ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሳዑዲ የሞት ፍርድ የሚጠብቃቸው ኢትዮጵያውያን በጭንቀት ከእስር ቤት ለቢቢሲ ደውለው ያጋሩት ታሪክ
- ፀሐፊ, አክሊሉ ጸጋይ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ትግርኛ
- ታትሟል
- የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ
በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ እየተጠባበቀ ያለው ወጣት ኢትዮጵያዊ እስር ቤት ውስጥ ሳለ ከቢቢሲ ጋር በስልክ የመነጋገር ዕድል ሲያገኝ ድምጹ ውስጥ ጭንቀት እና ተስፋ መቁረጥ ያስተጋባል።
ሀብቶም እና ሌሎችም በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ስማቸው ተለውጧል።
ሀብቶም ከሦስት ዓመት በላይ በደቡባዊ የሳዑዲ ክፍል በምትገኘው ኻሚስ ሙሻይት ከተማ በእስር ላይ ይገኛል።
ከጀርባው የእስረኞች ድምጽ ጎልቶ ይሰማል። ሀብቶም እርዳታ ለማግኘት ይማጸናል። የአገሩ መንግሥት ዕጣ ፈንታውን ለመለወጥ እምብዛም ጥረት ባለማድረጉ የተበሳጨ ይመስላል።
እሱ እና ሌሎችም አብረውት የታሰሩ ሰዎች ጦርት እና ድህነት በመሸሽ ለተሻለ ሕይወት ሲሉ ቤታቸውን ጥለው ተሰድደዋል።
በጂቡቲ እና የመን በኩል የወሰደው ጉዞው መጨረሻ ግን እስር ሆኗል። በሳዑዲ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ተከስሰው እስር ቤት ከሚገኙ እና ቁጥራቸው እየጨመረ ካለው ኢትዮጵያውያን ጋር ተቀላልቅሏል።
ታሪካቸውን ለመናገር እጅጉን በመፈለግ ሌሎችም እስረኞች ስልኩን ተቀብለው ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር አውርተዋል።
በርካታ ቁጥር ካላቸው እስረኞች መካከል ሰባቱን አነጋግረናል። በእስር ቤቱ የሞት ፍርድ እየተጠባበቁ ሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 200 ሊደርስ ይችላል።
ፓኪስታናውያን፣ ሱናዳውያን እና ዮርዳኖሳውያንን ጨምሮ ሌሎችም የውጭ አገር ዜጎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
በያዝነው ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት 17 ኢትዮጵያውያን በሞት ተቀጥተዋል።
የሳዑዲ ዜጋ ካልሆኑት መካከል የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ነው።
አምስቱ የሞት ቅጣቶች የተፈጸሙት ሰኞ ዕለት ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሠራው ጥናት መሠረት ከሁለት ዓመት በፊት ሁለት ኢትዮጵያውያን ብቻ በሞት ተቀጥተዋል። በ2025 ቁጥሩ 35 ደርሷል።
ቁጥሩ ለምን እንደጨመረ ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ሁለት ዓመት ካስቆጠረው እና ጠባሳ ጥሎ ካለፈው የትግራይ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች እየተሰደዱ ሊሆን ይችላል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ዳና አሕመድ "በቅርብ ዓመታት ውስት ሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ለተያያዙ ወንጀሎች የሞት ቅጣትን ከማስፋፋቷ ጋርም የሚያያዝ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሀብቶም እንደ ሌሎቹ ቢቢሲ ያነጋገራቸው እስረኞች ሁሉ ከትግራይ ነው።
ሀሺሽ በስውር በማስገባት ጥፋተኛ ተብሏል።
በሳዑዲ አረቢያ ዳኞች የሚተላለፍ ብይን የሞት ቅጣት ሊያስከትል ይችላል።
