ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ "የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ቢኖሩም ተቆጥባ እንደቆየች" ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ
ኢትዮጵያ "የውጭ ጣልቃ ገብነቶች" ቢኖሩም እንኳን "በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጥባ" እንደቆየች እና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት "እንዳሻሻለች" ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት ስላላት ድርሻ መግለጻቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት በፌደራል ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደ አዲስ በተቀሰቀሰበት ወቅት ነው።
ትናንት ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ማለዳ የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ከተገለጸ በኋላ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች ውጊያዎች መካሄዳቸው ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ታዬ፤ በተመድ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሯን በማጠናከር እና በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የሚደረጉ ጥረቶችን ብትደግፍም "የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እየገቡ" እንደሆነ ጠቁመዋል።
እነዚህ የውጭ ኃይሎች ማን እንደሆኑ በስም አልጠቀሱም።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ትናንት ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ አጎራባች አገራት ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጥረት እና ወታደራዊ መካረር "እጅግ እንዳሳሰባቸው" ገልጸውም ጎረቤት አገራቱ "ግጭቱ እንዲቆም እና ንግግር እንዲደረግ" ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት ቀጣናውን ወደተባባሰ ነውጥ እንዳይወስደው ተሰግቷል። በቀይ ባሕር ዙርያ ያለው ውጥረት እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነትም እንደቀጠለ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ "በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ውስጥ የጠላቶች ጣልቃ ገብነት ቢቀጥልም በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጥበን ቆይተናል" ሲሉ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መናገራቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያትታል።
"ለአጥፊ እና አውዳሚ ኃይሎች የምናስተላልፈው መልዕክት ግልጽ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ሰዎች በሰላም እና በብልጽግና የመኖር መብታቸውን እንዲያከብሩ እናሳስባለን" ሲሉም አክለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች "ጦርነት መክፈታቸውን" ገልጸዋል።
ትግራይን የሚያስተዳድሩት የህወሓት መሪዎች ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ተከፈተብን" ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው "እርምጃ እንዲወስዱ" መታዘዛቸውን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ህወሓት "በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ፣ በወሰማና በሌሎች አካባቢዎች" ላይ ጦርነት "መክፈቱን" አስታውቋል።
ህወሓት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን (ኦነሠ) ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱት 'የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና' የተባለው ጥምረት ትናንት ባወጣው መግለጫ በፌደራል መንግሥቱ "በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጥቃቶች" እንደተከፈቱ ገልጿል።
የጥምረቱ አባል ድርጅቶቹ "በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በዋግሕምራ፣ በአፋር ክልል ሰሜናዊ ቀጠናዎች" ላይ "ፀረ ማጥቃት" እያደረጉ እንደሆነም ጠቅሷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ፤ በደቡብ ትግራይ እና በአፋር ክልል ግጭት እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው የተናገሩ ሲሆን፤ አያይዘውም በቅርቡ በታጣቂ ኃይሎች የተፈጠረው ጥምረት "አለመረጋጋቱን እንደሚያባብስ" ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት በተመለከተ የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" ከስሰዋል።
አምባሳደሩ ጨምረውም "ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ" አሳስበው፤ አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት አመልክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ፤ የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በመግለጫዎቹ "ማዘናቸውን" ገልጸዋል።
አቶ አማኑኤል፤ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ በዝምታ ቆይተው አሁን የሰነዘሩት ወቀሳ "ፍትሐዊ አይደለም" ብለዋል።