ስለመሆኗ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

    የእስራኤል ጦር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ሲወጣም የሰላም ቀጣና ያደራጅ እንደሆነ አልታወቀም።

    የሐማስ ጦር መሣሪያዎችንም ማን ተረክቦ እንደሚያስተዳድራቸው በስምምነቱ ላይ አልተቀመጠም።

    የትጥቅ መፍታት ሂደቱም ሆነ የእስራኤል ጦር ለቅቆ መውጣት እንዴት እንደሚረጋገጥም በዝርዝር አልቀረበም።

  3. ትራምፕ የሰላም ዕቅድ ካቀረቡ በኋላ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን ገለፁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን እና ጋዛን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንደሚያደርግ አስታወቁ።

    ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ምሽት ከስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ይህም ያቀረቡትን የሰላም ዕቅድ ወደ ተግባር ለማስገባት ከፍተኛ እምርታ ነው ተብሏል።

    በዚህ ስምምነት መሠረት ጋዛ በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ቦርድ በሚቆጣጠረው የፍልስጤም የቴክኖክራቶች መንግሥት መተዳደር ትጀምራለች።

    ሐሙስ ዕለት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ “ይህ ለዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ወሳኝ እርምጃ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

    አክለውም “ይህ ስምምነት፣ በመጨረሻም የፍልስጤምን ሕዝብ ለመርዳት ከሰላም ቦርድ ጋር በቅርበት የሚሰራ አዲስ የፍልስጤም መንግሥት ጋዛን እንዲያስተዳድር ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

    በሥምምነቱ መሠረት የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው ይወጣሉ።

    ስምምነቱ የተደረሰው የሐማስ ባለሥልጣናት፣ የሰላም ቦርዱ አባላት፣ የግብጽ፣ ኳታር እና ቱርክ አደራዳሪዎች በተገኙበት ነው።

    የሐማስ ባለሥልጣናት ትጥቅ በመፍታት እና የእስራኤል ጦር የጋዛ ሰርጥን ለቅቆ እንዲወጣ ከስምምነት መደረሱን አረጋግጠዋል።

    ባለሥልጣናቱ የሰላም ቦርዱ እና አደራዳሪዎቹ እስራኤል በስምምነቱ ላይ ለተዘረዘሩት ነጥቦች ተገዢ እንድትሆን እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

    የሐማስ የድርድር ቡድን አባል የሆኑት ጋዚ ሃማድ፣ ቡድኑ "በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሕዝቦቻችንን ከግድያ እና ከመፈናቀል ለመታደግ ሲባል" ስምምነቶችን እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

    እስራኤል እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

    በሚያዚያ ወር ሐማስ በትራምፕ የቀረበውን የሰላም ቦርድ ጥረት ጋር በተያያዘ የቀረበውን ትጥቅ የመፍታት ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አድርጎ ነበር።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሐማስ ትጥቅ ከፈታ በኋላ እስራኤል ከጋዛ ለመውጣት ትስማማ እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ “እስራኤልን የምንጠይቃት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ከተስማሙበት የ20 ነጥብ ዕቅድ ውጪ ሌላ ነገር አይደለም፤ ስለዚህም ዕቅዱን እንደሚያከብሩት ሙሉ እምነት አለን" ሲል ምላሽ ሰጥተዋል።

    እስራኤል በ20 ነጥብ ዕቅዱ መሠረት ላለመውጣት ከወሰነች፣ ትራምፕ "እጅግ እንደሚያዝኑ" ባለሥልጣኑ ጨምረው ገልጸዋል። እስራኤል ጥሩ አጋርነቷን እንደምትቀጥል እንደሚያምኑም ባለሥልጣኑ አብራርተዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው “የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ ሲጠናቀቅ የእስራኤል ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው ይወጣሉ፤ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ኃይል፣ ጋዛ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎረቤቶቿ ደህንነቷ የተጠበቀ ቦታ እንዲሆን ኃላፊነቱን ለመረከብ ከአዲሱ የፍልስጤም ፖሊስ ኃይል ጋር በጋራ ይሠራል” ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ አደራዳሪዎቹን ግብጽ፣ ኳታር እና ቱርክን አመስግነዋል።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል የግብጽ መገናኛ ብዙኃንንን ጠቅሶ ካይሮ ሁለተኛውን ዙር የተኩስ አቁም ስብሰባ እንደምታዘጋጅ ዘግቧል።

  4. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኩዌት በሚገኝ የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር ላይ ጉዳት ማድረሱን ገለጸ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ኩዌት ውስጥ በሚገኘው አሊ አል-ሳሌም የአሜሪካ አየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ ፈጸምኩት ባለው ጥቃት ጉዳት ማድረሱን አስታወቀ።

