ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ለጀማሪ ወታደሮች የ80% ደመወዝ ጭማሪ አደረጉ
የናይጄሪያ ወታደሮች እስከ 80% የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግላቸው መሆኑ ተገለጸ።
በአንድ ወር ውስጥ ለወታደሮች የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ፤ የአገሪቱን ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ለመቀልበስ እየሠሩ ለሚገኙት ወታደሮች "ከፍተኛ አድናቆት" ለማሳየት ያለመ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል።
ሐምሌ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር ዝቅተኛ የውትድርና ወለል ላይ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን ደመወዝ ከ36 ዶላር ወደ 73 ዶላር ከፍ አድርጓል።
አሁን ላይ ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሠረት ከመስከረም ጀምሮ ደመወዛቸው 132 ዶላር ይሆናል።
የናይጄሪያ መንግሥት ለወታደሮች ባደረገው ጭማሪ ከጀማሪ ወታደር እስከ ሳርጀንት ያሉት ዕርከኖች በ80% ደመወዛቸው ከፍ ይላል። ከወታደራዊ ኦፊሰር እስከ ኮሎኔል ላሉት 50% እና ከብርጋዲየር ጄነራል እስከ ጄነራል ላሉት ዕርከኖች ደግሞ 30% ጭማሪ ተደርጓል።
በናይጄሪያ የተለያዩ አካባቢዎች ተባብሶ የቀጠለውን ነውጥ ለማርገብ ፕሬዝዳንቱ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል።
ኢስላሚስት ታጣቂዎች እና ሰዎችን ለገንዘብ የሚያግቱ 'ሽፍቶች' አገሪቱን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ወር ለአገሪቱ ጦር የማስፋፊያ ዕቅድ ፈቃድ መስጠታቸው ይታወሳል።
የአገሪቱን ጦር አቅም ለማስፋፋት የተያዘው ዕቅድ የደኅንነት ስጋትን ለመቀልበስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የማስፋፊያ ዕቅዱ 28,000 ተጨማሪ ወታደሮችን መመልመል እና አራት ወታደራዊ ዕዞችን መጨመርን ያካትታል።
የአገሪቱ አለመረጋጋት በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ዋነኛ አከራካሪ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኗል።
ፕሬዝዳንቱ የደመወዝ ጭማሪን ባደረጉበት ወቅት፤ እየተስፋፋ የመጣውን የሽፍቶች እንቅስቃሴ፣ እገታ እና ሽብርን እየታገሉ ያሉ የሠራዊቱ አባላት "እየከፈሉ ለሚገኙት መስዋዕትነት" ምስጋና አቅርበዋል።
"ለአገራችን ግዴታቸውን እየተወጡ ደኅንነታችንን የሚጠብቁ ወንዶች እና ሴቶች ሊደገፉ እና ሊመሰገኑ ይገባል" ብለዋል።
የደመወዝ ጭማሪውን ወታደሮች ለአገራቸው ለሰጡት አገልግሎት "የጥልቅ ምስጋና ማሳያ" አድርገው እንዲወስዱትም ጠይቀዋል።
"በአንድነት የአገራችንን ሥሪት ለማፍረስ የሚሞክሩ ጠላቶቻችንን እናሸንፋለን" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የአገሪቱ መሪዎች ወታደራዊ ስምሪትን እና ለጦሩ የሚመደብ ወጪን በማስፋት መረጋጋት ለማስፈን ያደረጉት ጥረት ብዙም ስኬታማ አልሆነም።
ታጣቂ ኢስላሚስቶች፣ ተገንጣዮች እንዲሁም ንጹኃንን አግተው ገንዘብ የሚጠይቁ ወንጀለኛ ቡድኖች ለአገሪቱ የደኅንነት ስጋት ሆነዋል።
እንደ ቦኮ ሀራም እና በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው የኢስላሚክ ስቴት ክንፍ ያሉ ኢስላሚስት ታጣቂዎች በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል።
በሰሜን ምዕራብ እና ሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በከፍተኛ መጠን የታጠቁ የወንጀል ቡድኖች ሰዎችን በማገት ገንዘብ ይጠይቃሉ።
አዲስ በተደረገው የደመወዝ ጭማሪ መሠረት የወታደሩ ዓመታዊ በጀት ከ484 ሚሊዮን ዶላር ወደ 678 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ይላል።
ጡረታ የወጡት ሜጀር ጄኔራል ባሽር ጋልማ "ይሄ ለረዥም ጊዜ ስንጠይቅ የነበረው ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀጣይ መንግሥታት ይህንን አይነቱን በጀትን ማስቀጠል መቻላቸው ላይ ግን ጥያቄ አላቸው።
ሌሎች የደኅንነት መሥሪያ ቤቶችም ጭማሪ በማድረግ "አገሪቱን ለመጠበቅ የሚደረገውን የጋራ ጥረት መደገፍ እንዳለባቸው" ገልጸዋል።
ከደመወዝ ጭማሪ ባሻገር የወታደሮች መለያ ልብስ፣ ጫማ እና አዳዲስ መሣሪያ ማቅረብ ትኩረት እንደሚሹም አክለዋል።
ቢቢሲ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው ወታደሮች የደመወዝ ጭማሪው እስከሚተገበር ድረስ ምንም ማለት አልፈለጉም።
ፕሬዝዳንት ቲኑቡ እንዳሉት የወታደሮችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ጦሩን የሚያዘምኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለማቅረብ አስተዳደራቸው ቁርጠኛ ነው።