ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት ከተስማማ በኋላ በተፈጸሙ የእስራኤል ጥቃቶች ሕጻናትን ጨምሮ 13 ሰዎች ተገደሉ
እስራኤል ባለፉት ቀናት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ሰባት ሕጻናትን ጨምሮ 13 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የጋዛ ሲቪል መከላከያ ባለሥልጣን እንደገለጸው፤ የእስራኤል ወታደራዊ አውሮፕላን ጥቃቶቹን የፈጸመው በጋዛ ከተማ፣ ኻን ዩኒስ እና ዴር ኤል ባላህ ነው።
እስራኤል ለሁለተኛ ተከታታይ ምሽት በጋዛ ጥቃት ፈጽማለች። ድብደባውን ያካሄደችውም ሐማስ የጦር መሣሪያዎቹን ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ቦርድ እንዲያስረክብ የሚያደርገውን ትጥቅ የመፍታት ዕቅድ መቀበሉን ካሳወቀ ከቀናት በኋላ ነው።
የፍልስጤም የጤና ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት በጋዛ ከተማ መኖሪያ ቤት ላይ በተፈፀመ ጥቃት አንድ ሕጻንን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ አቅራቢያ ደግሞ ሌላ አንድ ሰው መገደሉን አስታውቀዋል።
በኻን ዩኒስ የተፈጸመውም ጥቃት የደረሰው መኖሪያ ቤት ላይ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ድብደባ አባት፣ እናት እና የዘጠኝ ዓመት ልጃቸው ተገድለዋል።
በዴር ኤል ባላህ ደግሞ መኖሪያ ህንፃ በመመታቱ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ሕይወታቸው አልፏል።
ጥቅምት ላይ የእስራኤል እና ጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈጸመ አንስቶ ከ1,100 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ጥቃቶቹ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ያነጣጠሩ እንደሆኑ ተናግረዋል። ሁለት የሐማስ ታጣቂዎች መገደላቸውንም ጠቅሰዋል።
የእስራኤል የኤነርጂ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን በበኩላቸው 70 በመቶ የሚሆነው ግዛት በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሆነበት የጋዛ ሰርጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማቆም በሚል የተደረሰ ስምምት እንደሌለ እሁድ ዕለት ተናግረዋል።
በትራምፕ የሰላም ቦርድ እቅድ መሠረት እስራኤል ጋዛን ለቅቃ መውጣት ይኖርበታል። የኤነርጂ ሚኒስትሩ ኮኸን ግን ሐማስ ትጥቁን የማይፈታ ከሆነ ለመቆጣጠር እንዲቻል የጋዛ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ስር መሆን እንዳለበት መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር እሁድ ዕለት በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ሁለት የሐማስ ወታደራዊ አዛዦችን መግደሉን አስታውቋል። ከአዛዦቹ አንዱ የኑክህባ ኃይል፣ ሌላኛው ደግሞ የማጋዚ ክፍለጦር አባላት እንደነበሩም ገልጿል።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ ጋዛ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት የጃባሊያ ክፍለ ጦር አባል የሆነ የሐማስ ተዋጊን መገደሉን ጠቅሷል። የተገደሉት ሦስት የሐማስ አባላት በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅደው ነበር ብሏል።
የሰላም ቦርድ ሐማስ እና ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች "ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱ" ስምምነት ላይ መድረሱን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር።
አርብ ዕለትም እስራኤል በቀረበው ስምምነት "እጅግ ደስተኛ" እንደሆነች እንዲሁም እቅዱ "ለመካከለኛው ምሥራቅ ትልቅ እርምጃ" መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል ሐማስ መሣሪያውም ወይም በጋዛ ያለውን ቁጥጥር አሳልፎ የመስጠቱ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ እንዳላት ተገልጿል።
ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤ ንጋቪር እቅዱን "ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ይህ እቅድ በአሜሪካ አሸማጋይነት የተደረሰው እና የጋዛን ጦርነት ለመቋጨት ያለመው ተኩስ አቁም አካል ነው።
ባለፈው መስከረም ላይ ይፋ የተደረገው ባለ 20 ነጥብ እቅድ ስምምነቱን የሚያስፈጽም የሰላም ቦርድ እንደሚቋቋም ይገልጻል። ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ ማድረግ፣ የእስራኤል ወታደሮችን ከጋዛ ማስወጣት እና ጋዛን መልሶ መገንባትም የሚሉትም የእቅዱ አካል ናቸው።