ደቡብ አፍሪካውያን በጆሃንስበርግ ተገድለው የተገኙትን ዘጠኝ ሴቶች ለመዘከር እና መፍትሔ ለመጠየቅ ተሰባሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደቡብ አፍሪካውያን በዚህ ሳምንት በጆሃንስበርግ አቅራቢያ ተገድለው የተገኙትን ዘጠኝ ሴቶች ለመዘከር እና መፍትሔ ለመጠየቅ ተሰባሰቡ።
በርካቶች ሴቶች በየቀኑ የሚጋፈጡት እንደሆነ የሚገልጹት ጥቃት ቁጣ እና ስጋትን ፈጥሯል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ባለፉት ሁለት ወራት ፖሊስ በምሥራቃዊ ጆሃንስበርግ ኢኩርሁልኒ የዘጠኝ ሴቶችን አስክሬን ያገኘ ሲሆን ምርመራ እያካሄደ ነው።
አብዛኞቹ ሟቾች በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ልብሶቻቸው የተቀዳደዱ ሲሆን ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተውባቸዋል።
በጆሃንሰበርግ ከተገደሉት መካከል አንዷ የሆነችውን ኤሊዛቤት ሞስላክጎሞ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ዛሬ እየተካሄደ ነው።
ኤሊዛቤት ለመሮጥ ከቤቷ ከወጣች በኋላ ነበር ከቀናት በኋላ አስክሬኗ የተገኘው።
ሀዘንተኞች ሻማ በማብራት እና “በቃ! በሴቶች ላይ የሚፈፀም ግድያ ይቁም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።
ጥቁር ለብሰው በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት መካከል ሊራቶ ሊንትሴላ የተባለች ሴት “እዚህ የተገኘነው ኤልዛቤትን ስላጣን ነው። ግን እኛም የትም ቦታ ደኅንነታችን የተጠበቀ አይደለም” ብላለች።
ግድያዎቹ እአአ በ2025 ፆታን መሠርት ያደረጉ ጥቃቶች ብሔራዊ ቀውስ ሆኖ በታወጀባት ደቡብ አፍሪካ ቁጣን ቀስቅሷል።
በርካታ ሴቶች ለጥቃቱ የተሰጠው ትኩረት እና የባለሥልጣናት ቃል ደኅንነት እንዲሰማን ማድረግ አልቻለም ብለዋል፥።
ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ሐሙስ ዕለት ደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት እንድትለምድ እንማይፈቅዱ እና ድርጊቱን ፈፃሚዎች ለፍርድ እንደማያቀርቡ ቃል ገብተዋል።
ነገር ግን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አገልግሎት በሙስና እና በበጀት እጥረት ተዳክሟል። በዚህም ምክንያት ከ10 ግድያዎች ውስጥ ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ የሚቀርበው አንዱ ብቻ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በአማካኝ በዓለም ላይ ከሚገደሉ ሴቶች መካከል በአገሪቱ የሚገደሉት አምስት እጥፍ እንደሚበልጥ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት መረጃ ያሳያል።




















