ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ቤተሰቦቼ በሕይወት ስለመኖራቸው እስካሁን ምንም አላውቅም"- ወላጆቿ ከ25 ዓመት በፊት የታሰሩባት ኤርትራዊት
ሃና ጴጥሮስ ሰለሞን ከ25 ዓመታት በፊት አባቷ ያለምንም ፍርድ ሲታሰሩ፣ እርሷና ወንድሞቿ እንዴት ወላጅ አልባ እንደሆኑ ስታስታውስ እንባዋ ይፈስሳል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናታቸውም በመታሰራቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንም ስለ እናትና አባቷ የሰማ የለም።
"እንደ ስፖርተኛ ፎጣ በትከሻው ላይ አድርጎ ነበር" ስትል አባቷን የ10 ዓመት ልጅ እያለች ለመጨረሻ ጊዜ ያየችበትን ሁኔታ ታስታውሳለች። ዱብ ዱብ ለማለት ነበር የወጣው።
"በየማለዳው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር።"
ወላጆቿ የተገናኙት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃነቷን ለማግኘት ባደረገችው ረዥም ጦርነት ወቅት ነበር።
አባቷ ጴጥሮስ ሰለሞን በጦርነቱ ወቅት ከነበሩት ከፍተኛ መሪዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን በብዙዎች ዘንድ በነበራቸው ኃላፊነት የተነሳ እንደ ብሔራዊ ጀግና ተደርገው ይቆጠራሉ።
ከነፃነት በኋላ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከመንግሥት ጋር አለመግባባት በጀመረበት ወቅት የአሳ ሀብት ሚኒስቴርን ይመሩ ነበር።
ያ ማለት እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 2001 እርሳቸውና ሌሎች 14 ታዋቂ ፖለቲከኞች ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉበት ጊዜ ሲሆን፣ ይህም ከነፃነት በኋላ የፀደቀው ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን እንዲሁም አገራዊ ምርጫ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው። እነዚህ ሰዎች ጂ-15 በመባል ይታወቃሉ።
ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጋው የኤርትራ ሕዝባዊ ነፃ አውጪ ግንባር መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ግን የቀረበውን ጥያቄ በበጎ አልተቀበሉትም።
ሃና የአባትነት ፍቅራቸውን በሚገባ ሳታጣጥም ከሚንስትርነት ተባረሩ። ከዚያ በኋላም ቢሆን በየዕለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ማልደው ከቤታቸው ይወጡ ነበር።
አልቃይዳ በአሜሪካ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ መላው ዓለም ትኩረቱ በተከፋፈለበት ወቅት ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የፖለቲካ ለውጦችን እንዲያካሂዱ በይፋ ጥያቄ ባቀረቡት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምን ያህል እንደተከፉ ተረዳች። ከዚያ በኋላ የሆነው በኤርትራ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ሆነ።
መስከረም 8/1994 ዓ.ም. ማለዳ ላይ የጸጥታ ኃይሎች በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በዋና ከተማዋ አሥመራ ከሚገኙት 11 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቤት ደጃፍ ተገኙ።
