ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትብብር የመሠረቱት ታጣቂ ቡድኖች አንድ የሚያደርጋቸው እና የሚያለያያቸው ምንድን ነው?
ሰባት ታጣቂ ቡድኖች "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን እሁድ መስከረም 10/2019 ዓ.ም. አስታውቀዋል።
ይህንን ትብብር ከመሠረቱት የትጥቅ ቡድኖች መካከል የተወሰኑት በአንድ ወቅት በጠላትነት የሚተያዩ እና እርስ በርስ የተዋጉ ነበሩ።
የአማራ ፋኖ እና ህወሓት ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውቅት በተለየየ ወገን በመሆን ውጊያ አካሄደዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኘው እና ህወሓት በኃይል ተወስዶብኛል የሚለውን ግዛት አሁንም ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ትብብር ለኅልውና በሚል የተመሠረተው አዲስ የታጣቂ ቡድኖች ስብስብን የሚመራው ዘመነ ካሴ በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርቦ ባነበበው መግለጫ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት ለመጣል እና "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል።
ይህንን መግለጫም ሌሎቹ የትብብሩ አባላት በራሳቸው መንገድ ተቀብለው በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርተውታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ አማካሪ እና የቀድሞው ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ግብፅ እና ኤርትራን ታጣቂ ቡድኖችን በማደራጀት ከስሰዋል።
ሁለቱም አገራት የሚቀርብባቸውን ውንጀላ በተለያየ ጊዜ አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ታጣቂ ቡድኖች የፈጠሩት ትብብር ምን ዓይነት አደጋ ይደቅንበታል?
ጥምረት የፈጠሩት ቡድኖች እነማን ናቸው?
የአፋብን መሪ የሆነው ዘመነ ካሴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርን ለመጣል ጥምረቱን የመሠረቱትን ሰባት ቡድኖች ሲዘረዝር ከእራሱ ቡድን በተጨማሪ ህወሓት፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የኦጋዴን ሕዝብ ነፃነት ግንባር እና የአፋር ብሔራዊ አንድነት ግንባር አባላት እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
ዘመነ ከብዙ ጥረት እና ትግል በኋላ ተመሠረተ ያሉትን ትብብር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ህወሓት በየግል ገጻቸው ላይ አረጋግጠዋል።
የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ቃል አቀባይ የሆኑት እና ከአገር ውጪ የሚገኙት አቶ አብዲከድር አዳኒ ሂርሞጌ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላቸው ተስፋ በመሟጠጡ ትብብሩን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
ዘመነ ከመግለጫው በፊት 'ሌ ትምፕስ' ከተባለ የስዊትዘርላንድ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ "ይህ ከትግራት ኃይሎች ጋር በመነጋገር የተወሰነ ነው" ብለዋል።
ታጣቂ ቡድኖቹ ላለፉት ሰባት ወራት ሲነጋገሩ መቆየታቸውን ዘመነ ለጋዜጣው ተናግሮ ነበር።
የአፋብን ቃል አቀባይ የሆነው አስረስ ማረ ዳምጤ በበኩሉ ከህወሓት እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የተፈጠረው ትብብር ለኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አማራጭ አስተዳደር የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ በትብብሩ ውስጥ አባል መሆኑን አረጋግጦ፣ በኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱት እና ራሳቸውን ፋኖ ብለው ከሚጠሩ ቡድኖች የአማራ ኃይሎች ራሳቸውን እንዲያርቁ ጥሪ አቅርቧል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፈው ሳምነት ባወጣው መግለጫ ትብብሩ በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል።
አንደኛ፣ የተቃዋሚ ኃይሎች "እርስ በርስ የሚያደርጉትን ሽኩቻ" አቁመው ትኩረታቸውን በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ላይ እንዲያደርጉ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውን "በቀጥታ በመሳተፍ የሚፈቱበትን ሰፊ መሠረት ያለው የሽግግር መድረክ" ለመፍጠር መሆኑን አክሏል።
ሠራዊቱ በመግለጫው የአማራ ኃይሎች ከክልሉ ውጪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ "በመተባበር፣ ሊገኝ ከሚችለው የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ጥቅም እጅግ የላቀ የፖለቲካ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ" አለው ብሏል።
አክሎም "የአማራ ኃይሎች ይህን ቡድን በተመለከተየሚያደርጉትን ኃላፊነት ከጎደለው የሚዲያ ንግግሮች እንዲታቀቡ እና ከዚህ ቡድን ጋር ያላቸውን ግንኙንት በግልጽ እንድያቋርጡ" ጠይቋል።
የፌደራል መንግሥቱ ምን ዓይነት ስጋት ተደቅኖበታል?