ነገር ግን ሪፕራይቭ፣ ሂውማን ራይትስ ዋች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የመብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ተገቢውን የፍርድ ሒደት አይከተሉም።
ተከሳሾች ጠበቃ አያገኙም፤ ፍርድ ቤትም አይቀርቡም። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ዳና እንደሚሉት፤ አስተርጓሚ የሚቀርብም ከሆነ በቂ አይደለም።
በአሠራር ደረጃ ይግባኝ ማለት ቢቻልም ያለ ጠበቃ ይግባኙን ማቅረብ አይቻልም።
"ከዚያም ፍርዱ ወዲያውኑ ተፈጻሚ ይሆናል" ይላሉ።
"ፍርድ ተላልፎ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገምግሞ፣ ንጉሡ ይሁንታ ሰጥተው እስከሚጸና ድረስ ባለው አጠቃላይ የፍርድ ሒደቱ ግልጽነት የለውም ማለት ይቻላል። የሞት ፍርድ የሚጠባበቁ ሰዎች እና ቤተሰባቸው ስለ ዕጣ ፈንታቸው መረጃ አይሰጣቸውም" ሲሉም ያክላሉ።
ሀብቶም እንደሚለው ከጠበቃ ጋር ለመነጋገር እና እራሱን ለመከላከልም ዕድሉ አልተሰጠውም።
በአረብኛ የተጻፈ ሰነድ ላይ እንዲፈርም እንደተገደደም ይናገራል። ይህ ጽሑፍ በፍርድ ውሳኔው እንደተስማማ ይገልጻል። ሆኖም ግን ምን ላይ እየፈረመ እንደሆነ አላወቀም።
ሌሎችም ቢቢሲ ያነጋገራቸው እስረኞች ስለ ፍትሕ ሥርዓቱ ተመሳሳይ ታሪክ ተናግረዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋችም ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር በመነጋገር "የጅምላ ፍርድ፣ ተገቢውን የፍትሕ ሒደት ያልተከለ የጅምላ የፍርድ ቤት ሥርዓት እና መቼ እንደሚፈረድባቸው በውል ሳያውቁ ታስረው የሚጠባበቁ ሰዎች" እንዳሉ መረዳቱን በተቋሙ የተፈናቃዮች እና ስደተኞች ከፍተኛ አማካሪ ናዲያ ሀርድማን ይናገራሉ።
የፍርድ ሒደቱ ፍትሐዊ አይደለም የሚለውን ክስ በተመለከተ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የሳዑዲ ባለሥልጣናት ምላሽ አልሰጡም።
ሆኖም ግን እያንዳንዱ የሞት ፍርድ ሲፈጸም በይፋዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል መግለጫ ይወጣል።
መግለጫው የምርመራ ሒደት፣ የፍርድ ቤት ሒደት፣ ይግባኝ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እና የንጉሥ የፍርድ ይሁንታ ውሳኔን በግልጽ ይዘረዝራል።
መግለጫው ዜጎችን "ከአደንዛዥ ዕፅ መቅሰፍት" እና ከሚያደርሰው ጉዳት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኛነት ያንጸባርቃል።
ሀብቶም እንደሚለው በእስር ቤቱ በሚገኘው ክፍሉ ውስጥ ባለ የግድግዳ ስልክ አማካኝነት ከቤተሰቡ ጋር አልፎ አልፎ መገናኘት ቢችልም፤ የሞት ፍርድ እየጠበቀ መሆኑን ሊነግራቸው አልፈለገም።
"አሁን ከሚነገራቸው ከሞትኩ በኋላ ቢሰሙ ይሻላል" ይላል።
ሕልሙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቆ፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ፣ ሥራ ይዞ ቤተሰቦቹን መርዳት ነበር። ነገር ግን በትግራይ ጦርነት ምክንያት ሊያሳካው አልቻለም።
"ሕልሜ ከሰመ፤ ስለዚህ ለመሰደድ ወሰንኩ" ይላል።
በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከሚደረገው አደገኛ ጉዞ ተርፎ በፍየል ጠባቂነት አነስተኛ ገንዘብ ያገኝ ጀመር። ቀጣሪዎቹ እሱ እና ሌሎችም የተሻለ ገንዘብ የሚያገኙበትን ዕድል አቀረቡላቸው።