ጴጥሮስ የተለመደውን የመረጮ ልብሳቸውን አድርገው ሲወጡ በደህንነት አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ቤተሰቦቻቸው ምን እንደደረሰባቸው ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እናታቸው አስቴር ዮሃንስ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ስለሄደች ሃና እና ሦስቱ ወንድሞቿ እና እህቶቿ ከአያታቸው ጋር እንዲቆዩ ተደረገ።
ሃና በወቅቱ ስለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ስትናገር፣ ነገሮች ግልጽ የሆኑት ጴጥሮስ ከጠፉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር ትላለች።
"የክፍል ጓደኞቼ አባቴ አገሩን ሸጧል ብለው ነገሩኝ።"
"ያኔ ነው ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እና ሰዎች ለአገራቸው ነፃነት የተዋጉትን አባቴንና ባልደረቦቹን እንዴት እንደወነጀሏቸው የተረዳሁት። በጣም ተጎድቻለሁ።"
በአሜሪካ የነበረችው አስቴርም በተከሰተው ነገር በጣም በመደንገጧ መጥፎ ሁኔታ ላይ ነበረች። የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለልጆቿ ፓስፖርት መስጠት ይችሉ እንደሆነ ብትጠይቅም ወደ አገሯ እንድትመለስ በመንገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።
ለሁለት ዓመታት ስለሁኔታው ካሰበች ከተጨነቀች በኋላ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ማረጋገጫ ካገኘች በኋላ ለመመለስ ወሰነች።
ሃና እና ወንድሞቿ እና እህቶቿ የእናታቸውን መምጣት አጥብቀው ፈልገው የነበረ ቢሆንም መስጋታቸው ግን አልቀረም።
"በስልክ እንዲህ አልኳት፦ 'ቢያስሩሽስ?'" ስትል እናቷ ከመምጣቷ በፊት የተነጋገሩትን ታስታውሳለች።
"ምንም ነገር እንደማይደርስባት ስትናገር ያለችኝ 'ምንም ጥፋት አላጠፋሁም፤ ልጆቼን ለማሳደግ ብቻ ነው የምመጣው' ነበር ያለችኝ" ትላለች።
በኋላ ላይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ራሳቸው አስቴር ምንም እንደማይደርስባት ቃል እንደገቡላት ሃና ማወቅ ችላለች። ነገር ግን ቤተሰቡ እአአ ታህሳስ 11/2003 በአሥመራ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲጠብቃት፣ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር በመንገደኞች መውጫ በኩል ሳትመጣ ቀረች።
ተስፋቸው እርሷን ለመቀበል ከያዙት አበባ ጋር መጠውለግ ጀመረ። "በጣም ረዥም፣ ረዥም ጊዜ ነበር የጠበቅናት። በመጨረሻም ተስፋ ቆርጠን ወደ ቤታችን ተመለስን።"
"መጀመሪያ ወደ አሜሪካ ደወልን፤ ጓደኞቿ እና ዘመዶቻችን አውሮፕላን ማረፊያ እንዳደረሷት ነገሩን።"
ከዚያም አንድ ባለሥልጣን አስቴርን ሻንጣዋን እንድትወስድ ከአየር ማረፊያው ደውሎ ጠየቀ። ያኔ ነው ወደ አገሯ እንደተመለሰች ነገር ግን ወደ ቤቷ እንደማትመጣ የተገነዘቡት።
በቀጣዮቹ ወራት እናታቸው ያለችበትን ለማወቅ ያደረጉት ጥረት፣ ያቀረቡት ልመና ሰሚ አላገኘም። በምትኩ የሃና አያት በባለሥልጣናት ጥያቄ ማቅረባቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።
በኋላ ላይ ቤተሰቡ አስቴር በአሥመራ በሚገኘው ካርሼሊ በመባል በሚታወቀው ስመጥር እስር ቤት ውስጥ ታስራ እንደነበር ሰማ።