    በጥቃቱ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ሁለት የድሮኖች መጠለያዎች እንዲሁም ለወታደራዊ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች የሚውል የነዳጅ ማከማቻ እንደወደመ ገልጿል።

    ነገር ግን እስካሁን ይህን የአብዮታዊ ዘቡን ጥቃት እና አደረስኩት ያለውን ጉዳት በተመለከተ ከኩዌትም ሆነ ከአሜሪካ ባለሥልጣት ወይም ከገለልተኛ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ጥቃቱ “ዘመቻ ናስር 2” የተባለ መሆኑን እና የአሜሪካ ኃይሎች በቀጣናው ለመኖራቸው የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ገልጿል።

    ነገር ግን ለጥቃቱ ጥቅም ላይ ስለዋሉት የጦር መሳሪያ ዓይነቶች፣ ስለደረሰው የውድመት መጠን ወይም በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት ምንም ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

    አብዮታዊ ዘቡ በኩዌት ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ኃይሎች በሚገኙበት አሊ አል-ሳሌም አየር ኃይል ሰፈር ላይ ቀደም ሲል ጥቃት ፈጽሞ በአሜሪካ መገልገያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጾ ነበር።

    ኢራን በአሜሪካ ለሚፈጸምባት ጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ሰፈሮች ላይ ተደጋጋሚ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው።

    በተለይም በዮርዳኖስ፣ ኩዌት እና ባህሬን ውስጥ ያሉት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ከባድ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው ተዘግቧል።

  5. ቻይና ለኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን ልትሸጥ ነው መባሉን አስተባበለች

    ቻይና ለኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ከትከሻ ላይ የሚወነጨፉ የአየር መቃዋሚያ ሚሳዔሎችን ልታቀርብ ነው መባሉን መከላከያ ሚኒስቴሯ አስተባበለ።

    የጦር መሳሪያ ሽያጩን በተመለከተ ስለቀረበው ሪፖርት የተጠየቁት የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጂያንፍ ቢን በሰጡት ምላሽ “ሐሰት” ሲሉ፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ዘገባውን “መሠረተ ቢስ” ብሎታል።

    ሮይተርስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሦስት ምንጮችን ጠቅሶ ቻይና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ቻይና ሠራሽ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን ለኢራን እንደምታቀርብ ዘግቦ ነበር።

    በስምምነቱ ኪውደብሊው-12 እና ኤፍኤን-16 የተባሉ ሚሳዔሎችን ጨምሮ ዋጋቸው ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ቻይና ለኢራን እንደምታቀርብ ገልጿል።

    የመጀመሪያዎቹ የጦር መሳሪያዎች በምዕራብ ቻይና ከምትገኘው ከተማ ኡሩምኪ ተነስተው በፓኪስታን በኩል ወደ ኢራን እንደሚጓጓዙ የሮይተርስ ምንጮች ተናግረዋል።

    ፓኪስታን በበኩሏ በእንዲህ ዓይነቱ የጦር ማሳሪያ ዝውውር ውስጥ እጇ እንደሌለበት በመግለጽ ዘገባውን “የፈጠራ እና የተዛባ” ብለዋለች።

    ኪውደብሊው-12 እና ኤፍኤን-16 የአየር መከላከያ ማሳሪያዎች ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ እና በዝቅተኛ ከፍታ የሚበሩ የአውሮፕላኖችን፣ የሄሊኮፕተሮችን እንዲሁም የድሮኖችን ሙቀት በመከተል ዒላማቸውን የሚመቱ ናቸው።

    ኢራን ከቻይና መሳሪያዎቹን ስለመግዛቷ የተዘገበው ለወራት በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈጸመባት ጥቃት የተዳከመውን የአየር መከላከያ ሥርዓቷን መልሳ ለመገንባት እና ለማጠናከር ጥረት እደያረገች ባለበት ጊዜ ነው።

  6. በኬንያ ፀረ- ተባይ ኬሚካል የተረጨበት ቲማቲም ለ15 ዝሆኖች ሞት ምክንያት እንደሆነ ተገለጸ

    በደቡባዊ ኬንያ፣ አምቦስሊ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ ሞተው የተገኙት 15 ዝሆኖች በአካባቢው ከሚገኝ እርሻ ፀረ-ተባይ ኬሚካል የተረጨበት ቲማቲም በመመገባቸው ሳይመረዙ እንዳልቀረ ተገለጸ።

    የአገሪቷ የዱር እንስሳት ጥበቃ አገልግሎት እንዳለው ከዝሆኖቹ በተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ሙከራ ምርመራ ‘ሳይናይድ’ የተባለ ኬሚካላዊ ውህድ ተገኝቷል።