ጥቅል እንዲያደርሱ ተጠይቀው በጉዞ ላይ ሳሉ ፖሊስ አስቆማቸው። እጃቸው ላይም ጫት ተገኘ።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ይፋዊ መግለጫዎች ሀሽሽ ማዘዋወር ቢሉም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግን የጠቀሱት ጫትን ነው።
ሀብቶም "ምን ይዘን እንደነበር አላወቅኩም። ኋላ ላይ ጫት መሆኑ ተነገረኝ። ጫት ምን እንደሆነ እንኳን አላውቅም" በማለት ሥራውን ለመሥራት የፈቀደው የቀረበለት ገንዘብ አማልሎት እንደሆነ ይናገራል።
ሀብቶም "ባለማወቅ ጥፋት መሥራቱን" ያምናል። የፍርድ ውሳኔው ወደ እስራት እንዲለወጥለትም ይፈልጋል።
ሚያዝያ ላይ ሦስት አብረውት የነበሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች በሞት ተቀጥተዋል።
ሰኔ ላይ ደግሞ ዘጠኝ እስረኞች ተገድለዋል።
ሚያዝያ ላይ የሞት ቅጣቶቹ ሲፈጸሙ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ከተወሰኑ የኢትዮጵያ አመራሮች ተቃውሞ ተሰምቷል።
አቡነ ማትያስ፤ መንግሥት ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገር አሳስበዋል።
እስረኞቹንም "በሞት ጥላ ሥር የሚኖሩ ድምጽ አልባ ልጆች" ብለዋቸዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ሚያዝያ ላይ ባወጣው ሪፖርት የሳዑዲ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሞት ቅጣት እንዲያቆሙ እና የሁሉም ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንዲከናወን እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ እና በቆንስላው ድጋፍ እንዲሰጥም ጠይቋል።
ግንቦት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ እና የሳዑዲ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አል-ኩራጂ አዲስ አበባ ሲገናኙ በሳዑዲ አረቢያ ስላለው አጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ደኅንነት ጉዳይ ተነስቷል።
ይህንን ተከትሎ ሰኔ ላይ የኢትዮጵያው አምባሳደር ጣፋ ቱሉ ዳዲ በሳዑዲ እስር ቤት ጉብኝት አድርገዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው እስረኞች ግን ያሉበትን ሁኔታ ለአምባሳደሩ ለማስረዳት በቂ ጊዜ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
በቀጣዩ ሳምንት ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን በሞት የተቀጡ ሲሆን፤ ጉብኝቱ እምብዛም ተጽዕኖ የፈጠረ አይመስልም።
የአፍሪካ ኅብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ ላይ ያሉ ዜጎቿን ደኅንነት እንድትጠብቅ ኢትዮጵያን አሳስቧል።
ቢቢሲ በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከፌደራል መንግሥቱም አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሞት ፍርድን ባይጠቅስም ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ "የሕግ ሒደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው" ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ "ከሚመለከታቸው" የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር "በቅርበት እየተነጋገረ" መሆኑን አስታውቋል።
