ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለ11 ዓመት ተደብቆ የቆየው ግድያ ሲጋለጥ የሟች እናት እና ወንድሞች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን፣ ሆመቾ ከተማ ውስጥ ከ11 ዓመታት በፊት በወንድሞቹ ተገድሎ ሽንት ቤት ውስጥ ተቀብሯል በተባለው ዴታሞ ኤርጉዶን ግድያ ጋር በተያያዘ የሟች እናትን ጨምሮ ሰባት የቤተሰቡ አባላት መጠርጠራቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በ2007 ዓ.ም. ኅዳር ወር የተገደለው ዴታሞ ኤርጉዶን በመግደል ተጠርጥረው የሟች እናት ፣ ሦስት ወንድሞቹ እና ሁለት የአጎቱ ልጆች መያዛቸውን የሆመቾ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አዲሱ ዘኪዮስ ተናግረዋል።
ወንጀሉ በወቅቱ በነበረው አጠራር ግቤ ወረዳ፣ ሃሊልቾ ቤሮ ቀበሌ፣ ላይኛው ጌምቤ በተባለ አካባቢ የተፈጸመ ሲሆን፣ ቦታው በአሁኑ ወቅት በሆመቾ ከተማ አስተዳደር ሰሜን ሆመቾ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ላይኛው ጌምቤ በመባል ይታወቃል።
ዴታሞ በወቅቱ ከ18 እስከ 20 ዓመት ዕድሜ ውስጥ እንደነበረ የሚገመት ሲሆን፣ አስከሬኑ አምስት ሜትር ጥልቀት ባለው፣ በቤተሰቡ መኖርያ ግቢ በሚገኝ ሽንት ቤት ውስጥ ተቀብሮ መገኘቱን ፖሊስ ጠቁሟል።
በሟች እና በቤተሰቡ መካከል ለግድያ የሚያበቃ ግጭት የተፈጠረበት ትክክለኛ ምክንያት በግልጽ እንዳልታወቀ የሚገልጹት ም/ኢንስፔክተር አዲሱ፤ ግጭቱ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ብለዋል።
በመስቀል በዓል ወቅት በተሸጠ በሬ የተነሳ በተፈጠረ የገንዘብ ጥቅም አለመስማማት ሳይሆን እንዳልቀረ ፖሊስ ግምቱን አስቀምጧል።
የዴታሞ ግድያ ለ11 ዓመታት በቤተሰቡ ውስጥ ተደብቆ እንዲቆይ ያደረገው ምሥጢር የተገለጠው በተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊሱ እንደሚሉት፣ የሟች ወንድም እና የአጎት ልጅ ሚስቶች ጸብ ውስጥ ይገባሉ።
በጸቡ ወቅት የሟች ወንድም ሚስት "የባልሽን ወንድም አስከሬን አስቆፍረሽ ታወጫለሽ" ስትል ይህ ወሬ የአካባቢው ሰዎች ጆሮ ውስጥ ይገባል። ይህንን የሰሙ ሰዎችም ለፖሊስ ጥቆማ እንዳደረሱ እና ምርመራው እንደተጀመረ ም/ኢንስፔክተር አዲሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎ የምርመራውን መከፈት የሰማ በግድያው አንደኛው ተጠርጣሪ የሆነው የሟች ወንድም ለፖሊስ እጅ መስጠቱን ፖሊስ ገልጿል። ተጠርጣሪው ግድያው በማን፣ እንዴት እና የት እንደተፈጸመ ለፖሊስ ማስረዳቱንም አስታውቀዋል።
ተጠርጣሪው በሰጠው ቃል መሠረት፣ ዴታሞ በቤተሰቦቹ በድንጋይ ተቀጥቅጦ ሕይወቱ እንዲያልፍ መደረጉን ፖሊስ ገልጿል።
ወንጀሉ የተፈጸመውም በሌሊት ሲሆን፣ ሟች በተኛበት እንደተገደለ የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ፖሊስ ጠቁሟል። ሟች በወቅቱ የውስጥ ልብስ ብቻ እንደለበሰ እና በዚያው ሁኔታ እንደተቀበረም ታውቋል።
ፖሊስ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከቤተሰብ መረጃ ለማሰባሰብ ሙከራ ማድረጉን የሚገልጹት ም/ኢንስፔክተር አዲሱ፣ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት በስፍራው የነበረችውን እና በኋላም አግብታ ከአካባቢው ርቃ መኖር የጀመረችውን የሟች እህት ቃል እንደማስረጃ መጠቀሙን አስረድተዋል።