    ኬሚካሉ በተወሰኑ እፅዋት እና ምግቦች ውስጥ የሚገኝ እንዲሁም በኢንደስትሪዎች ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

    ከዝሆኖች መካከል አስሩ የመንቀሳቀስ ችግር አጋጥሟቸው የተገኙ ሲሆን፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ሞተዋል።

    ቀሪዎቹ አምስቱ ግን ሕይወታቸው አልፎ ነበር የተገኙት። በክስተቱ ላይ የሚካሄደው ምርመራ እንደቀጠለ ነው።

    የዝሆኖቹ ሞት ያጋጠመው ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ባለው አንድ ወር ውስጥ እንደሆነም የዱር እንስሳት ጥበቃ አገልግሎቱ ገልጿል።

    ክስተቱ ዝሆኖች ምግብ እና ውሃ ለመፈለግ በሚንቀሳቀሱበት የፓርኩ አቅራቢያ እየተስፋፋ ባለው የእርሻ እንቅስቃሴ ላይ ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል።

    ፓርኩ እና አካባቢው አምቦስሊ ሥነ ምኅዳር በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በዱር እንስሳት ሃብቷ ከምትታወቀው ታንዛኒያ ጋር የሚያዋሰን ሰፊ አካባቢ ነው።

    ባለሥልጣናት እንዳሉት አደንን በማስቆም የተሳካ ውጤት በተመዘገበበት በቀጠናው፣ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ሞት ሲመዘገብ በአስርተ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ነው።

    በአምቦስሊ ብሔራዊ ፓርክ እና አካባቢው ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ዝሆኖች እንደሚገኙበት ይገመታል።

  7. ኡጋንዳዊው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ችሎት ውስጥ ራሳቸውን ከሳቱ በኋላ ሆስፒታል ገቡ

    ኡጋንዳዊው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኪዛ ቤሲጄ፣ ችሎት ውስጥ ሳሉ ራሳቸውን ስተው ከወደቁ በኋላ ጽኑ ህሙማን ክፍል መግባታቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ።

    የተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያ ድርጅት (ዩኤንኤድስ) ኃላፊ የሆኑት ባለቤታቸው ዊኒ ብያኒማ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “ ራሳቸውን አያውቁም፤ መናገር አይችሉም፤ ለሚያነቃቃ መድኃኒት እንኳ ምላሽ አይሰጡም” ብለዋል።

    የ70 ዓመቱ ፖለቲከኛ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ።

    ዋና ጠበቃቸውም ባለፈው ወር የታሰሩ ሲሆን "የአገር ክህደት ተግባርን ባለማሳወቅ" ክስ ቀርቦባቸዋል።

    ፖለቲከኛው ችሎት ውስጥ ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ የመንግሥት ጠበቆች እንዲወክሏቸው መሾማቸውን እየተቃወሙ ነበር።

    ከዚያም በእስር ቤቱ ጠባቂዎች ወደ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

    ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን በመገዳደር አራት ጊዜ ለፕሬዚደንትነት የተወዳደሩት ፖለቲከኛው፣ ከኬንያ ታፍነው ወደ ኡጋንዳ የተወሰዱት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

    ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከረዳታቸው ኦቤይድ ሉታሌ ጋር በእስር ላይ ይገኛሉ።

    በሁለቱም ላይ የአገር ክህደት ክስ ቀርቦባቸዋል።

    አቃቤ ሕግ፣ ፖለቲከኛው እና ረዳታቸው "የፕሬዝዳንት ሙሴቪንን መንግሥት ለመጣል ሴራ ጠንስሰዋል" ሲል ነው ክስ ያቀረበባቸው። እነርሱ ግን ክሱን አስተባብለዋል።

    በኡጋንዳ የአገር ክህደት ከባድ ወንጀል ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሞት ሊፈረድበት ይችላል።

  8. “አሜሪካ ስጋት ሆና እስከቀጠለች ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ አይከፈትም”- ኢራን

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ ስጋት ሆና እስከቀጠለች ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግመኛ አይከፈትም” ሲል አቋሙን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት “ማስፈራራት እና ማጋነን” የሚቀጥሉ ከሆነ እንዲሁም አሜሪካ በቀጣናው በሚገኘው ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ እስከቀጠለ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደማይከፈት አብዮታዊ ዘቡ አመልክቷል።

    የኢራን መንግሥት የሚያስተዳድረው ኢርና እንደዘገበው የአገሪቱ ጦር “ዛቻ እና ማስፈራሪያ ነገሩን የበለጠ የሚያባብስ እና የሚያጠላልፍ ነው” ሲል አስጠንቅቋል።