ህወሓት እና አፋብን ባላቸው የአደረጃጀት አቅም እና በየአካባቢው ባሏቸው ታጣቂዎች ምክንያት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር ትልቁን ፈተና የሚፈጥሩ ኃይሎች እንደሆኑ በሰፊው ይታመናል።
በተጨማሪም፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና ሌሎች ቡድኖችን ጨምሮ፣ በህወሓት እና በአፋር ብሔራዊ አንድነት ግንባር የሚካሄድ ወታደራዊ ዘመቻ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር ይችላል።
ሠራዊቱ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጫና የደረሰበት ሲሆን፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ለዓመታት ሲካሄዱ በቆዩት የትጥቅ አመፆች ምክንያትም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።
እንዲህ ዓይነቱ ጥምረት፣ በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ጦርነት ወቅት ቡድኑ ካደረገው እንቅስቃሴ ጋር ሲነጻጸር፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ህወሓት የሚገጥመውን ተቃውሞ ሊቀንስ ይችላል።
ለሁለት ዓመት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች እጅግ ከፍተኛ ፍልሚያ የተደረገባቸው የጦር ግንባሮች ነበሩ።
የአፋብን እና የህወሓት ወታደራዊ አቅም ምን ይመስላል?
አፋብን የአማራ ክልል 80 እና 90 በመቶ በቁጥጥሩ ሥር አንደሚገኙ ይናገራል። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ደግሞ 95 በመቶ የአማራ ክልል ሰላማዊ ነው ብለዋል።
የአፋብን ቃል አቀባይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተጨማሪም ቡድናቸው ከክልሉ ውጪ እንደሚንቀሳቀስም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከቤንሻንጉል ክልል ታጣቂዎች ጋር ከክልሉ ውጪ ስልታዊ ትብብርን መፍጠሩን ንቅናቄው አስታውቋል።
ይሁን እንጂ አፋብን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ምን ያህል ቁጥጥር አለው የሚለውን ለማረጋገጥ ከባድ ነው።
ቡድኑ በአብዛኛው የአማራ ክልሎች ቁጥጥር እንዳለው ቢናገርም፣ በግንቦት ወር በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በክልሉ ድምጽ ያልተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች ስምንት ብቻ ናቸው።
አፋብን ያለው የሠራዊት ቁጥር በይፋ የሚታወቅ ባይሆንም በ2015 ዓ.ም. ነሐሴ ወር በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት፣ 50 በመቶዎቹ፣ ፋኖን መቀላቀላቸውን በወቅቱ የሰላም ሚኒስትር የነበሩት አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከዚያ በኋላ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ22 ሺህ በላይ ተዋጊዎች ትጥቃቸውን ፈትተው በተደረገላቸው ምህረት ወደ ኅብረተሰቡ መቀላለቀላቸውን ተናግሯል።
በሌላ ወገን ህወሓት በትግራይ ውስጥ በስፋት ይንቀሳቀሰሳል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ ተቋማት ላይ የፋይናንስ ድርጅቶችን ጨምሮ ሰፊ ተጽዕኖ አለው።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አቅሙ አሁንም አልተሟጠጠም።
በ2015 ዓ.ም. የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ከስምምነት ሲደረስ ከ270 ሺህ በላይ ተዋጊዎች እንደነበሩት ተገልጿል።
ነገር ግን ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል የቻሉት 63 ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው።
ትብብር የፈጠሩት ቡድኖቹ ምን ተግዳሮት ይገጥማቸዋል?
ትብብር የመሠረቱት ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የጋራ ጠላታቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት መሆኑን አውጀዋል።
ነገር ግን ቢያንስ ሁለቱ የትብብሩ አባል የሆኑት ቡድኖች ለረዥም ጊዜ የቆየ እና ያልተፈታ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ቅራኔ አላቸው።
ይህ ቅራኔ በማንኛውም ጊዜ ሊያገረሽ የመቻል ዕድሉ ሰፊ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች የሕዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው እንደማይሰጡ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህ ደግሞ ወልቃይት ጠገዴን እና የራያ አካባቢዎችን ያካትታል።
የፌደራል መንግሥቱ ከጦርነቱ በፊት የነበሩ የትግራይ ግዛቶችን ከአማራ ኃይሎች ነጥቆ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ አሁን በትብብሩ ውስጥ ያሉት የአማራ እና ትግራይ ኃይሎች መካከል ቁልፍ የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ሊቀጥል እችላል።
አፋብን "ቅንጣት ታክል" አማራን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም ሲል በተለያየ ጊዜ ተናግሯል።
ትብብሩ ሌላው ሊገጥመው የሚችለው ችግር የኃይል ሚዛን መዛባት ነው። ህወሓት ከአፋብን የበለጠ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተጋልጦ እና ግንኙነት ያለው ድርጅት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ከአማራ ክልል ተነጥለው የራሳቸውን ነጻ ግዛት መመሥረት ከሚፈልጉት የአገው እና ቅማንት ታጣቂ ቡድኖች ጋር አሁንም ግንኙነቱ ጠንካራ ነው።
እነዚህ ቡድኖች ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ በነበረባቸው ሁለት ዓመታት የቅርብ ድጋፍ በመስጠት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
ግብፅ እና ኤርትራ የሚከሰሱት በምንድን ነው?
የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓት እና አፋብን ከኤርትራ እና ከግብፅ ትዕዛዝ በመቀበል አገሪቱን ለማፍረስ እየሠሩ ነው ሲል ይወነጅላቸዋል።
ኢትዮጵያ ሁለቱን አገራት "ታሪካዊ ጠላቶቼ" ስትል ትፈርጃቸዋለች።
ትብብሩንም በግብፅ እና በኤርትራ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን መጠቀም እንዳትችል የተፈጠረ ሴራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት በኤርትራ እና በትግራይ ባለሥልጣናት በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል የተመሠረተው "ጽምዶ" በመባል የሚታወቀው ትብብር ከዚህ ጋር አያይዘው አቅርበዋል።
አንዳንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች እና የፖለቲካ ተንታኞች የኤርትራ እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች በጋራ መታየታቸውን በመጥቀስ ትብብሩ ወደ ወታደራዊ አጋርነት ይለወጣል ሲሉ ይናገራሉ።
በሐምሌ ወር፣ ከፍተኛ የህወሓት ባለሥልጣናት ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ታጣቂ ቡድኖች እና ከኤርትራ ጋር መተባበር እንደሚቻል ጠቁመው ነበር።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ የሕዝብ ውይይቶች ላይ፣ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ የክልሉ መሪዎች "ከሥልጣን ለውጥ በኋላ ሊፈጠር ስለሚችል ሁኔታ" ለመወያየት ስማቸው ካልተጠቀሰ አጋሮች ጋር ንግግር እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
በወቅቱ "ብቻችንን አይደለንም። መንግሥትን ለመጣል አጋሮች አሉን" ሲሉ ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከወታደራዊ ኃይል ባሻገር ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ድንበር የሚሻገር የንግድ፣ ፖለቲካ እና ሎጀስቲክ ትብብር ሊያጠናክር ይችላል።
ህወሓት በተደጋጋሚ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት የሚጀመር ከሆነ ከዚህ በፊት እንደነበረው ጦርነት ከበባ ሊፈጸምበት እንደማይችል ሲናገር ተሰምቷል።
ይህም በወቅቱ ከኢትዮጵያን ተሰልፎ የነበረውን የኤርትራ ጦር በአጋርነት መያዙን ለማመላከት የቀረበ ነው።
የዐቢይ አስተዳደር ምን አለ?
በነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና አፋብን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን የመጠቀም ፍላጎት ከሚቃረኑ የውጪ ኃይሎች እና ኤርትራ ጋር እየሠሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።
ይሁን አንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሱዳንን ጨምሮ ተመሥርቷል ያሉትን ትብብር አጣጥለዋል።
ሱዳን ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እንደ ህወሓት ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች ስትል ያቀረበችውን ክስ ውድቅ አድርጋለች።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ኃይሎች አዛዥ የሆኑ የተወሰኑ ግለሰቦች ከፌደራል መንግሥት ጋር ትብብር እያደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ግን ከቡድኑ ጋር እየሠራ እንደሆነ በይፋ ባይገልጽም መሪዎቹ ግን በአዲስ አበባ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ ሲሳተፉ ታይተዋል።
ትብብሩ ምን ያህል ተጨባጭ መሆን ይችላል?
ታጣቂ ቡድኖቹ በአንድ ወጥ የአመራር መዋቅር ወይም በቋሚ የፖለቲካ አደረጃጀት ስር የመሰባሰባቸው ዕድል አነስተኛ ነው።
እንዲህ ዓይነት ጥምረት ሊያስከትለውን የመጨረሻ ውጤት አስቀድሞ ለመገመት ገና ቢሆንም፣ ጥረቱ ስኬታማ ከሆነ ግን ፌዴራል መንግሥቱ እስካሁን በተናጠል ሲጋፈጣቸው የነበሩትን ሁለት ግጭቶችን ወደ አንድ የሚያዋህድ ይሆናል።
የተለያዩ ቡድኖች በሂደቱ ያላቸውን ተሳትፎ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለሚያደርጉት ድርድር እንደ መደራደሪያ መሳሪያ ከተጠቀሙበት ጥረቱ ሊከሽፍ ይችላል።
በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተፈጠሩ የመንግሥት ተቃዋሚ ጥምረቶች፣ የፖለቲካ መግለጫዎቻቸውን ወደ የተቀናጀ ወታደራዊ እርምጃ ለመቀየር ተቸግረው ነበር፤ ይህም የሆነበት ምክንያት የአባል ቡድኖቹ የተለያዩ ግቦችን መከተላቸው፣ በተለያዩ ክልሎች መንቀሳቀሳቸው እና የተዋሃደ የአመራር መዋቅር አለመኖሩ ነው።
በመሆኑም፣ እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች በተግባር ሂደት ላይ አለመግባባቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ።
ይህም በ2014 ዓ.ም. ህወሓት እና የአሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሌሎች ስድስት የታጠቁ ቡድኖች ጋር በመሆን እንደመሠረተው እና በመጨረሻም ግቡን ማሳካት ሳይችል እንደቀረው ጥምረት የመሆን ዕጣ ሊገጥመው ይችላል።