ቻይና ከኢስዋቲኒ ውጭ ላሉ የአፍሪካ አገሮች በሙሉ ከቀረጥ ነጻ ንግድ ፈቀደች

በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ንግድ ወደ ቤይጂንግ ያጋደለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ንግድ ወደ ቤይጂንግ ያጋደለ ነው
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ቻይና ከዛሬ ጀምሮ ከታይዋን ጋር ግንኙነቷን ካስጠበቀችው ኢስዋቲኒ ውጭ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ታሪፎችን መሰረዟን አስታወቀች።

እአአ ከታህሳስ 2024 ጀምሮ ቻይና ለ33 ዝቅተኛ ዕድገት ላላቸው የአፍሪካ አገራት ከቀረጥ ነፃ ዕድል ፖሊሲን ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች። አሁን ፖሊሲው 53 አገሮችን የሚሸፍን ሲሆን እስከ ሁለት ዓመታት ድረስ ተግባራዊ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ስለሚኖረው ነገር ግን ግልጽ አልተደረገም።

ቤይጂንግ ለአፍሪካ የአንድ ወገን የዜሮ ታሪፍ ፈቃድ የሰጠች የመጀመሪያዋ ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ አገር እንደሆነች በኩራት ገልጻለች።

ተንታኞች እንደሚሉት ግን ቻይና ተጽዕኖዋን ለማሳደግ ዕድሉን እየተጠቀመች ቢሆንም፣ ከቻይና ጋር ከፍተኛ የንግድ ጉድለት ላለባት አፍሪካ የታሪፍ ጉዳይ የላኪዎች ዋና እንቅፋት አይደለም ብለዋል።

ያልተመጣጠነ የንግድ ሚዛን

"ቻይና ራሷን ከዶናልድ ትራምፕ እና ከአሜሪካ በተቃራኒ ለንግድ ነጻነት እና ለአፍሪካ ተስማሚ የኢኮኖሚ አጋር አድርጋ እያስቀመጠች ነው" ይላሉ በኦስትቻይና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የምርምር ባልደረባ የሆኑት ሎረን ጆንስተን።

አሜሪካ በነሐሴ ወር እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ላይ ጥላ የነበረ ቢሆንም የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ የአብዛኛዎቹ ታሪፍ 10 በመቶ ሆኗል።

የቻይና ዜሮ-ታሪፍ ስርዓት የአፍሪካ የግብርና የወጪ ንግድን በመጨመር "የገጠሩን ሕዝብ ገቢን ከፍ ለማድረግ፣ ምርታማነትን ለማሻሻል እና በመጨረሻም ረሃብን እና ድህነትን ለመቀነስ ይረዳል" ብለዋል ጆንስተን።

የቻይና-አፍሪካ ንግድ ግን ወደ ቻይና ያጋደለ በመሆኑ የሚዛን መዛባት አለበት። ይህም ማለት ቻይና ወደ አፍሪካ የምትልከው አፍሪካ ወደ ቻይና ከምትልከው በላይ ከመሆኑም ባለፈ ልዩነት እየሰፋ ነው።

ባለፈው ዓመት አፍሪካ ከቻይና ጋር ያላት የንግድ ጉድለት በ65 በመቶ ጨምሮ 102 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ደርሷል።

የአፍሪካ ወደ ቻይና የምትለከው በዋናነት እንደ ነዳጅ እና የብረት ማድን ያሉ ማዕድናት እና ጥሬ ዕቃዎችን ነው።

በአሁኑ ጊዜ በአህጉሪቱ ውስጥ የቻይና ዋና የንግድ አጋሮች ከሚባሉት መካከል ኢኮኖሚዋና በዋናነት በነዳጅ የሚመራው አንጎላ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካን ይጠቀሳሉ።

እንዲህ ባለ ልዩነት ባለው አህጉር ውስጥ ወጥ የሆነ ከቀረጥ ነፃ የሆነ ስርዓት መከተል ያልተመጣጠነ ትርፍ ሊያስከትል እንደሚችል ጆንስተን ገልጸዋል።

እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ያሉ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት የወጪ ንግዳቸውን ለማስፋፋት የተሻለ ዕድል ይኖራቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጄርቪን ናይዱ በበኩላቸው የዜሮ ታሪፍ እርምጃ በአህጉሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ችግር እና የመሠረተ ልማት ክፍተት የሚሞላ አይደለም።

"ብዙ የአፍሪካ አገራት እንደ ውስን የኢንዱስትሪ አቅም፣ ደካማ የሎጂስቲክስ እና በጥሬ ዕቃ ኤክስፖርት ላይ ጥገኛ የመሆን ያሉ መዋቅራዊ ገደቦች ያጋጥሟቸዋል፣ ይህንን ደግሞ የታሪፍ ቅነሳው ለብቻው ሊፈታው አይችልም" ብለዋል።

አፍሪካ ወደ ቻይና በብዛት የምትልከው እንደ ኮባልት ያሉ ማዕድናትን ጨምሮ ጥሬ እቃዎችን ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አፍሪካ ወደ ቻይና በብዛት የምትልከው እንደ ኮባልት ያሉ ማዕድናትን ጨምሮ ጥሬ እቃዎችን ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሲንጋፖር የሚገኘው የምሥራቅ እስያ ተቋም ዳይሬክተር አልፍሬድ ሺፕኬ በበኩላቸው "የኤክስፖርት አቅም ባላቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መጠነኛ እና የተከማቸ እንደሆነ" በመግለጽ የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ይስማማሉ።