    አገራትን በስም ሳይጠቅስም “ወራሪዎችን የሚረዱ አገራት ባህሪያቸውን ካላስተካከሉ ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ብሏል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በስተደቡብ በኩል “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ለማለፍ የሞከሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ትናንት ምሽት እንዲመለሱ መደረጉን” አስታውቋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በስተደቡብ በኩል “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ለማለፍ የሞከሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ትናንት ምሽት እንዲመለሱ መደረጉን” አስታውቋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) “የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መርከቦች የሚያልፉበትን መንገድ መወሰን አይችልም” ብሏል።

  9. አሜሪካ እና ኢራን ወደ ግጭት መመለሳቸው እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ

    አሜሪካ እና ኢራን ግጭት አቁመው ወደ ዲፕሎማሲ መንገድ እንዲመለሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠየቁ።

    የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ ፋራህ ሐቅ በኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “ [ጉቴሬዝ ሁለቱ አገራት] ወደ ድርድር ጠረጴዛ የማይመለሱ ከሆነ ግጭቱ ይስፋፋል ብለው ይሰጋሉ። ባለፉት ሰዓታት ውስጥ የታየውም ይሄ ነው” ብለዋል።

    “እየታየ ያለው ነገር አወንታዊ አይደለም። የተመድ ዋና ጸሐፊ ተዋጊዎቹ ግጭቱን አቁመው በድጋሚ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ይፈልጋሉ” ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

    በፓኪስታን እና ኳታር አሸማጋይነት ድርድሮች መቀጠላቸውን ቃል አቀባዩ ፋራህ ጠቅሰዋል።

    ከሰሞኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "እጅግ ወዳጅነት የተሞላባቸው ድርድሮች" እየተካሄዱ መሆኑን ቢናገሩም ኢራን ንግግር ተጀምሯል መባሉን አስተባብላለች።

  10. በሀዋሳ ከተማ በረዶ ቀላቅሎ በጣለ ከባድ ዝናብ የአንዲት እናት ሕይወት አለፈ

    በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ በረዶ እና ከባድ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ኃይለኛ ዝናብ፤ የአንድ ሰው ሕይወት እንዳለፈ እና 10 ሰዎች ላይ “መጠነኛ ጉዳት” መድረሱን የከተማው አስተዳደር ለቢቢሲ ገለጸ።

    ትናንት ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም. ያጋጠመው ከባድ ዝናብ ከአመሻሽ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ እንደቆየ የሀዋሳ ከተማ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ምርጫዬ ደመቀ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ዝናቡ በተለምዶ አረብ ሰፈር፣ ስልጤ ሰፈር እና መናኽሪያ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ የገለጹት ኃላፊው፤ የአንዲት ሴት ሕይወት ማለፉንም አስረድተዋል።

    የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሴት በዝናቡ ሰዓት በጥሩ ይዞታ ላይ ባልነበረ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ እንደነበረችም ገልጸዋል። ቤቷ ውስጥ እንዳለች ሕይወቷ ማለፉንም ጠቁመዋል።

    ሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ኃላፊው እንደሚገልጹት በቤቶች እና ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለመለየት ግብረ ኃይል ተሰማርቷል።

    የከተማው አስተዳደር ትናንት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ በረዶ እና ኃይለኛ ንፋስ በቀላቀለው ዝናብ ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ጭምር መውደቃቸውን ገልጿል። በዚህም ምክንያት "አንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች የመብራት አገልግሎት" መቋረጡንም አስታውቆ ነበር።

    ይህንን ክስተት ተከትሎ፣ መሰል የዝናብ እና የጎርፍ አደጋዎች የሚያደርሱት ጉዳቶችን ለመቀነስ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ ጠይቀዋል። ከመንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲከተሉ እና ለአደጋ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

    የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በዘንድሮው የክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ የመጋለጥ ስጋት እንዳለባቸው ከገለጻቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ሐዋሳ ከተማ ነው። ከሲዳማ ክልሉ ዋና ከተማ በተጨማሪም በሁሉም ክልሎች ውስጥ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች እንዳሉ ተቋሙ በትንበያው አስቀምጧል።

    በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን ቀይህ ተኽሊ ወረዳ ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 14 ቀን በረዶ እና ኃይለኛ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ምክንያት የአንድ ታዳጊ ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

    በዚህ ክስተት 10 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ከ200 በላይ እንስሳት መሞታቸውን እንዲሁም ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ አዝዕርት መውደሙን የወረዳው ምክትል ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  11. ታዋቂው ደራሲ ሳልማን ሩሽዲን ለመግደል የሞከረው ግለሰብ በሽብር ወንጀል ተፈረደበት

    ታዋቂው ደራሲ ሳልማን ሩሽዲን ለመግደል በመሞከር 25 ዓመት ተፈርዶበት እስር ቤት ያለው ግለሰብ በተጨማሪ የሽብር ወንጀል ክሶች ተፈረደበት።

