ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ1994ቱን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት በተመለከተ በዩኬ የመጀመሪያው ክስ ቀረበ
በሰሜን ለንደን የሚኖር አንድ ሩዋንዳዊ ግለሰብ እአአ በ1994 ከተፈፀመው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በዩናይትድ ኪንግደም ክስ የቀረበበት የመጀመሪያው ሰው መሆኑን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
በቀድሞ ስሙ ዶ/ር ቪንሰንት ባጂንያ በመባል የሚታወቀው የ65 ዓመቱ ዶ/ር ቪንሰንት ብራውን ከዘር ማጥፋት ጋር ተያያዥ በሆነ አንድ የተባባሪነት ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል አካል ከሆነ ግድያ ጋር በተያያዙ ስድስት የተባባሪነት ወንጀሎች ተከስሷል።
በዐቃቤ ሕግ አገልግሎት የልዩ ወንጀሎችና ፀረ ሽብርተኝነት ክፍል ኃላፊ ፍራንክ ፈርጉሰን፣ ብራውን "ሌሎች ሰዎች የፈጸሟቸው የግድያና የዘር ማጥፋት ድርጊቶች እንዲፈጸሙ መመሪያ ሲሰጥ እና ሲቀሰቅስ ነበር" ተብሎ መከሰሱን ተናግረዋል።
ብራውን ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12 በዌስትሚኒስተር ማጂስትሬትስ ፍርድ ቤት ይቀርባል።
ፈርጉሰን እንደገለፁት፣ ብራውንን ለመክሰስ የተወሰነው "በሜትሮፖሊታን ፖሊስ የጦር ወንጀሎች ቡድን የቀረበ የማስረጃ ፋይል ከተመረመረ በኋላ" ነው።
"የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሕግ መስፈርቶቻችን ስለመሟላታቸው ድምዳሜ ላይ ደርሰናል" ሲሉም አክለዋል።
የጦር ወንጀሎች ቡድኑ ምርመራውን በአውሮፓውያኑ መስከረም 2019 የጀመረ ሲሆን፣ ይኸውም የሩዋንዳ መንግሥት በኪጋሊ ሩገንጌ ግዛት ውስጥ ሚያዝያ 1994 በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን እንዲመረምር በይፋ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
በ1994፤ በ100 ቀናት ውስጥ፣ በሩዋንዳ በግምት 800,000 የሚሆኑ የቱትሲ ብሔረሰብ አባላት እና ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ሁቱዎች በአክራሪ ሁቱዎች ተገድለዋል።
አክራሪዎቹ ሁቱዎች፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቱትሲ ማኅበረሰብ አባላትን እንዲሁም የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ የጎሳ ማንነታቸውን ሳይለዩ ኢላማ ያደረገ ጥቃት ነበር የፈፀሙት።
ከዘር ማጥፋቱ ወንጀል በኋላ ሥልጣን የያዙት በዋነኝነት የቱትሲ ኃይሎች በበቀል ድርጊት በሺዎች የሚቆጠሩ የሁቱ ተወላጆችን ገድለዋል ተብለው ተከሰዋል።
የሜትሮፖሊታን ፖሊስ እንዳለው፣ በብራውን ላይ ክስ የቀረበው "ለሰባት ዓመታት ከተካሔደ ውስብስብ እና ሰፊ ምርመራ" በኋላ ነው።
"ይህ እርምጃ ዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ሰርተዋል ተብለው ለሚጠረጠሩ ግለሰቦች መሸሸጊያ አለመሆኗን ያሳያል" ሲሉ የለንደን ፀረ-ሽብርተኝነት ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ሄለን ፍላናጋን ተናግረዋል።
አክለውም "የጦር ወንጀሎች ቡድኑ በዘር ማጥፋትና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራቱን ይቀጥላል" ብለዋል።
"በዩኬ ውስጥ በሚኖሩ ሌሎች ግለሰቦች ላይም ከሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ጋር ተያያዥ በሆኑ ተመሳሳይ ወንጀሎች ዙሪያ በርካታ ምርመራዎች አሁንም በመካሄድ ላይ ናቸው።"