የሟች እህት ወንጀሉን እንዳታጋልጥ ማስፈራሪያ ሲደረግባት እንደነበር እና በዚያም ምክንያት ዝምታ መምረጧን ፖሊስ ገልጿል።
ከሟች ወንድሞች በተጨማሪ ተጠርጥራ የተያዘችው የሟች እናትም ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት በቦታው እንደነበረች ፖሊስ ጠቁሟል።
ምክትል ኢንስፔክተር አዲሱ እንደሚሉት "እናትም ዝምታን መርጣ፣ አንደኛውን ሞቷል፣ ይቀበር" የሚል ሃሳብ ማንሳቷን ካሰባሰቧቸው ማስረጃዎች እንዳገኙ ገልጸዋል።
ሌላኛው ተጠርጣሪ የሟች ወንድም፣ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ እንደነበር የጠቆመው ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመበት ጊዜ በቦታው ባይኖርም፣ በግድያው ዙሪያ የተሰጠ ምስክርነት እና የተገኘ ፍንጭ ተጠርጣሪ እንዲሆን ምክንያት አድርጎታል ብሏል።
ፖሊስ እንደሚለው፣ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች አንዱ በሰጠው ቃል፣ ይህ ግለሰብ በደቡብ አፍሪካ በነበረበት ወቅት ቤተሰቡ ዴታሞ እንዳስቸገራቸው ሲነግሩት፣ "ገድላችሁ ጉድጓድ ውስጥ ቅበሩት" ማለቱ ተነግሯል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ግድያው እንዲፈጸም ሃሳብ ሰጥቷል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገበት መሆኑም ተጠቁሟል።
ሌላኛው ተጠርጣሪ የሟች ወንድም በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስለሚገኝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋል አልቻለም።
ጉዳዩ ለ11 ዓመታት ተደብቆ የቆየበትን ሁኔታ በተመለከተም ፖሊስ ሲያስረዳ ቤተሰቡ በጋራ በመተባበር ወንጀሉን መሸፈኑን ገልጿል።
"ዴታሞ የት ሄዶ ነው?" ብሎ አንድ የአካባቢው ሰው ቤተሰቡን ጠይቆ እንደነበር እና "መከላከያ ገብቷል" የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ፖሊስ ምርመራ ባደረገበት ወቅት ያገኘው መረጃ እንዳመላከተ ም/ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።
ም/ኢንስፔክተር አዲሱ እንደሚሉት፤ በቤተሰቡ እና በሟች መካከል ቀድሞውኑ አለመግባባቶች ነበሩ።
ዴታሞ ከመገደሉ አንድ ዓመት በፊት "ይሰርቃል፣ ቤት ውስጥ ያስቸግራል" በሚል እንዲታሰር አድርገው እንደነበር ፖሊስ ጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት ፖሊስ የዴታሞን አስከሬን ለማጣራት የፎረንሲክ ምርመራ እያካሄደ ነው።
ምክትል ኢንስፔክተር አዲሱ፣ "አስከሬኑ በመውጣቱ እና በመመርመሩ ትልቅ ውጤት ያመጣልናል የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል።
የፎረንሲክ ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ የተገኙ መረጃ እና ማስረጃዎች ለሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ እንደሚተላለፉ ከዚያም ጉዳዩ በሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚታይ ም/ኢንስፔክተር አዲሱ ተናግረዋል።