    ክሱ የሽብር ቡድኖችን በግብዓት መደገፍን ይጨምራል። ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አሜሪካ እና ዩናይትድን ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ሽብርተኛ ብለው የፈረጁት ሄዝቦላህ ይገኝበታል።

    ሀዲ ማራር በኒው ዮርክ የፌደራል ፍርድ ቤት ረቡዕ ዕለት ተፈርዶበታል።

    የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ በአውሮፓውያኑ 1989 ሳልማን ሩሽዲ እንዲገደል ያወጡትን ፋትዋ ለመፈጸም መሞከሩን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

    ድንበር ተሻጋሪ የሽብር ድርጊት በመፈጸም እና ለሄዝቦላህ ድጋፍ በመስጠትም ተፈርዶበታል።

    ተሸላሚው ደራሲ በፍርድ ቤት ቃሉን ሲሰጥ ሕይወቱን ያረፈውን የእሳት አደጋ ተከላካይ አመስግኗል።

    ሳልማን ሩሽዲ መድረክ ላይ ንግግር እያደረገ ሳለ በደረሰበት የስለት ጥቃት አንደ ዐይኑን አጥቷል።

    ሕንድ የተወለደው እና የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው ሩሽዲ፤ በዘመናዊው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ደራሲያን መካከል አንዱ መሆኑ ይነገርለታል።

  12. ሩሲያ በዩክሬን ባደረሰችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ተገደሉ

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ረቡዕ በሰጡት ማስጠንቀቂያ ሩሲያ “መጠነ ሰፊ ጥቃት” ልታደርስ ትችላለች ብለዋል።

    ዛሬ ሐሙስ ንጋት ላይ በርካታ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን የዩክሬን ጦር አስታውቋል።

    ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።

    ዩክሬን ሚሳዔል መቃወሚያ የሆነውን ‘ፓትሪዮት ኢንተርሴፕተር’ እንድታመርት ፈቃድ እንዲሰጣት ዜሌንስኪ ጠይቀዋል።

    በዩክሬን ክሪቭ ሪህ ከተማ በደረሰው ጥቃት የሞቱት ሕጻናት ዕድሜያቸው 5 እና 12 መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ጉዳት ከደረሰባቸው ስምንት ሰዎች መካከል ሁለቱ ሕጻናት መሆናቸውም ተገልጿል።

    በመዲናዋ ኪቭ ምሽት ላይ በሦስት ሕንጻዎች በተነሳ እሳት ሳቢያ አንድ ሰው መሞቱን የከተማዋ ከንቲባ ቪታል ክሊትሾኮ በቴግራም ገጻቸው አስታውቀዋል።

  13. የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተሰነዘረውን የጥቃት ሙከራ ተከትሎ ዋሽንግተን ኢራን ላይ "ከፍተኛ" ድብደባ ፈጸመች

    የአሜሪካ ጦር ኢራን በዋሽንግተን ኃይሎች ላይ ለሰነዘረቻቸው የሚሳዔል ጥቃት ሙከራዎች የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ሲል፤ ረቡዕ ምሽት ኢራን ላይ "ከፍተኛ" ድብደባ መፈጸሙን አስታወቀ።

    በዚህ ጥቃት "በርካታ" የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዒላማዎች መመታታቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ገልጿል።

    አሜሪካ ጋብ አድርጋው የነበረውን ድብደባ በድጋሚ የጀመረችው፤ ማክሰኞ ዕለት ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዞ ላይ የነበሩ መርከቦች ላይ ሚሳዔሎችን በማስወንጨፏ እንደሆነ ዕዙ ተናግሯል።

    የአሁኑ መካረር የታየው አሜሪካ እና ሳዑዲ በጋራ ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የኢራን ተቀጽላዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ በገለጹ ማግሥት ነው። ይህ ወታደራዊ እርምጃ የጦርነቱን አድማስ አስፍቶታል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ለአንድ ሰዓት ገደማ የቆየውን የረቡዕ ምሽት ጥቃት "ኢራን ትናንት በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ ለሰነዘረችው የጥቃት ሙከራ የተሰጠ ኃይለኛ ምላሽ" ሲል ገልጾታል። በኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎች በሙሉ እንዲከሽፉ መደረጋቸውንም አክሏል።

    በአሜሪካ ጥቃት የኢራን "ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላት፣ የሜሳዔል እና የድሮን ተቋማት፣ የባሕር ዳርቻ ቁጥጥር እና መከላከያ ስፍራዎች፣ እና የባሕር ኃይል አቅሞች" ዒላማ መደረጋቸውም ተገልጿል።

    ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ አስቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ለኢራን ሙከራ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝተው ነበር።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ጦር ሠፈር እና የዕዝ ማዕከልን ዒላማ ያደረገው "ህጻናት ገዳይ በሆነችው አሜሪካ ለተፈጸሙት የጥቃት ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት" እንደሆነ ገልጿል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት ወር ኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት በከፈቱበት ወቅት፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱ የሚቆየው ለጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ ግጭቱ ሊያበቃ እንደሆነ የሚጠቁም ምልክት ሳይታይበት አምስተኛ ወሩን ደፍኗል።

    የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የዋሽንግተን ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ፤ ትራምፕ ከሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ልዑል ካሊድ ቢን ሰልማን ጋር መገናኘታቸውን አስነብቧል።

    የሳዑዲው መከላከያ ሚኒስትር አገራቸው ውጥረቱ እንዲረግብ እንደምትፈልግ ማሳወቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የዋይት ሀውስን አስተያየት ለማካተት ጥያቄ አቅርቧል።

    አሜሪካ ለ13 ተከታታይ ቀናት ጥቃት ስትፈጽምበት፤ ኢራንም አጸፋውን ስትመልስበት የቆየው ግጭት ለቀናት አንጻራዊ መረጋጋት ከታየበት በኋላ በድጋሚ ተቀጣጥሏል።

    አንዳች አይነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ በታየባቸው ያለፉት ቀናት ሁለቱም ወገኖች ጥቃት መፈጸም አቁመው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ "እጅግ ወዳጅነት የተሞላባቸው ድርድሮች" እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረው ነበር። ኢራን ግን ንግግር ተጀምሯል መባሉን አስተባብላለች።

  14. አሜሪካ እና ሳዑዲ በኢራቅ ውስጥ የፈጸሙትን ጥቃት ኢራን አወገዘች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጥምረት ኢራቅ ውስጥ የፈጸሙትን ጥቃት “በጽኑ እንደሚያወግዝ” አስታወቀ።

    ጥቃቱ የአሜሪካ እና ሳዑዲ ጥቃት ጦርነቱን በመካከለኛው ምሥራቅ ለማስፋፋት ያለመ ነው ሲልም ወቅሷል።

    ኢራን ሁለቱን አገራት “ነውጠኛ” ስትል ያወገዘች ሲሆን፣ የፈጸሙት ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ስምምነትን እንደሚጥስም አስታውቃለች።

    ጥቃቱ የአሜሪካ እና የጽዮናዊው [እስአኤል] መንግሥት “ፍላጎት” እንደሆነ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ይጠቅሳል።

    “ጽዮናዊው መንግሥት ጦርነቱን እና ግጭቱን ወደ ምዕራብ እስያ ማስፋፋት ይፈልጋል” ሲልም የእስራኤልን መንግሥት ከስሷል።

    አሜሪካ እና ሳዑዲ በኢራቅ የሚገኙ እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

    የኢራቅ ‘ፖፑላር ሞቢላይዜሽን ፎርስ’ ቡድን በጥቃቱ ቢያንስ 20 አባላቱ እንደተገደሉበት እና 32 እንደቆሰሉበት አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) “ኢራቅ ውስጥ በኢራን የሚደገፈው አሸባሪ ቡድን ላይ አነጣጥረን ጥምር ጥቃት [ከሳዑዲ አረቢያ ጋር] ፈጽመናል” ብሏል።

    ሳዑዲ በበኩሏ ጥቃቱ የተፈጸመው ቡድኑ የነዳጅ ማውጫዎቿን ዒላማ ካደረገ በኋላ እነደሆነ አስታውቃለች።

  15. አሜሪካ በ8 የኢራን የነዳጅ መርከቦች እና 10 ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት የኢራን ንብረት የሆኑ ስምንት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እና አሥር ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት (የገንዘብ ሚኒስቴር) በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ተቋማት ስድስቱ ቻይና ይገኛሉ።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ገደብ ባለበት እንደቀጠለ ነው።

    በኢራን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ በተጣለው እገዳ ምክንያት የአሜሪካ ኃይሎች ብዙ መርከቦች እንዳያልፉ ከልክለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት የጣለው አዲስ ማዕቀብ የተሰማው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን “ክፉኛ ለመደብደብ” ከዛቱ ከሰዓታት በኋላ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጦራቸው በኢራን ላይ ላለፉት ቀናት ያቆመውን ጥቃት መልሶ እንደሚጀምር አመልክተዋል።

  16. ኢራን የአሜሪካ ጦር ሰፈርን ማጥቃቷን ተከትሎ ትራምፕ ኢራንን “ክፉኛ” እንደሚመቱ ዛቱ

    ኢራን ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ማክሰኞ ዕለት ለሰነዘረችው የሚሳዔል ጥቃት አጸፋ “ከባድ ጥቃት” እንደሚፈጸምባት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

