“ትብብር ለኅልውና” የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮን "ተገንጣይ" እና "ሽብርተኝነት" የሚሉ አገላለጾች ተቃወመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰባት አማፂ ኃይሎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ንግግር ምላሽ ሰጠ።
ታጣቂ ኃይሎቹን “ተገንጣይ ቡድኖች” ሲሉ የጠሯቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለ ጥቃቱ ምንም ባይባልም፤ ሩቢዮ ጥቃቱን እንደ ሽብርተኝነት አይተውታል።
ጥምረቱ ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እየወሰድኳቸው ያሉ “ራስን የመከላከል” ወታደራዊ እርምጃዎች “የተገንጣይነት ዒላማ” ያለው አይደለም ብሏል።
ንቅናቄውን “ተገንጣይ” ብሎ መግለፅ ትክክል እና ተገቢ አይደለም በማለት መሠረታዊ ግቡ በአገሪቱ አንድነት፣ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣት እንደሆነም በመግለጫው ጠቅሷል።
“ትብብር ለኅልውና” ወታደራዊ እርምጃዎቹን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ጨምሮ ለእርቅ ለማውረድ ሰላማዊ መንገዶች ውድቅ በመደረጋቸው “የመጨረሻ አማራጭ” ሲል ገልጿቸዋል።
ወታደራዊ ተቋማት ላይ የሚፈፅማቸውን ተልዕኮዎች “ሽብር” ብሎ መጥራት "ለእውነታ የተንሸዋረረ መልክ" መስጠት ነው ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር አጣጥሏል።
“ትብብር ለሕልውና” ማርኮ ሩቢዮ ግጭቱን የገለፁበት መንገድ መንግሥት “የጦርነት አጀንዳውን ያለ ተጠያቂነት” እንዲቀጥል እና ለሁሉም የሰላም ጥረቶች በሩን የሚያዘጋ ነው ሲልም ነቅፏል።
ጥምረቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አሜሪካ በአጠቃላይ በግጭቱ ላይ “ሚዛናዊ እና ገንቢ” አቋም እንዲኖራት ጥሪ አቅርቧል።
ሰባት ታጣቂ ቡድኖች "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን ያስታወቁት መስከረም 10/2019 ዓ.ም. ነው።
ይህንን ጥምረታቸውን ይፋ ካደረጉ ከሦስት ቀናት በኋላ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግመኛ ግጭት ተቀስቅሷል።



