ኔቶ በግሪን ላንድ ጉዳይ አሜሪካ እና ዴንማርክ መስማማታቸውን አደነቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን በኃይል እንደሚጠቀልሉ ከተናገሩ በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተከስቶ የነበረ ቢሆንም አሜሪካ እና ዴንማርክ በግዛቲቱ ደህንነት ላይ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ኔቶ ስምምነቱ ቀጣናውን ለማረጋጋት ያግዛል ሲል ትራምፕ በበኩላቸው ዴንማርክ ለአሜሪካ "በደህንነት ዙሪያ እነዲሁም ሌሎች ፍላጎቶች ላይ ቋሚ ቁጥጥር" ትሰጣለች ብለዋል።

የዴንማርክ እና የግሪንላንድ መሪዎች ምንም እንኳ የስምምነቱን ዝርዝር ነጥቦች ይፋ ባያደርጉም፣ "ደህንነትን ያጠናክራል" በማለት አሞካሽተው በሚቀጥለው ሳምንት ይፈረማል ብለው አንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

አገራቱ ስምምነቱ ላይ የደረሱት ትራምፕ ለመከላከያ ዓላማ እና ለማዕድናት ሃብት ስትራቴጂያዊ ቦታ እንደሆነች በመጥቀስ በብሔራዊ ስጋት ምክንያት ግሪንላንድን "እንደሚጠቀልሉ" ሲዝቱ ከቆዩ ከወራት በኋላ ነው።

ስምምነቱን የሚያሳይ ሰነድ እስካሁን ይፋ አልሆነም።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ስምምነት ላይ የተደረሰው "አሜሪካ ምንም ዓይነት ዋጋ ሳትከፍል እንደሆነ" ገልጸው፣ የግሪንላንድን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ከጥቃት ለመከላከል አሜሪካ "አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ" እንድታደርግ ያስችላታል ብለዋል።

ይህም "ማንኛውም የአሜሪካ ጠላት በግሪንላንድ ወታደራዊ ስምሪት ማድረግ ወይም ያለ እኛ ግልጽ ፈቃድ በግሪንላንድ ኢንቨስት ማድረግ አይችልም የሚል ሕግን እንደሚያካትት" ትራምፕ አክለዋል።

የኔቶ ቃል አቀባይ ድርጅታቸው ስምምነቱን እንነደሚያደንቅ ገልጸው "ደህንነትን፣ መረጋጋትን እና በቀጣናው ወሳኝ የሆነ ትብብርን ለማሻሻል ይረዳል" ብለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስምምነቱን " ታሪካዊ" እና "ለአሜሪካ እና ሕዝቦቿ ትልቅ ድል" ብለውታል።

የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚት ፍሬደሪክሰን ለሦስቱም ወገኖች "ስምምነቱ ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ በመኖሩ ደስተኛ ነኝ" ካሉ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በፊርማቸው እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስምምነቱ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ አካባቢ ያለውን የጋራ ደኅንነት ያጠናክራል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ "የአገሪቷን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም የግሪንላንድ ሕዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን" ያከበረ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም ስምምነቱ በሕግ አውጪዎች መጽደቅ እንደሚኖርበት ገልጸው፣ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ በሆኑ የፓርላማ ሒደቶች እንደሚያልፍ ጠቅሰዋል።

የግሪንላንድ አስተዳደር መሪ ጂንስ ፍሬደሪክ ኒልሰንም ስምምነቱን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ "የግሪንላንድን፣ የዴንማርክን እና የአሜሪካን ደኅንነት የሚያረጋግጥ እና የሚያጠናክር ስምምነት ላይ መደረስ መቻሉ የሚያስደስት ነው" ብለዋል።

"ስምምነቱ ለግሪንላንድ ፍላጎቶች እና በዓለም አቀፍ ትብብር ውስጥ ቦታ እንዳለን እውቅና የሰጠ ነው፤ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስምምነቱ በደሴቲቱ ላይ ያለውን የዴንማርክ ሉዓላዊነት "እንደገና ለማረጋገጥ" እንዳገዘ ተናግረዋል።

"የዴንማርክ ሉዓላዊነት እና ዓለም አቀፍ ሕግ መከበራቸውን፣ እንዲሁም እኛም የፈለግነው ይህንኑ እንደነበር ብቻ ነው የምጠቅሰው፤ ስለዚህ ይህ መልካም ነገር ነው" ሲሉ ማክሮን መናገራቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ትራምፕ፣ ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ ለሌሎች ጠላቶች የተጋለጠች ናት በማለት በማዕድን የበለፀገችውን በዴንማርክ ሥር የምትተዳደረውን ግዛት በገንዘብ ለመግዛት ወይም በኃይል ወደ አሜሪካ ለመጠቅለል ለወራት ሲዝቱ ቆይተዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ በግሪንላንድ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያስፈራሩም የቆዩ ሲሆን ይህም ከዴንማርክ እና ከሌሎች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ቁጣን አስከትሏል።

አሁን ላይ የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ይፋ አልተደረገም። ቢቢሲ የዴንማርክ ኤምባሲን እና ዋይት ሃውስን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ሆኖም ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተዋል።

እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው ግሪንላንድ ወደፊት ራሷን የቻለች አገር ብትሆንም ስምምነቱ በጊዜ የተገደበ እንዳልሆነ ይገልጻል።

ከዚህም በተጨማሪ ለአሜሪካ ያለ ግሪንላንድ እና ዴንማርክ ፈቃድ ተጨማሪ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል የተናጠል ሥልጣን ይሰጣል። ይህም "በፈለገች ጊዜ ወደ ግዛቷ መግባትን፣ የጦር ሠፈር መመስረትን እና የበረራ መብቶችን" ያካትታል።

ስምምነቱ በ1951 ከዴንማርክ ጋር ከተደረሰው እና አሜሪካ እንደፈለገች ወደ ግሪንላንድ ወታደሮችን መላክ ከሚያስችላት ስምምነት የሚለየው በምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

አሜሪካ በግዛቷ ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ በሚገኘው ፒቱፊክ የጦር ሠፈር በቋሚነት የሰፈሩ ከ100 በላይ ወታደሮች አሏት።