ወደ 2,000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን "ንጉሣዊ ምሕረት እንዳገኙም" ገልጿል። ወንጀሎቹ እና የተላለፈባቸው ፍርድ ምን እንደሆኑ ግን አልተጠቀሰም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እስረኞች ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እናገኛለን ብለው እየጠባበቁ ሲሆን፤ በተጨናነቁ እስር ቤቶች እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነም ይናገራሉ።
በሌላኛው የእስር ቤቱ ክፍል የሚገኘው ደስታ እንደሚናገረው እሱ ባለበት ክፍል ውስጥ 200 ወንዶች ተጨናንቀው ይገኛሉ። ለ90 ሰዎች እንዲበቃ በተዘጋጀው ክፍል ውስጥ 45 ተደራራቢ አልጋዎች በግድግዳ ጥጎች ይገኛሉ።
ቀን ላይ እስረኞቹ በአስጨናቂ ሁኔታ እርስ በርስ ተጠጋግተው መሬት ላይ ይቀመጣሉ።
ምሽት ላይ ቅዝቃዜ ሲሆን የሚለብሱት ብርድ ልብስ ስለሌለ ሰውነታቸውን በቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ እንደሚሸፍኑ ይናገራል።
"የሞት ፍርደኛ መሆን የሚፈጥረው ስጋት ላይ በተጨናነቀ ሁኔታ መቆየቱ ለበሽታ እና ለጭንቀት አጋልጦናል" ይላል ደስታ።
"ጠባቂው በሩን የሚከፍተው አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ ለማስገባት ነው። አፍ እና አፍንጫውን በጭምብል ይሸፍናል። በሩ የሚከፈተው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። ምግቡን ከሰጠን በኋላ በፍጥነት በሩን ቆልፎ ይሄዳል።
"ማንኛውንም ጥያቄ መጠየቅ ወይም ማነጋገር አይቻልም። ጥያቄ ከጠየቅክ ከፍተኛ ድብደባ ይደርስብሀል።"
ከየመን ድንበር ለመሻገር ሲሞክር ከታሰረ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኗል። አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ተከስሷል።
"ሦስት ኢትዮጵያውያን ነበርን፤ አንድ የመናዊም ከእኛ ጋር ነበር። ደኅንነቱ የተጠበቀውን መንገድ ስለሚያውቅ ድንበር ለመሻገር እንደሚረዳን ነገረን። ለዚህም በምላሹ ጫት የያዘ ጥቅል ከወሰድን ገንዘብ እንደሚከፍለን ቃል ገባልን።
"የሚያሳዝነው ተሻግረን ብዙም ሳይቆይ በፖሊሶች ተያዝን። ጥይት ተኮሱብን፤ የመናዊው ሮጠ፤ እኛ ግን አልቻልንም። ደንግጠን ነበር፤ ወደ የት እንደምንሄድም የምናውቀው ነገር አልነበረም።"
ቢቢሲ እንዳነጋገራቸው ሌሎች እስረኞች ደስታም የሞት ፍርድ ይፈረድብኛል ብሎ አልጠበቀም። የእስር ጊዜውን ጨርሶ ወደ አገሩ እንደሚመለስ ነበር የሚያምነው።
ሆኖም ግን እሱም በአረብኛ የተጻፈ የሞት ቅጣትን የሚጠቅስ ሰነድ ላይ እንዲፈርም እንደተገደደ ይናገራል።
ኋላ ላይ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ውሳኔውን ለመገዳደር እንዳልተፈቀደለት እና የጠበቃ ውክልናም እንዳልነበረው ይናገራል።
ደስታ "የመጀመሪያ ቀን ዳኛው ጋር ስትቀርብ 'ክሱን ትቀበላለህ?' ብሎ ይጠይቅሀል። ለሁለተኛ ጊዜ ስትቀርብ ሞት ይፈርድብሀል" ይላል።
ግንበኛ ስለሆነ ቤተሰቡን ለመደገፍ በመቸገሩ፣ ጦርነቱ ወደ ቤቱ እየተቃረበ ሲሄድ ከትግራይ ወጥቷል።
አሁን በድጋሚ ለሕይወቱ ፈርቷል። እሱ፣ ሀብቶም እና ብዙዎች የሞት ፍርድ የተወሰናቸው እርዳታ እንዲደረግላቸው ይማጸናሉ።
ሀብቶም "አንድ እስረኛ ሌላኛውን ማጽናናት አይችልም። ከማልቀስ ውጭ አማራጭ የለንም። መቼ እንደሚሆን ባናውቅም ተራችንን እየጠበቅን ነው" ይላል።
"በጥልቅ ፍርሃት ውስጥ እየኖርን ነው። የሚሰጠንን ምግብ መብላት እንኳን አልቻልንም።"