የኢንዶኔዥያ ታጣቂዎች አሜሪካዊ አብራሪን መግደላቸውን እና አውሮፕላኑን ማቃጠላቸውን አስታወቁ

ጭስ የሚነሳበት ተራራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኢንዶኔዥያ ውስጥ በምትገኘው ፓፑዋ ግዛት የሚንቀሳቀሱ ተገንጣይ አማፂያን፤ አሜሪካዊ አብራሪን ተኩሰው መግደላቸውን እና አውሮፕላኑን ማቃጠላቸውን አስታወቁ።

'ዘ ዌስት ፓፑዋ ናሽናል ሊብሬሽን አርሚ' የተሰኘው ታጣቂ ቡድን፤ ኒኮላስ ኤፍ ጎስሊን የተባለውን አሜሪካዊ አብራሪ የገደለው ሐሙስ ዕለት በሀይላንድ ፓፑዋ ግዛት ካረፈ በኋላ መሆኑን አስታውቋል።

የሲቪል አውሮፕላን አብራሪው የኢንዶኔዥያን ወታደሮች ወደ ቀጠናው እያጓጓዘ ነበር ሲሉ የከሰሱት ተገንጣይ አማጺያኑ፤ የአብራወው ሞት "መልዕክት" አስተላልፏል ብለዋል።

በተፈጥሮ ሀብት በበለጸገችው ሀይላንድ ፓፑዋ ግዛትን ነጻነት ለማወጅ የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ የኢንዶኔዥያ መንግሥት እና የምዕራብ ፓፑዋ ተወላጆች ለዓመታት ግጭት ውስጥ ናቸው።

የኢንዶኔዥያ ባለስልጣናትም የጎስሊን አውሮፕላን ተቃጥሎ መገኘቱን አረጋግጠዋል። አብራሪው እና አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሰባት ተሳፋሪዎች ላይ የተፈጠረውም ምን እንደሆነ ግን አለመታወቁን ገልጸዋል።

በአሜሪካዊው ዜጋ ሲበርር የነበረው እና ሰባት ተሳፋሪዎችን የጫነ አውሮፕላን ተቃጥሎ የተገኘው ያሁኪሞ የተባለው ክልል በሚገኝ አንድ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እንደገለጸው አውሮፕላኑ ለማረፍ በተቃረበበት ሰዓት የተከሰተ የደኅንነት ስጋት አልነበረም። ካረፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ግንኙነቱ መቋረጡን ባለሥልጣኑ አስረድቷል።

አውሮፕላኑ ከተነሳበት አየር ማረፊያ ዳይሬክተር የተገኘው የመጀመሪያው ሪፖርት አብራሪው መሞቱን እንደሚያሳይ የአገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክቶሬት ጄነራል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መግለጫው አክሎም፤ "ክስተቱ ለመፈጠሩ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የተጠረጠረው ጉዳይን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ተጨማሪ ማረጋገጫ እየተጠበቀ ነው" ብሏል።

የኢንዶኔዥያ የፖሊስ እና ወታደራዊ ጥምር ኦፕሬሽን ቃል አቀባይ ዩሱፍ ሱቴጆ፤ በአማፂያን አውሮፕላኑ ላይ ጥቃት ስለመፈጸማቸው ወይም ውስጥ በነበሩት ተሳፋሪዎች ላይ ምን እንደደረሰ ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቢቢሲ በጃካርታ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

የአማጺው ቃል አቀባይ ሰቢ ሳምቦም ባወጡት መግለጫ፤ የሲቪል አውሮፕላኖች የኢንዶኔዥያን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ እያገለገሉ በመሆኑ፤ ታጣቂ ቡድኑ አወዛጋቢ በሆኑት ግዛቶች የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች ላይ ክለከላ መጣሉን ገልጸዋል።

"አውሮፕላኑ የታጣቂ ቡድኑን ማስጠንቀቂያ በመጣሱ ወዲያውኑ ተተኩሶበታል፤ ተቃጥሏል" ብለዋል።

"በመላው በፓፑዋ ምድር ወታደሮችን ወይም ሎጅስቲክስ በማጓጓዝ ለኢንዶኔዥያ ጦር ኃይል እገዛ የሚያደርግ ማንኛውንም የሲቪል አውሮፕላንን ለመምታት ዝግጁ ነን" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የኢንዶኔዥያ ባለስልጣናት የፓይለቱን አስከሬን መረከብ የሚፈልጉ ከሆነ ወታደር ወይም ፖሊስ ሳያስከትሉ ወደ አከባቢው መምጣት እንዳለባቸው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የኢንዶኔዥያ መንግሥት ግጭቱን ለመቋጨት ለሚያስችል ድርድር ክፍት እንዲሆንም አክለው ጠይቀዋል።

የሁለቱ አካላት ግጭት የጀመረው ፓፑዋ በአውሮፓውያኑ 1969 ወደ ኢንዶኔዥያ መካተቷን ተከትሎ ነው። ለዓመታት የተካሄደው ግጭት ለንጹኃን ሞት እና መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ታጣቂዎቹ ይናገራሉ።

2024 ላይ ይኸው ታጣቂ ቡድን ለ19 ወራት በእስረኛነት ይዞት የነበረውን የኒውዝላንድ አብራሪ ከረጅም ድርድር በኋላ ለቅቋል። ከአንድ ወር በፊትም ታጣቂዎቹ ገጠራማ መንደር ሄሊኮፍተር ያሳረፈ የኒውዚላንድ ዜጋ አብራሪን ገድለዋል።