በጀርመን ሠራተኞች በታመሙበት የመጀመሪያው ቀን የሐኪም ፈቃድ እንዲያስገቡ መጠየቃቸው ተቃውሞ አስነሳ

የተጨነቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በጀርመን ሠራተኞች በታመሙበት የመጀመሪያው ቀን የሐኪም ፈቃድ እንዲያስገቡ መጠየቃቸው ብዙዎችን አስቆጥቷል።

የሕመም ፈቃድን በተመለከተ የተደረጉ ሌሎችም ለውጦች ውዝግብ አስነስተዋል።

ሠራተኞች የሐኪም ፈቃድ በስልክ ማግኘት እንደማይችሉ ተገልጿል። ይህ አሠራር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መተግበር የጀመረ ነው።

መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ "በጀርመን የሕመም ፈቃድ በጣም ረዥም ነው" ብለዋል።

አሁን ባለው አሠራር ሠራተኞች የሕክምና ማስረጃ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ከሦስት ቀናት በላይ መሥራት ካልቻሉ ነው።

በዚህ አሠራር የሐኪም ፈቃድ ማቅረብ ያለባቸው በአራተኛው ቀን ነው። ነገር ግን ቀድመውም ማስረጃውን መጠየቅ ይችላሉ።

የፍሬድሪክ መርዝ ወግ አጥባቂ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና በጥምረቱ ውስጥ ያለው ሶሻል ዲሞክራትስ ፓርቲ ይሄንን አሠራር ለመለወጥ ወስነዋል።

"ከባድ ውሳኔ ነው፤ ነገር ግን ከሥራ ለረዥም ጊዜ በመቅረት የሚከሰተውን ጉዳት ተቀብለን መቀጠል አንችልም" ሲሉ መራሔ መንግሥቱ ተናግረዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እንደነበረው "የተጋነነ" የሕክምና ፈቃድ ጥየቃን መንግሥታቸው እንደማይቀበል ገልጸዋል።

"ጀርመን ከወርሽኙ ቀድሞ ወደነበረው አሠራር እየተመለሰች ነው" ብለዋል።

የሕክምና ቡድኖች ውሳኔውን አጥብቀው ተችተዋል።

የጤና ባለሙያዎች እና የመድኅን ሠራተኞች ማኅበር ኬቢቪ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሐኪም ፈቃድ እንዲያገኙ ብቻ ሆስፒታል እንዲሄዱ ማስገደድ "እብደት ነው" ብሏል።

ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ "የሚያስለው ወይም ጨጓራውን ያመመው ሰው መተኛት ነው ያለበት እንጂ በቀዶ ሕክምና የተጨናነቀ ቦታ መሄድ አይገባውም" ብለዋል።

ሌላኛው የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር 'አሶሴሽን ኦፍ ጀነራል ፕራክቲሽነርስ' ተላላፊ በሽታዎች ሁለት ቀን በመተኛት እንደሚድኑ ጠቅሶ፤ ታማሚዎች ወደ ሆስፒታል ከሄዱ ከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚፈጠር አስጠንቅቋል።

የገዢው ፓርቲ ምክትል መራሔ መንግሥት ላርስ ኪናግቤል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ በሚል "ሊሠራ የሚችል አማራጭ መፍትሔ" እየፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሌበር ሚኒስትር ባርቤል ባስ በበኩላቸው ሠራተኞች በታመሙበት የመጀመሪያው ቀን የሐኪም ማስረጃ ያምጡ መባሉን እንደሚመረምሩ ተናግረዋል።

"ውጤታማ ይሆናል ወይስ መሰናክል ይፈጥራል የሚለውን እንመረምራለን" ብለዋል።

ሌላኛው ፖለቲከኛ ጀንስ ስፓህን እንዳሉት የጀርመን የሕመም ፈቃድ በአውሮፓ ኅብረት ካለው ከፍተኛው ነው።

"ከፍተኛ የሕክምና ፈቃድ ቀናት ይጠየቃል። በአንድ ሠራተኛ እስከ 18 ቀናት ይደርሳል። የእውነት የታመሙ ሰዎች በእርግጥ ቤታቸው ማረፍ አለባቸው" ብለዋል።

በጀርመን ከሕክምና ፈቃድ ውጪ የግብር እና ሌሎችም ማሻሻያዎችም እየተደገሩ ይገኛሉ።