የሌ/ጄነራል ታደሰ ጠባቂዎች "እንደተቀየሩ" እና ወደ ቤታቸው "መግባት እና መውጣት" እንደማይቻል የቢቢሲ ምንጮች ገለጹ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደን መኖሪያ ቤት ሲጠብቁ የነበሩ የፀጥታ ባልደረቦች ትናንት ምሽት "እንደተቀየሩ" እና ቤተሰባቸውም "ወደ ውጭ መውጣት" እንዳልቻለ ቢቢሲ ከምንጮቹ ለመረዳት ችሏል።

የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቅርብ ቤተሰብ እንደገለጹት፤ ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ምሽት "ወደ 4 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ" ከዚህ ቀደም የነበሩት ጥበቃዎች በሌሎች ተተክተዋል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰን እንዲጠብቁ ተመድበው የነበሩት የፀጥታ አባላት ከተቀየሩ በኋላ ቤተሰባቸው "ከቤት መውጣት እንዳልቻለ" የቢቢሲ ምንጭ ተናግረዋል። ሌሎች ቤተሰቦቻቸው "ከውጭ ወደ ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውንም" አክለዋል።

ላለፉት ሦስት ወራት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ "እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ከቤት ሳይወጡ" እንደቆዩ የገለጹት የቅርብ ቤተሰብ፤ በትግራይ ክልል አስተዳደር የተመደቡ "ወደ አምስት የሚደርሱ ጠባቂዎች እየተለዋወጡ ጥበቃ ያደርጉ እንደነበር" ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ለሌተናንት ጄነራል ታደሰ የተመደቡት የጥበቃዎች ቁጥራቸው ተቀንሶ የቀሩት "ወደ አምስት የሚደርሱ ጠባቂዎች" ትናንት "መለወጣቸውን" አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩት ጠባቂዎች በሌሎች እንደሚለወጡ "አያውቁም ነበር" ያሉት የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቅርብ ቤተሰብ፤ "ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ጨርሳችኋል" ሲሉ ለቀድሞዎቹ ጠባቂዎች መንገራቸውን አስረድተዋል።

"[የተቀየሩት ጠባቂዎች] ትናንት [ረቡዕ] በአራት አቅጣጫ አካባቢውን ዞሩት። ድንገት ወደ ጊቢው መጡባቸው። እነሱም [የቀድሞ ጠባቂዎች] በማያውቁት ሁኔታ ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ጨርሳችኋል አሏቸው።"

ከረቡዕ መስከረም 13 ጀምሮ እስከ ዛሬ ሐሙስ ድረስ በሌተናንት ጄነራል ታደሰ መኖሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ እና ከውጭም ያሉት ጠባቂዎች "ከ10 በላይ እንደሚሆኑ" በአካባቢው ያሉ የቢቢሲ ምንጭ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ለነበሩት ጠባቂዎች "በፖሊስ ኃይል ተተክቷል፤ እኛ ነን የምንጠብቀው፤ ውጡ፤ ከዚህ ሰዓት በኋላ ታግዳችኋል" ሲሉ መናገራቸውንም አክለዋል።

የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጠባቂዎችን የቀየሩት የፀጥታ ባልደረቦች "በማን እንደተመደቡ የሚገልጽ ወረቀት አለመያዛቸውን" የቢቢሲ ምንጭ ተናግረዋል።

በሌላ ቦታ የሚኖሩ የጄነራሉ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው ቢመጡም "ተጉላልተው መግባት ሳይችሉ" መቅረታቸውን የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሌተናንት ጄነራል ታደሰን የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት ማራዘሙን ካስታወቀ በኋላ ውሳኔውን የተቃወመው ህወሓት፤ ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገ ምርጫ የተቋቋመውን "የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" መመለሱ አይዘነጋም።

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ካቢኔ የመጀመሪያውን ስብሰባ ባደረገበት ዕለት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" መሆኑን መናገራቸውም ይታወሳል።

ከወራት በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቤተሰቦች "በቁም እስር ላይ ያሉ ያህል" እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ወደ መቀለ ተጉዘው ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር እንዲነጋገሩ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም "ከበላይ አካል የተላለፈ" በተባለ ትዕዛዝ ሳይገናኙ መቅረታቸውን ተናግረውም ነበር።

ትናንት ረቡዕ የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጥረው በረራዎች መቋረጣቸው ከተገለጸ በኋላ ግጭቶች በአማራ አና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ መካሄዳቸውም ተዘግቧል።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ግጭቱ እንዲረግብ የሚጠይቁ መግለጫዎች አውጥተዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች ጦርነት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

ትግራይን የሚያስተዳድሩት የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።