    ፕሬዝዳንቱ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት “በከባዱ እንመታቸዋለን. . . ቅጣት ይጠብቃቸዋል. . . ልክ እናስገባቸዋልን...” በማለት ጦራቸው በኢራን ላይ ላለፉት ቀናት ያቆመውን ጥቃት እንደሚጀምር አመልክተዋል።

    የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ማክሰኞ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ሚሳዔሎች በመተኮስ “ድንገተኛ ጥቃት ለመፈጸም ሞክሯል” በማለት፤ ነገር ግን ሁሉም ሚሳዔሎች “በተሳካ ሁኔታ” መክሸፋቸውን ገልጿል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጸም የተናገሩት ሠራዊታቸው ለ13 ተከታታይ ቀናት በኢራን ላይ ሲፈጽም የቆየውን ጥቃት ባለፈው አርብ ካቆመ በኋላ ነው።

    ኢራን በአሜሪካ ለተፈጸመባት ጥቃት ዮርዳኖስን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ የአሜሪካ ወታደሮችን መግደሏ ተዘግቧል።

    የአሜሪካ ጥቃት መቆሙን ተከትሎ ኢራንም የአጸፋ ጥቃቷን አቁማ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት ሁለቱን አገራት ለማቀራረብ እና የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዳሉት በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ኢራንም አጸፋ መመለሷ አይቀሬ መሆኑን ባለፉት ሳምንታት የነበሩት ሁኔታዎች ያመለክታሉ።

  17. በጃፓን በተከሰተው ርዕደ መሬት ሳቢያ 13 ሰዎች ሞቱ

    ደቡብ ምዕራብ ጃፓን በሚገኘው ኩይሹ ግዛት ወደ 100 የሚጠጉ ውስን ርዕደ መሬቶች ተከሰቱ።

    ከፍተኛ መጠን ያለው ርዕደ መሬት መነሳቱን ተከትሎ 13 ሰዎች ሞተዋል። ከፍተኛውን ርዕደ መሬት ተከትሎም መጠነኛ የሆኑ 100 የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል።

    በርካታ ሰዎች ድንገተኛ የደም ዝውውር መቋረጥ እንደገጠማቸው ተገልጿል።

    በጃፓን ከፍተኛ ሙቀት ያለ ሲሆን፤ በኩማማቶ አካባቢ በሚገኝ የወረቀት ፋብሪካ እና የመደብር ፍርስራሽ ውስጥ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማዳን ጥረት ቀጥሏል።

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳኔይ ታካይቺ “ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም ላይ ነን” ሲሉ ሰዎችን በሕይወት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ገልጸዋል።

    በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በድንገተኛ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

    የጃፓን ሜትሮሎጂ ተቋም ባወጣው ማስጠንቀቂያ ነዋሪዎች አነስተኛ መጠን ላላቸው ርዕደ መሬቶች (aftershocks) ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

    “ለሚቀጥለው ሳምንት፣ በተለይም ለቀጣይ ሁለት እና ሦስት ቀናት እስከ 7 ማግኒትዩድ የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ ይኖራል” ሲልም አስታውቋል።

    ትናንት ማክሰኞ ኩማማቶ በተከሰተው ርዕደ መሬት ኤዩን የተባለ ግዙፍ መደብር ተጎድቷል።

  18. አሜሪካ እና ሳዑዲ የኢራን አጋር የሆኑትን የኢራቅ ታጣቂዎች ሲደበድቡ በባሕረ ሰላጤው ዳግም ውግያ አገርሸ

    አሜሪካ ለሦስት ቀናት በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ ገትታ ከቆየች በኋላ ረቡዕ ዕለት በኢራቅ የሚገኙ እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ዋሺንግተን እና ሪያድ ጥቃቱን የፈጸሙት በጋራ መሆኑን አሳውቀዋል።

    ኢራን በበኩሏ በወሽመጡ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦች እንዲሁም በዮርዳኖስ ወደሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሠፈር ሚሳዔሎችን ማስወነጨፏን ገልጻለች።

    የኢራቅ ‘ፖፑላር ሞቢላይዜሽን ፎርስ’ በመባል የሚታወቀው እና በኢራን የሚደገፈው ቡድን በአሜሪካ ጥቃት ቢያንስ 20 አባላቱ እንደተገደሉበት እና 32 እንደቆሰሉበት አስታውቋል።

    ሳዑዲ ጥቃቱ የተፈጸመው ቡድኑ የነዳጅ ማውጫዎቿን ዒላማ ካደረገ በኋላ እነደሆነ አስታውቃለች።

    አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጋራ የፈጸሙት ይህ ጥቃት በሳዑዲ የሚገኙ ሱኒዎችን በኢራቅ ከሚገኙ ሺዓዎች ጋር ጦርነት ውስጥ በመክተት አዲስ የግጭት በር የከፈተ ሆኗል።

