ናሳ ከሕዋ የወደቀን ቴሌስኮፕ "ቀልቦ የሚይዝ" የጠፈር መንኮራኩር አስወነጨፈ

የፎቶው ባለመብት, NASA
ናሳ ከሕዋ የወደቀን ቴሌስኮፕ ቀልቦ የሚይዝ የጠፈር መንኮራኩር አስወንጭፏል።
'ስዊፍት ኦብዘርቫቶሪ' የተባለው ቴሌስኮፕ በሁለንታ (universe) ከፍተኛ ፍንዳታዎች ከመከሰታቸው በፊት የሚመረምር ነው። በቀጣይ ወራት ውስጥ ግን ወደ ምድር ተምዘግዝጎ በመውደቅ እንደሚጋጭ ተሰግቷል።
ናሳ ወደ ሕዋ የላከው ሊንክ የተባለው የጠፈር መንኮራኩር አነስተኛው ቴሌስኮፕ ከምድር ጋር ሳይጋጭ በፊት የሚይዘው ይሆናል።
መንኮራኩሩ ሳተላይቱን በሮቦት እጆቹ ቀልቦ ወደ ሕዋ እንደሚመልሰውም ተገልጿል።
መንኮራኩሩ የተወነጨፈው ትናት አርብ ነው። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ነገር ተሞክሮ አያውቅም።
የሕዋ ሳይንቲስቱ ዶ/ር ሳይመን ባርበር "ከፍተኛ አደጋ ያጠላበት ተልዕኮ ነው። ናሳ ግን እንዲተገበር ወስኗል። ቴሌስኮፑ ካለው ዋጋ አንጻር ሳይንቲስቶች ተስፋ አድርገዋል" ብለዋል።
የወደቀው ቴሌስኮፕ በዩኒቨርስ ከፍተኛ የሆነውን እምቅ ኃይል ፍንዳታ (high-energy phenomena) የሚያጠና ነው። ዶ/ር ሳይመን እንደሚሉትም ይህንን ክስተት ለማጥናት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, NASA/Scott Wiessinger
ስዊፍት ኦብዘርቫቶሪ የተባለው ሳተላይት በፀሐይ ግለት ምክንያት ከምድር ከባቢ በመገፋቱ መውደቅ እንደጀመረ ተገልጿል።
መሬትን የሚዞርበት ፍጥነት በመቀነሱም ከነበረበት ከፍታ ዝቅ እያለ ነው።
ሳተላይቱ ሲወነጨፍ 372 ማይል (600 ኪሎሜትር) ላይ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 220 ማይል (360 ኪሎሜትር) ዝቅ ብሏል።
ከዚህ ቀደም ሳተላይቶች ወደ ምድር ተምዘግዝገው መሬት ጋር ሲቃረቡ ተቃጥለዋል።
ስዊፍት ኦብዘርቫቶሪ ሳተላይት ግን በተመራማሪዎች ተወዳጅ ስለሆነ ይሄ እጣ ፈንታ እንዳይገጥመው ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ግዙፍ መኪና የሚያህለው ሳተላይቱ ሦስት ቴሌስኮፖች ተገጥመውለት ወደ ሕዋ የተላከው በአውሮፓውያኑ 2004 ነበር።
ቴሌስኮፑ የሚያጠናው በሁለንታ (ዩኒቨርስ) ከፍተኛ የሆነው የእምቅ ኃይል ፍንዳታ የሚከሰተው ግዙፍ ከዋክብት ሲከስሙ ወይም ሲሞቱ ነው።
በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ጨረቃ በ10 ቢሊዮን ዓመታት ከምትለቀው ጋር የሚስተካከል ኃይል ያመነጫሉ።
ናሳ እንደሚለው ስዊፍት ኦብዘርቫቶሪን የመሰለ ቴሌስኮፕ የለም። የጠፈር መንኮራኩር በመላክ ሊያድነው የወሰነውም ለዚህ ነው።
መንኮራኩሩ የተሠራው ካታሊስት ስፔስ ቴክኖሎጂስ በተባለ አሪዞና በሚገኝ ተቋም ነው።
ሳተላይቱ 186 ማይል (300 ኪሎሜትር) ከመውደቁ በፊት መንኮራኩሩን ለማስወንጨፍ አንድ ዓመት ነበራቸው።
ወደ ሕዋ የተላከው የጠፈር መንኮራኩር በቀጣይ ሳምንታት ካሜራውን፣ አቅጣጫ ጠቋሚውን እና ሌሎችም የሚያስፈልጉትን ክፍሎች ማስነሳት ይጀምራል።
ሊንክ የተባለው መንኮራኩር ወደ ቴሌስኮፑ ተጠግቶ ከተለያየ አቅጣጫ ፎቶ ያነሳል። ከዚያም ቴሌስኮፑን ቀልቦ እንደሚይዝ ተገልጿል።
ቴሌስኮፑ ተቀልቦ እንዲያዝ ተደርጎ እንዳልተሠራ የሚናገሩት የሕዋ ሳይንቲስቱ ዶ/ር ሳይመን ባርበር "መንኮራኩሩ በጥንቃቄ ራሱን ከሳተላይቱ ጋር ያገናኛል" በማለት አስረድተዋል።
በቀጣይ ሁለት እና ሦስት ወራት ውስጥም ቀስ በቀስ ሳተላይቱን ወደነበረነት ቦታ ይመልሰዋል።















