ትራምፕ የሰላም ዕቅድ ካቀረቡ በኋላ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን እና ጋዛን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንደሚያደርግ አስታወቁ።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ምሽት ከስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ይህም ያቀረቡትን የሰላም ዕቅድ ወደ ተግባር ለማስገባት ከፍተኛ እምርታ ነው ተብሏል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ጋዛ በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ቦርድ በሚቆጣጠረው የፍልስጤም የቴክኖክራቶች መንግሥት መተዳደር ትጀምራለች።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ “ይህ ለዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ወሳኝ እርምጃ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
አክለውም “ይህ ስምምነት፣ በመጨረሻም የፍልስጤምን ሕዝብ ለመርዳት ከሰላም ቦርድ ጋር በቅርበት የሚሰራ አዲስ የፍልስጤም መንግሥት ጋዛን እንዲያስተዳድር ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
በሥምምነቱ መሠረት የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው ይወጣሉ።
ስምምነቱ የተደረሰው የሐማስ ባለሥልጣናት፣ የሰላም ቦርዱ አባላት፣ የግብጽ፣ ኳታር እና ቱርክ አደራዳሪዎች በተገኙበት ነው።
የሐማስ ባለሥልጣናት ትጥቅ በመፍታት እና የእስራኤል ጦር የጋዛ ሰርጥን ለቅቆ እንዲወጣ ከስምምነት መደረሱን አረጋግጠዋል።
ባለሥልጣናቱ የሰላም ቦርዱ እና አደራዳሪዎቹ እስራኤል በስምምነቱ ላይ ለተዘረዘሩት ነጥቦች ተገዢ እንድትሆን እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የሐማስ የድርድር ቡድን አባል የሆኑት ጋዚ ሃማድ፣ ቡድኑ "በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሕዝቦቻችንን ከግድያ እና ከመፈናቀል ለመታደግ ሲባል" ስምምነቶችን እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እስራኤል እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።
በሚያዚያ ወር ሐማስ በትራምፕ የቀረበውን የሰላም ቦርድ ጥረት ጋር በተያያዘ የቀረበውን ትጥቅ የመፍታት ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አድርጎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሐማስ ትጥቅ ከፈታ በኋላ እስራኤል ከጋዛ ለመውጣት ትስማማ እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ “እስራኤልን የምንጠይቃት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ከተስማሙበት የ20 ነጥብ ዕቅድ ውጪ ሌላ ነገር አይደለም፤ ስለዚህም ዕቅዱን እንደሚያከብሩት ሙሉ እምነት አለን" ሲል ምላሽ ሰጥተዋል።
እስራኤል በ20 ነጥብ ዕቅዱ መሠረት ላለመውጣት ከወሰነች፣ ትራምፕ "እጅግ እንደሚያዝኑ" ባለሥልጣኑ ጨምረው ገልጸዋል። እስራኤል ጥሩ አጋርነቷን እንደምትቀጥል እንደሚያምኑም ባለሥልጣኑ አብራርተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው “የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ ሲጠናቀቅ የእስራኤል ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው ይወጣሉ፤ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ኃይል፣ ጋዛ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎረቤቶቿ ደህንነቷ የተጠበቀ ቦታ እንዲሆን ኃላፊነቱን ለመረከብ ከአዲሱ የፍልስጤም ፖሊስ ኃይል ጋር በጋራ ይሠራል” ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ አደራዳሪዎቹን ግብጽ፣ ኳታር እና ቱርክን አመስግነዋል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል የግብጽ መገናኛ ብዙኃንንን ጠቅሶ ካይሮ ሁለተኛውን ዙር የተኩስ አቁም ስብሰባ እንደምታዘጋጅ ዘግቧል።
