የሃና አባት በመስከረም 18 እና 19/2001 ተይዘው ከታሰሩት ግለሰቦች ጋር ከአስመራ በስተሰሜን ምስራቅ ቆላማ አካባቢዎች በሚገኘው ዒራዒሮ በመባል በሚታወቀው አደገኛ እና ምስጥራዊ እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል። በአገር ክህደት ወንጀል የተከሰሱት እነዚህ ታሳሪዎች አንዳቸውም ለፍርድ ቀርበው ወይም ዘመዶቻቸውን እንዲያዩ ተፈቅዶላቸው አያውቅም።
በተመሳሳይ ጊዜ መንግሥት ሁሉንም የግል ጋዜጦችን ዘግቶ ጋዜጠኞቹን እና አርታኢዎቹን በዒራዒሮ አስሯቸዋል ተብሎ ይታመናል።
የኤርትራ መንግሥት፣ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘውን ኤምባሲውን ጨምሮ ቢቢሲ እስረኞቹ የት እንዳሉ ወይም በሕይወት መኖራቸውን ወይም አለመኖራቸውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጥ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ሃና ልክ እንደ ብዙ ሺህ ወጣት ኤርትራውያን፣ ከወታደራዊ አገልግሎት ሸሽታ የተሻሉ እድሎችን ፍለጋ አገሯን ለቅቃ ወጣች። በወቅቱ ፓስፖርት ማግኘት ስላልቻለች በድብቅ ነበር በድንበር በኩል የወጣችው።
አሁን 35 ዓመት የሆናት ሃና ትዳር መስርታ በአሜሪካ ትኖራለች።
የትራውማ ስፔሻሊስት በመሆን እያገለገለች የምትገኘው ሃና ወላጆቿን በማጣቷ አሁንም ድረስ ስሜቷ እንደተጎዳ ትናገራለች።
የወላጆቿን የቆዩ ምስሎች ስትመለከት ከመታሰራቸው በፊት የነበሯቸውን አስደሳች ጊዜያት እንዳትረሳ ትጨነቃለች።
ቤተሰቡ የነበረው ሳቅ፣ ለልደት፣ ለበዓል ሲሰባሰብ "አባቴ ሁልጊዜ ሰዎችን ቤት ውስጥ መሰብሰብ ይወድ ነበር፣ መልካም ጊዜያት ነበሩ" ስትል ወደ ኋላ በትዝታ ትመለሳለች
እናቷ ይሰሩላት የነበረውን "ማንም ዳግም የማያበስለውን" የእንቁላል እና የድንች ሳንድዊች ትናፍቃለች።
አባቷ የአሳ ሀብት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ወደ ባህር ዳርቻ በሚያደርጉት ጉዞ፣ ሃና በመኪናው ውስጥ የዘፈን ውድድሮችን ያዘጋጁ እንደነበር ታስታውሳለች።
"አንድ በአንድ እንድንዘፍን ይጠይቀን ነበር፤ ያሸነፈ ልጅ ስጦታ ይሰጠዋል።"
ከሚወዷቸው ዘፈኖች መካከል አንዱ "እህቴ የወሰደችው ሹራብ፣ ሰማያዊ ሹራብ ነበረኝ" የሚል ግጥም ያለውን ነበር።
ዘፈኑ የነፃነት ታጋይ የነበረችውን እና በጦርነቱ ወቅት የተገደለችውን እህታቸውን ያስታውሳቸዋል።
እንዲሁም እናቷ ሙዚቃን የሚወዱ ሲሆን የአባ፣ የዶሊ ፓርተን እና የዊትኒ ሂዩስተን ተወዳጅ ዘፈኖችን ይጫወቱ እና ይዘፍኡ ነበር።
አባቷ እስኪታሰሩ ድረስ ሃና የአዲስ ዓመትን ጨምሮ በሦስት ትላልቅ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን በዓላት የሚደምቀውን መስከረም በተስፋ የተሞላች እንደነበር ታስታውሳለች። አሁን ግን ይህ ወር ምንም ደስታ አያመጣላትም።
ኢብራሂም ሸሪፎ ስሜቷን በትክክል ይረዳል። ሁለቱም ወላጆቹ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አባላት የነበሩ ሲሆን ከ25 ዓመታት በፊት ከታሰሩት የቡድን-15 ሰዎች መካከል ነበሩ።
በወቅቱ የ13 ዓመት ልጅ ነበር።
"ለእኔ መስከረም 18/2001 ጨለማ ቀን ነው፤ ግን ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ ለኤርትራ እና ለሕዝቦቿም ጨለማ ቀን ነው፤ ምክንያቱም ሕግና ዲሞክራሲ የታሰረበት ቀን በመሆኑ ጭምር ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
