ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ 'በቁም እስር ላይ' ናቸው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ከሥልጣናቸው ከተወገዱ ወዲህ ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚያብራራ ተጨባጭ መረጃ አልወጣም።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ከሥልጣናቸው ከተወገዱ ወዲህ ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚያብራራ ተጨባጭ መረጃ አልወጣም።

ፌደራል መንግሥት ሌተናንት ጄነራል ታደሰን የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት ማራዘሙን የተቃወመው ህወሓት፤ ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገ ምርጫ የተቋቋመውን "የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" መልሷል።

ምክር ቤቱን የህወሓት ሊቀ መንበር የሆኑትን ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡም አይዘነጋም።

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ካቢኔ የመጀመሪያውን ስብሰባ ባደረገበት ዕለት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" መሆኑን ተናግረዋል።

በዕለቱ ፕሬዝዳን ጽሕፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ ባወጡት አጭር መግለጫ፤ " 'ተመርጠናል' የሚሉ አካላት ዛሬ" በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር "የካቢኔ ስብሰባ አዳራሽ የካቢኔ ስብሰባ" መጀመራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ አካላት በአመራርነት የተመረጡት "ችግሩ በውይይት እና የጋራ መግባባት እንዲፈታ የቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው" እንደሆነ በማንሳትም ወቅሰዋል።

የካቢኔ ስብሰባ የተጀመረበትን ቀን "ቀጣይ አደገኛ መንገድ የተጀመረበት ዕለት" እንደሚያደርገው ገልጸው፤ "በዚህ ምክንያት ለሚከተለው መዘዝ ተጠያቂው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን በጉልበት እየያዘ ያለው ኃይል መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ይህንን የመጨረሻ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ፣ በምን ሁኔታ እንደሚገኙ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። ቢቢሲ ትግርኛም ሁኔታውን ለማጣራት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

ረቡዕ ዕለት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ወደ መቀለ መጓዛቸውን ተከትሎ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ለማወቅ ተጨማሪ ጥረት ተደርጓል። ለመጀመሪያ ጊዜም ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ተጨባጭ መረጃ ማግኘት ተችሏል።

በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ቅርብ ቤተሰባቸው ለቢቢሲ ትግርኛ እንደገለጹት፤ አምባሳደር ማሲንጋ ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ተጉዘዋል።

"በእርግጥ አምባሳደር ማሲንጋ ጄነራል ታደሰን ለማግኘት የሞከሩት አሁን ብቻ አይደለም። ከዚህ በፊትም ሞክረው አልተሳካላቸውም" ያሉት የጄነራሉ የቅርብ ዘመድ ከዚህ ቀደም የተያዘው ቀጠሮ መሰረዙን ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት ረቡዕ የተያዘው ቀጠሮ ሁለተኛ ሙከራ እንደነበርም አክለዋል።

"የትናንቱ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ 'ይገናኛሉ' የሚል ተስፋ ነበረን። ቀጠሮው ከቀኑ 5 ሰዓት ነበር። እሳቸውም ቀጠሮ እንዳላቸው ያውቁ ነበር። አምባሳደሩ መቀለ እንደገቡም ያውቁ ነበር። ከዚያ ግን 4 ሰዓት ገደማ ለዋና የደኅንነት ኃላፊው ስልክ ተደውሎ ትዕዛዝ ተላልፏል" ብለዋል።

ይሄንን መረጃ ለማረጋገጥ ከሰላም፣ ፀጥታ እና ደኅንነት ቢሮ ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

ትዕዛዙ ምን ነበር?

የሌተናንት ጄነራል ታደሰ እና አምባሳደር ማሲንጋ ቀጠሮ አንድ ሰዓት ያህል ሲቀረው ከቪአይፒ ጥበቃ ኃላፊ በተደወለ ስልክ ሁኔታው እንደተቀየረ የቢቢሲ ምንጭ ይናገራሉ።

"ምንም ዓይነት አጀባ አታድርጉ፤ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አታካሂዱ፤ ተሽከርካሪዎች አይንቀሳቀሱ፤ ይህንም ለራሱ [ለጄነራል ታደሰ] አሳውቁት" የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠ ገልጸዋል።