"የአፍሪካ አገሮች ምርትን ማስፋት፣ ኤክስፖርትን የማባዛት እና የእሴት ሰንሰለቱን ማሳደግ ከቻሉ በረጅም ጊዜ እምቅ አቅሙ የበለጠ ትርጉም ያለው ሊሆን ይችላል" ይላሉ ሺፕኬ።

በሲንጋፖር የሚገኙ የቻይና-አፍሪካ ግንኙነት ባለሙያው አሚት ጄን፤ የቻይና ሸማቾች ፍላጎት መለወጥ ለአፍሪካ አምራቾች አዳዲስ ገበያዎችን ሊከፍት እንደሚችል ጠቅሰዋል። ለምሳሌም የቻይና ሸማቾች ከ20 ዓመታት በፊት ከገዙት በላይ ብዙ ቡና እና ለውዝ እየገዙ ነው።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኬን ጂቺንጋም በዚህ ይስማማሉ።

"እነዚህ አዳዲስ እርምጃዎች የቻይና ገበያዎችን ተደራሽነት ያሻሽላሉ፤ ያለውን የንግድ ሚዛን ጉድለት በመዝጋት የአፍሪካ ኩባንያዎች እንዲበለጽጉ ዕድሎችን ያስፋፉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ለኬንያ እንደ አቮካዶ ላሉ የተወሰኑ ንዑስ ዘርፎች ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል። እንደማካዴሚያ ለውዝ፣ ቡና፣ ሻይ እና ቆዳ ያለው የግብርና ዘርፍ ከፍተኛውን ጥቅም ያገኛል።"

የአፍሪካ የፊስካል ፖሊሲ ኢኮኖሚስት የሆኑት ዋንጋሪ ኬቡቺ በበኩላቸው የአጭር ጊዜ ድጋፉ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ እና "ለግብርና፣ ለማዕድን እና ለሎጂስቲክስ ዘርፎች መጠነኛ ጭማሪ" እንዳላቸው ተናግረዋል። የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ትርፍ ከገበያ ተደራሽነት ብቻ ሊገኝ አይችልም ሲሉ ያስረዳሉ።

"መዋቅራዊ ችግሩ አልተለወጠም። አፍሪካ ጥሬ እቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ እና የተመረቱ ዕቃዎችን ማስመጣቷን ቀጥላለች። ይህ አለመመጣጠን የማያቋርጥ የንግድ ሚዛን መዛባትን ያስከትላል፣ የሀገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብን በማቀጨጭ እንዲሁም መንግስታት የህዝብ አገልግሎቶችን ለመደገፍ የሚያስፈልጉትን ሥራዎች እና የግብር መሰረት ይገድባል።"

"ከወደባችን የወጡ እሴት ያልተጨመረባቸው ሸቀጦች ላይ ዜሮ ታሪፍ መደረጉ ችግሩን አይፈታውም። ሊያሳድጉት ይችላሉ። የአፍሪካ መንግስታት አሁን ከባድ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለባቸው፡ የተሻሻለ የገበያ ተደራሽነትን ለኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዴት እንጠቀማለን?"

የኢስዋቲኒ ጉዳይስ?

ተንታኞቹ የኢስዋቲኒ መገለል ውስን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ያለው የፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነ ያምናሉ።

"ኢስዋቲኒ ከታይዋን የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ ሊረዳት እንደሚችል" ጄይን ያምናሉ።

በደቡብ አፍሪካ የምትገኘው የባህር በር የሌላት ኢስዋቲኒ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላቸው 12 አገሮች መካከል አንዷ ናት። ታይዋን ከቻይና ጋር "እንደገና የምትቀላቀል" ግዛቷ እንደሆነች ቤጂንግግ ትመለከታለች።

ታይዋን በበኩሏ ሉዓላዊ አገር እንደሆነች ትቆጥራለች።

ባለፈው ወር የታይዋን መሪ ላይ ቺንግ-ቴ ወደ ኤስዋቲኒ የሚያደርጉትን ጉዞ ሌሎች ሲሼልስ፣ ሞሪሺየስ እና ማዳጋስካር አውሮፕላናቸው በግዛታቸው ላይ እንዳይበሩ በመከልከላኣቸው ለመሰረዝ ተገደዋል። በቻይና የኢኮኖሚ "ከፍተኛ ጫና" ምክንያት ይህንን አድርገዋል ሰትል ታይዋን ከሳለች።

ኢስዋቲኒን ወደ ጎን በመተው ቻይና "ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት እያሳየች እና ከቻይና ጋር ያለች ግንኙነት ከገደቦች ጋር እንደሚመጣ እያሳየች ነው" ሲሉ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የታይዋን ማዕከል የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ዌን-ቲ ሱንግ ተናግረዋል።

"ቻይና የራሷን ወዳጆች እና የታይዋን ወዳጆች እንዴት እንደምትይዝ ለዓለም ማሳየት ትፈልጋለች" ብለዋል።