38 ዓመት የሞላው ኢብራሂም በኔዘርላንድስ በስደት የሚኖር ሲሆን በፖለቲካል ሳይንስ የሁለተኛ ዲግሪውን እየተከታተለ ነው።
አባቱ ማህሙድ አህመድ ሸሪፎ ከመታሰራቸው በፊት የአካባቢው መንግሥት ሚኒስትር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ኢብራሂም እና እናቱ አስቴር ፍሰሃጺዮን እህቷ ቤት ሳሉ አንድ የደህንነት ሠራተኞች በሩን አንኳኩተው ፒጃማዋን እንደለበሰች ሲወስዷት ያስታውሳል።
ኢብራሂም ስለ አባቱ በመጨነቅ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ቤቱ ቢሄድም ነገር ግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ በወጣበት ተይዞ መወሰዱ ተነገረው።
ሃናም ሆነ ኢብራሂም ያለ ወላጆቻቸው ሲያድጉ የሚደርስባቸውን አደጋ ተጋፍጠው፣ እንክብካቤ እና ድጋፍ ላደረጉላቸው ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ከፍ ያለ ምስጋና እንዳላቸው ይናገራሉ።
ወላጆቻቸው በአገራቸው ለውጥ እንዲመጣ በማለት በቆሙለት ዓላማም ኩራት ይሰማቸዋል።
"ኅሊና ነበራቸው፤ የተዋጉለትት እና የተዋደቁለት ዓላማ በኢሳያስና ቤተሰቡ ሲጠለፍ ዝም ብለው ማየት አልቻሉም" ይላል ኢብራሂም።
"እንደ ቤተሰብ፣ በሕይወት መኖራቸውንም አለመኖራቸውን ማወቅ አለብን" ሲል አክሎ፣ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን ትዝታ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ይፈልጋል በማለት ይከስሳል።
ሃና ባለፉት ዓመታት ዘመዶቻቸው የጠፉባቸው ሌሎች ብዙ ሰዎችም ሁኔታ እንዲሰማ ትፈልጋለች።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች የቡድን-15 የኅሊና እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የ80 ዓመት አዛውንት የሆኑት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አሁንም አገሪቱ እአአ በ1997 ያጸደቀችውን የመጀመሪያውን ሕገ መንግሥት ተግባራዊ አላደረጉም። ምንም ዓይነት ምርጫ ሳያካሂዱም ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በሥልጣን ላይ ይገኛሉ።
ሃና አባቷ ከመጥፋታቸው ቀደም ብሎ "መጥፎ ስሜት" እንደነበራት ታስታውሳለች። ከዚህ ፍርሃቷም የተነሳ አባቷ ወደተኙበት አልጋ እየተሳበች በመሄድ እግሮቻቸውን በገመድ አሰረች።
"ጠዋት ላይ ከእንቅልፉ ሲነቃ እግሮቹ ታስረው በማግኘቱ ለማስልቀቅ ሲሞክር እኔ ነቃሁ። እንዳይሄድ ለመንኩት ነገር ግን [ከሩጫው በኋላ] እንደሚመለስ አረጋገጠልኝ።"
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጥልቅ የሐዘን ባሕር ውስጥ ነው የምኖረው ስትል ትናገራለች።
"አንዳንድ ጊዜ ጸጥ ያለ ይሆንና መንሳፈፍ ትችላለህ፤ ነገር ግን ሌላ ጊዜ ሐዘኑ እንደ ማዕበል ተመልሶ ይመጣና ወደ ጥልቁ ያሰጥምሃል። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ትቆርጣለህ እና ትንፋሽ ያጥርሃል።"
ለወላጆቿ መልዕክት የሚደርሳቸው ቢሆን ምን ማለት እነደምትፈልግ ስትጠየቅ "ስለ እኛ አትጨነቁ። ትግሉን በጽናት እንደተወጣችሁት ሁሉ፣ ይህንንም ተቋቁማችሁ ልንገናኝ እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን" ብላለች።