በተጨማሪም "ይህ ትዕዛዝ ከተላለፈ በኋላ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ብታደርጉ ሊያስቆማችሁ የሚችል ሌላ ኃይል አለ። ስለዚህ ምንም ችግር እንዳይፈጠር ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ አታድርጉ" የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን አክለዋል።

ይህ መመሪያ ለሌተናንት ጄነራል እንዲሁም ለአሽከርካሪዎቻቸው እና ረዳቶቻቸው እንዲነገር ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

የጥበቃቸው ኃላፊ ይህን ትዕዛዝ ለሌተናንት ጄነራል ታደሰ ካሳወቃቸው በኋላ ጄነራሉ ትዕዛዙን እንዳልተቀበሉት እና "እኔ ራሴ መኪና ነድቼ እሄዳለሁ" ማለታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ይህም በጥበቃ አባሎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቅርብ ዘመድ ገልጸዋል።

በተለይም ቤተሰቦቻቸው "እባክህ ተወው፤ ባለው ሁኔታ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም" በማለት እንደለመኗቸው እና እንዳይወጡም እንዳሳሰቧቸው ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር ለመገናኘት ተስፋ አድርገው እንደነበር ጠቅሰውም፤ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቤተሰባቸውን ምክር ተቀብለው ከቤት ሳይወጡ እንደቀሩ ተናግረዋል።

ያለውን ሁኔታ ለአምባሳደር ማሲንጋ ደውለው እንዳስረዱም ገልጸዋል።

ይህ የስልክ ውይይት "20 ደቂቃ እንደወሰደ" ቢገልጹም የውይይቱ ይዘት ምን እንደነበር ለማወቅ አልተቻለም።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ "ይህ ክስተት አንድ ክልል ሲመሩ የነበሩ ጄነራል የመናገር መብታቸው፣ ሰዎችን የማግኘት መብታቸው እና የመንቀሳቀስ መብታቸው በተግባር እንደታገደ ያሳያል" ሲሉ ገልጸዋል።

"ቢወጡ ኖሮ ምን ያጋጥማቸው ነበር?" ሲሉም ጥያቄ ሰንዝረዋል።

የተላለፈውን ትዕዛዝ በመጣስ የሌተናንት ጄነራል የጥበቃ አባላት "ብቻዎትን አንልክዎትም፤ አብረን እንሄዳለን" ቢሏቸው ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስካሁን ድረስ እንደሚያሳስባቸው አክለዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ ከህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋን ጨምሮ ከሌሎች የክልሉ ባለሥልጣኖች ጋር ስለ ፕሪቶሪያ ስምምነት እና ስለ ተፈናቃዮች ሁኔታ ተወያይተው እንደተመለሱ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ጄኔራል ታደሰ በቁም እስር ላይ ናቸው?

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በሥልጣን ላይ ሳሉም ሆነ እንደ ወታደራዊ ኃላፊ ብዙ የሥራ ጫና ስለነበረባቸው ከዚህ ቀደምም ብዙ ጊዜ ወጥተው ይንቀሳቀሱ እንዳልነበር ይነገራል።

ነገር ግን ከረቡዕ በኋላ "በቁም እስር ላይ እንዳሉ ነው የተሰማን" ሲሉ የቅርብ ቤተሰባቸው ተናግረዋል።

ሚያዝያ 30 ከሥልጣናቸው ተነስተው በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን እንደተተኩ ከተገለጸ በኋላ፣ ወደ ፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ሄደው እንደማያውቁ እና ከክልሉ አስተዳደር ጋርም ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ተነግሯል።

ሆኖም ከመኖሪያ ቤታቸው አጠገብ ወዳለው የግል ቢሯቸው እንደሚሄዱ እና አብዛኛውን ጊዜያቸውን ቤት ውስጥ መጻሐፍት በማንበብ እንደሚያሳልፉ የቢቢሲ ምንጮች ይናገራሉ።

በዚህ ቢሯቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በፕላኔት ሆቴል ሰዎችን ያገኙ እንደነበር ተገልጿል። ሆኖም ይህ የሚሆነው "በባለሥልጣናቱ ፈቃድ እና በደኅንነት ቁጥጥር ሥር ነው" የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በትግራይ ያለው ውጥረት የሚያሳስባቸው ወገኖች ሌተናንት ጄነራል ታደሰን ለማግኘት እንደሚፈልጉ የጠቆሙት ምንጮቹ፤ በእርግጥም እሳቸውን ያገኙ አካላት እንደነበሩ ገልጸዋል።

