በደቡብ አፍሪካ ሰባት ሴቶች ተገድለው መገኘታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Thuthuka Zondi/BBC
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ ሰባት ሴቶች ተገድለው አስከሬናቸው መገኘቱን ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በጆሃንስበርግ በሁለት ወራት ውስጥ በርካታ ሴቶች ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ ወንጀሉን የፈጸሙትን ግለሰቦች ለመያዝ "የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም" ብለዋል።
በጆሃንስበርግ ሰሜን ምሥራቅ በሚገኘው ኬምፕቶን ፓርክ ከተማ በርካታ ሴቶች ተገድለው ተገኝተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ጠዋት የአንዲት ሟች አስከሬን የተገኘ ሲሆን ፖሊስ በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ እርቃናቸውን ተገድለው የተገኙ ሰባት ሴቶችን ሞት እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
ፕሬዚዳንቱ "እነዚህ ወንጀሎች በማኅበረሰባችን መካከል ፍርሃት እና አለመረጋጋትን እየፈጠሩ ነው፤ በተለይ ደግሞ በሴቶች ዘንድ" ብለዋል።
ፖሊስ ግድያዎቹን አንድ ግለሰብ የፈጸማቸው ወንጀሎች ስለመሆናቸው ድምዳሜ ላይ ባይደርስም ቡድኖች ከወንጀሉ ጀርባ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ብርጋዴር አትሌንዳ ማቴ "እነዚህ እዚህም እዚያም የሚፈጸሙ ተመሳሳይ ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገርግን እስካሁን ድረስ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ፍንጭ አላገኘንም" ብሏል።
ከመጀመርያው አስከሬን ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እስካሁን ድረስ ተገድለው ከተገኙት ሰባት ሴቶች መካከል ማንነታቸው የታወቀው የሁለቱ ብቻ ነው።
ሰኞ ዕለት ፖሊስ ከሟቾቹ መካከል አንዷ ሯጭ የነበረችው እና ከሕዝብ ዕይታ በመጥፋቷ መነጋገሪያ ሆና የነበረችው ኤሊዛቤት ሞሴላክጎሞ እንደምትባል አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በዚህ ወንጀል ላይ የሚደረገው ምርመራ ቅድሚያ እንዲሰጠው ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረው "የሕግ አስከባሪ አካላቶቻችን መረጃዎችን ለማጠናቀር፣ የማኅበረሰቦቻችንን ደህንንት ለመጠበቅ እና ወንጀለኛውን ወይንም ወንጀለኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ በፍጥነት እየሰሩ ነው" ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በአማካኝ በዓለም ላይ ከሚገደሉ ሴቶች መካከል በአገሪቱ የሚገደሉት አምስት እጥፍ እንደሚበልጥ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የሴቶቹ አስከሬን ሲገኝ በመላ አገሪቱ ቁጣን እና ፍርሃትን የቀሰቀሰ ሲሆን በርካቶች የአገሪቱ መንግሥት ሴቶችን ለመከላከል ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም ሲሉ ተችተዋል።
ሞሴላክጎኦ አስከሬን ቅዳሜ ዕለት በቤተሰቦቿ ከተገኘ በኋላ ማንነቷ ሰኞ ዕለት መለየት ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በየዕለቱ ከምታደርገው ሩጫ አለመመለሷ ያሳሰባት ልጇ ለፖሊስ አመልክታ ነበር።
የመጀመርያዋ ሟች ሴት አስከሬን የተገኘው በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን ሁለተኛዋ በነሐሴ ወር መጨረሻ የቀሪዎቹ ደግሞ በጳጉሜ ወር ውስጥ ሁለቱ ደግሞ ባለፉት ሁለት ቀናት ተገኝቷል።
ማክሰኞ ዕለት ፖሊስ ጳጉሜ ውስጥ በኬምፕቶን ፓርክ የተገኘው አስከሬን ምርመራ ከሚያደርጉባቸው ሟቾች ዝርዝር ውስጥ መካተቱን እና በአጠቃላይ ሰባት ሴቶችን ግድያ እየመረመሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ፖሊስ በኬምፕቶን ፓርክ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች "በተለይ ሰዋራ በሆኑ ሥፍራዎች" ብቻቸውን እንዳይንቀሳቀሱ አስጠንቅቋል።
የደቡብ አፍሪካ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ኮሚሽን የኬምፕቶን ፓርክ ነዋሪዎች ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማምጣት ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
"እነዚህ ሞቶች የሚያሳዩት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሴቶች፣ ተራ የሆነው የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው የሕይወትና ሞት ጉዳይ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ መኖራቸውን እንደቀጠሉ ነው" ሲል ገልጿል።
"ሴቶች እንደ መሮጥ፣ ወደ ሥራ በእግር መሄድ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም፣ ወደ ቤት መመለስ፣ ጓደኞቻቸውን መጎብኘት እና በማኅበረሰብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ የመሳሰሉ ተራ ተግባራት ሕይወታቸውን ለአደጋ ሊያጋልጡ ይችሉ እንደሆነ ስጋት ሳይገባቸው መከወን መቻል አለባቸው።"