    ሳዑዲ አረቢያ ከአሜሪካ ጋር በመሆን በዚህ ጦርነት ውስጥ መሳተፏን ስታሳውቅ ይህ የመጀመርያዋ ነው።

    ከአሜሪካ እንዲሁም ከኢራን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው የኢራን አስተዳደር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

    ዋሺንግተን ለረዥም ጊዜ ባግዳድ በኢራን በሚደገፉት ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እንድትወስድ ስትጠይቅ የቆየች ሲሆን የኢራን አስተዳደር ይህንን ለማድረግ ሲሞክር በአካባቢው አለመረጋጋት ተከስቷል።

    ሳዑዲ አረቢያ በሌላ አቅጣጫ በየመን ከሚገኙት የሁቲ አማፂያን ጋር ግጭት ውስጥ ገብታለች።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የሳዑዲ መርከቦች በቀይ ባሕር እንዳያልፉ እገዳ ጥለዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ በጋራ በኢራቅ ጥቃት ከፈጸሙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የአሜሪካ ጦር በወታደሮቹ ላይ ኢራን የከፈተችውን ድንገተኛ ጥቃት ማክሸፉን አስታውቋል።

    የዮርዳኖስ ጦር ከኢራን የተወነጨፉ አምስት ሚሳዔሎችን መትቶ መጣሉን ገልጿል።

    በዚህ ወር በኢራን ጦርነት ከሞቱት አራት የአሜሪካ ወታደሮች መካከል ሦስቱ የተገደሉት በዮርዳኖስ ነው።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ሚሳዔሎችም ማስወንጨፉን እንዲሁም ያለ ፈቃድ በወሽመጡ ለማለፍ የሞከሩ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃቱን አስታውቋል።

  19. አምስት የኬንያ የጸጥታ አባላት በሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ

    በሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ማንዴራ ክልል ውስጥ ከአል ሻባብ ታጣቂዎች ጋር በተደረገ ግጭት አምስት የኬንያ የጸጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን ፖሊስ ገለጸ።

    ታጣቂ ቡድኑ የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥት ለመጣል እና በእስላማዊ ሸሪዓ ሕግ የሚመራ ሥርዓትን ለመዘርጋት ለዓመታት ሲታገል ቆይቷል።

    ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ “በአካባቢው ቅኝት እያደረገ የነበረ ቡድን በዋንቴይ ግድብ አካባቢ ከአል ሸባብ አማጺያን ጋር ከተገናኘ በኋላ” ጥቃቱ መፈጸሙን ፖሊስ አስታውቋል።

    ፖሊስ ተጨማሪ ኃይል ከተላከለት በኋላ ታጣቂዎቹን መከታተል መጀመሩን እና የተቀበረ ፈንጂ መኪናው ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።

    በፈንጂው ፍንዳታ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ጨምሮ ገልጿል።

    አል ሸባብ በጸጥታ ኃይሎች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርስ ሲሆን በጥር ወር በጋሪሳ የአካባቢውን አስተዳደር እና አንድ መምህር ገድሏል።

  20. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በጋራ ለማስተዳደር አማን ያቀረበችውን ዕቅድ ውድቅ አደረገች

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በጋራ ለማስተዳደር አማን ያቀረበችውን ዕቅድ የመሳካት ዕድል የለውም ስትል ውድቅ አደረገች።

    አንድ ከፍተኛ የአራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ እነደተናገሩት ዕቀዱ “የመሳካት ዕድል የለውም” በማለት ወሽመጡን መቆጣጠር የኢራንን ሉዓላዊ መብቶች ማረጋገጥ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

    ባለሥልጣኑ ኢራን እና ኦማን ብቻ የሆርሙዝ ወሽመጥን በማስተዳደር ረገድ የሚጋሩት ድንበር ስላለ የመወሰን መብት እንዳላቸው በመጥቀስ የሌሎች የቀጣናው አገራትን ሚና ውድቅ አድርገዋል።

    ባለሥልጣኑ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በወሽመጡ ላይ ያላቸውን “ከእውነታው የተቃረነ ዕቅዳቸውን” ለማስፈጸም ኦማን ላይ ጫና እያደረጉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥ ተቃራኒ የባሕር ዳርቻዎችን ይቆጣጠራሉ።

    ነገር ግን ቴህራን የወሽመጡ የውስጠኛ መተላለፊያ እንዲሁም በከፊል ከወሽመጡ ውጪ ያሉ አካባቢዎች በኢራን ቁጥጥር ሥር መሆን አለበት ብላ እንደምታምን ባለሥልጣኑ ጨምረው ለሮይተርስ አስረድተዋል።