ለምሳሌ "ከአውሮፓ ኅብረት የተላኩ ተወካይ እንደሆኑ የሚታመን አንድ የቀድሞ ኖርዌይ አምባሳደር" ከአንድ ሳምንት በፊት እንዳነጋገሯቸው ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ጋርም ለመገናኘት እንደሚፈቀድላቸው ገምተው እንደነበር ገልጸው፤ "እንዳይገናኙ ስለፈለጉ ያስቆሙት ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ከረቡዕ ዕለቱ ክስተት በኋላ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ "በራሳቸው የሚቆጣጠሩት ነገር እንደሌለ" በመጥቀስ ወደፊት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ቤተሰባቸውን እጅግ እንዳሳሰበ ቢቢሲ ከእነዚህ ምንጮች ተረድቷል።

እስካሁን ድረስ ጥበቃቸው እና ተሽከርካሪያቸው ቢኖሩም፤ ቀስ በቀስ ጥበቃዎቻቸው እየተቀነሱ እንደሆነ ጠቁመዋል። ተሽከርካሪያቸውም "ሊወሰድ እንደሚችል" ጭምጭምታዎች መሰማታቸውን አክለዋል።

"[የረቡዕ ዕለቱ] ትዕዛዝ በጣም የሚያስቆጣ እና የሚያበሳጭ ነበር። የመናገር እና የመንቀሳቀስ መብታቸው እንደተገደበ ያሳያል" ብለዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ከሁለት ወራት በላይ ከቤታቸው ብዙም ባይወጡም፣ የረቡዕ እርምጃ ግን አሳሳቢ እና "በቁም እስር ላይ" እንዳሉ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን እነዚህ ምንጮች ገልጸዋል።

ቀድሞ ከነበረው ጥበቃ በተጨማሪ ሌላ "የተመደበ የጥበቃ ቡድን" እንዳለ መነገሩን በተመለከተ መረጃ የተጠየቁት የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቅርብ ዘመድ "በትክክል ባያውቁም" ጥርጣሬ እንዳላቸው አልሸሸጉም።

"መንቀሳቀስ አትችልም" የሚል ትዕዛዝ ተላልፎባቸው ከሆነ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ "ለመገመት አዳጋች አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

ውጥረት የተሞላበት ሁኔታ

የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራን በተመለከተ በፈራሚ ወገኖች መካከል የነበረው አለመግባባት ሚያዝያ 30 ቀን ወደተፈጠረው "መፈንቅለ ሥልጣን" የሚመስል ሁኔታ አምርቷል።

የህወሓት መሪዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን አብቅቷል በማለት ከጦርነቱ በፊት የተመረጠውን የክልሉን ምክር ቤት መልሰዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የህወሓትን እርምጃ በማውገዝ ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራ እንዲመለስ እየጠየቁ ይገኛሉ።

የአሜሪካ መንግስት "አክራሪ" ብሎ በጠራቸው እና ስማቸውን ባልገለጻቸው የህወሓት መሪዎች እና የቤተሰብ አባላቶቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ ጥሏል።

ህወሓት የአሜሪካን የቪዛ እገዳ "ሚዛናዊ ያልሆነ" ሲል ውድቅ አድርጎታል።

አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ "በትግራይ ያለውን እውነታ የማያንጸባርቅ እና የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂነት ያላደረገ ነው" ሲልም ተችቷል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን እና በሞት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን የያዘው አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በትግራይ የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ መከናወኑን አጥብቀው ቢያወግዙም የህወሓት መሪዎች "ብሔራዊ ህልውናችን ላይ አደጋ ተጋርጧል" በማለት ይከራከራሉ።

ውጥረቱ እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "በዚያ ክልል ጦርነት እንዲነሳ ሰፊ ፍላጎት አለ፤ ጥቅም ስለሌለው ግን እምቢ ብለናል" ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉም ተደምጠዋል።